የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የዘንድሮው ምርጫ ላይ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዕጩዎቼን አስመዝግቤ እንድወዳደር የሚፈቅድልኝ ከሆነ ወደ ምርጫው እመለሳለሁ ሲል አስታውቋል።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ እና አሁን ላይ ተደረገ በተባለ ጉባዔ የፓርቲው ሊቀ-መንበር ሆነው በተሾሙት አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ በመካከሉ ልዩነቶች መፈጠራቸውና ልዩነቱን ለመፍታት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጭምር አውጥቶት በነበረው መግለጫ ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ከዚህ ቀደም ከሁለቱም ወገን የገቡትን እገዳዎች በማየት እና የገቡ ሰነዶችን በመመርመር እንዲሁም ከሁለቱም ቡድን አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይት አድርጌ ነበር የሚለው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በውይይቱ ወቅት ፓርቲው የአመራር ቀውስ ውስጥ እንደገባ፣ ለአባላቱ አመራር መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ፣ በተለይም ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ያቀረቧቸው እገዳዎች ህጋዊ እንዳልሆኑ ተገንዝቤ ነበር ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም።
ቦርዱ በያኔው የድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ አራርሶ የሚመራው የስራ አስፈጻሚ ቡድን በጠራሁት ስብሰባ ላይ ሲገኝ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን ግን “ቦርዱ ይህንን የማመቻቸት ህጋዊ ሚና የለውም” በማለት በውይይቱ ላይ አልገኝም፤ በዚህም ያደረኩት ጥረት ሊሳካ አልቻለም ሲል መናገሩ ይታወሳል።
ቦርዱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት፣ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አመራሮች ለችግሩ መፍቻ ሊሆን የሚችለውን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉና ይህንን ለማድረግ ማንኛውንም መንገዶች እንዲጠቀሙ ማሳሰቡ አይዘነጋም።
ታዲያ አሁን ላይ ተደረገ በተባለ ጉባዔ አራርሶ ቢቂላ የግንባሩ ሊቀመንበር ሆነው ከመሾማቸው በተጨማሪ አቶ ብርሃኑ ለማ እና አቶ ቀጄላ መርዳሳ ምክትል ሊቀመንበር ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጉባዔው 43 ቋሚ እና 5 ተለዋጭ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መርጧል። በጉባዔው ህገ ደንቡን ያሻሻለው ፓርቲው የስነ ስርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴም አቋቁሟል።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን በይፋዊ ድረ-ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ በእኛ ዋና ጽ/ቤት የተካሄደው ጉባዔ ህገ-ወጥ ነው ያለ ሲሆን ፖሊስም ቢሆን ይህንን መሰል ህገ-ወጥ ስብሰባ እንዲካሄድ የመፍቀድ ህጋዊ ስልጣን የለውም ብሏል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዕጩዎቼን እንዳስመዘግብ የሚፈቅድልኝ ከሆነ ከዘንድሮው አገራዊ ምርጫ አልወጣም ማለቱን ተከትሎ አዲስ ዘይቤ ቦርዱ በጉዳዩ ላይ ምላሹ ምን እንደሆነ ጥያቄ አቅርበናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በምላሹ ኦነግ ወደ ምርጫው ለመግባት ዕጩዎቹን ማስመዝገብ እንዲችል ውሳኔ ሊተላለፍ የሚችለው አስፈላጊ ህጎችን መሰረት በማድረግ የቦርዱ አባላት በሚወስኑት ውሳኔ መሰረት ነው ሲል አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ እስካሁን የተወሰ ውሳኔ ስለመኖሩ ግን የቦርዱ የኮሙኑኬሽን ክፍል የደረሰው ነገር እንደሌለ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።