በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በድንበር አካባቢ ባለ የቦታ ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ከመግባባት መድረስ የተሳናቸው ኢትዮጵያ እና ሱዳን አሁን ደግሞ ይህንን አለመግባባታቸውን ሊያሰፋ የሚችል ሌላ ሶስተኛ ጉዳይ የገጠማቸው ይመስላል።
ከሰሞኑ የሱዳን ዜና ወኪል በአገሪቱ ደቡብዊ ግዛት ውስጥ ለሚገኘውና እራሱን የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ እንቅስቃሴ የሰሜኑ ክፍል በሚል ለሚጠራው አማፂ ኃይል ያባስ የሚባል ከተማ ላይ ኢትዮጵያ የሎጀስቲክስ ድጋፍ አድርጋለች የሚል ክስ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
በርግጥ የዜና ወኪሉ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳደረገች ተናገረ እንጂ ተደርጓል የተባለውን ድጋፍ በተጨባጭ ሊያጠናክር የሚችል ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረበም።
ከኢትጵያ ጋር በድንበር አካባቢ ያለውን የቦታ ይገባኛል ጥያቄ ለማስተጓጎል በደቡብ ሱዳን የአገሪቱ ክፍል ኩምሩክ ከተማ ላይ በጆሴፍ ቱካ የሚመራው ኃይል ወረራ እንዲፈፅም ኢትዮጵያ ወታደራዊ የመሳሪያ ድጋፍ እንዳደረገች የዜና ወኪሉ ቢናገርም ኢትዮጵያ በሱዳን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባና መሰል ወታደራዊ ድጋፎችን እንዳላደረገች ማስታወቋ አይዘነጋም።
ከኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ዕርዳታ ተቀብለዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ እንቅስቃሴ የሰሜኑ ክፍል ምክትል ሊቀ-መንበር ኮማንደር ጆሴፍ ቱካ አሁን ላይ በሰጡት መግለጫ “ከኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ እርዳታ ተቀብለሃል መባሌ የፈጠራ ወሬ ነው” ሲሉ አስተባብለዋል።
“ጦርነት አገሪቱን ወደ አለመረጋጋትና መበታተን የሚያደርስ ነው” ያሉት ኮማንደር ጆሴፍ “ሰላማዊ የሽግግር ሂደትን እንደሚደግፉ” አስታውቀዋል።
“በሱዳን የሽግግር መንግስት ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ጥቃት ለመሰንዘር ቀድመው የጦር ነጋሪት እየጎሰሙ ነው” ያሉት ምክትል ሊቀ-መንበሩ የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ተቀብሏል መባሉን “የፈጠራ ውሸት” ሲሉ አጣጥለውታል።
ከመንግስት ጋር የሰላም ድርድር ስለማድረግ የተጠየቁት ኮማንደር ጆሴፍ “ሱዳን ለሁሉም አማራጮች ክፍት ናት” ካሉ በኋላ የሰላም ድርድር ላይ ግን አሉታዊ አስተሳሰብ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን በመገምገም የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ በሱዳን ድንበር ላይ ታጣቂዎችን የማሰልጠን እና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ንግዶች ሲከናወኑ እንደነበር ከሕብረተሰቡ እና ከመተከል ኮማንድ ፖስት መረዳት መቻሉን በኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ በኩል መግለፁ የሚታወስ ነው።