መጋቢት 8 ፣ 2013

የዋጋ ንረቱን መስመር ለማስያዝ እየተሞከረ ነው ተባለ

City: Adamaወቅታዊ ጉዳዮችከተማ

የአዳማ ገበያ ልማት ጽ/ቤት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ንረት ላይ ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የዋጋ ንረቱን መስመር ለማስያዝ እየተሞከረ ነው ተባለ

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ንረት አስመልክቶ ‹‹ሠራተኞችን አሰማርቼ ጥናት በማድረግ ላይ ነኝ›› ሲል የአዳማ ገበያ ልማት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ በአዳማ ከተማ ገበያ ልማት ጽ/ቤት የገበያ ሕጋዊነት እና መሠረታዊ ልማት ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ጥበቡ ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ‹‹የዋጋ ንረቱ በአስገራሚ ሁኔታ መስመሩን ስቷል›› ብለዋል፡፡ አስተባባሪዋ እንዳሉት ቢሯቸው እያካሄደው በሚገኘው ጥናት የዋጋ ጭማሪው ከምርት አቅራቢዎች እንደሚነሳ ለማወቅ ችሏል፡፡

የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በከተማዋ ሦስት ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገበያዩበት አመዴ ገበያ ተገኝታ ያነጋገረቻቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉት የዋጋ ንረቱ በዚህ ከቀጠለ በልቶ አለማደር ደረጃ ሊደርሱ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው፡፡
‹‹ከጥራጥሬ ዘሮች ርካሽ የነበረው በቆሎ እንኳን በኪሎ 20 ብር ገብቷል፡፡ ዳቦ ከ3 እስከ 6 ብር እየተሸጠ ነው›› ያሉት ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወ/ሮ ትአግስት ገመቹ ናቸው፡፡ ሌላዋ ሸማች ወ/ሮ ብርሃኔ ‹‹የዋጋ ጭማሪው የትኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል አቅም ያላገናዘበ ነው፡፡ የሽንኩርት፣ የቃሪያ፣ የቲማቲም ዋጋ በዚህ ደረጃ ይጨምራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው›› ብለዋል፡፡

የስጋ ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ኃይሉ ሰሙ ወቅቱ የጾም በመሆኑ የአገልግሎት ዘርፋቸውን ከስጋ ወደ አሳ ቢዞሩም ከዋጋ ንረቱ አለማምለጣቸውን ይናገራሉ ‹‹ለአሳው የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቅመማ ቅመሞች በኪሎ ከ40 እስከ 50 ብር እየተሸጡ ነው፡፡ አንድ ኪሎ ሎሚም አንድ መቶ ብር ገብቷል፡፡ እኔም ዋጋ ጨምሬ ስለምገዛው ተጠቃሚው ላይ ዋጋ እጨምራለሁ›› ሲሉ ለሪፖርተራችን ነግረዋታል፡፡

በመሰረታዊ ጥሬ እቃዎች ሽያጭ ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ ረሂማ ሀሰን በበኩላቸው ‹‹አምራቾች ዋጋ ስለጨመሩ አከፋፋዮች ጨምረው ይሸጡልናል፡፡ እኛም በውድ የተረከብነውን ወጪአችንን እና ትርፋችንን ደምረንበት ለተጠቃሚ እናቀርባለን፡፡ ይህ ሂደት ሕብረተሰቡ ላይ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል›› የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በአዳማ ከተማ ገበያ ልማት ጽ/ቤት የገበያ ሕጋዊነት እና መሠረታዊ ልማት ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ጥበቡ መሰረታዊ ሸቀጣሸቀጥ አቅራቢዎች እና የሰብል ምርት የሚያቀርቡ ገበሬዎች ዋጋ በመጨመራቸው ምክንያት ነጋዴው እጁ ላይ ባለው ሸቀጥ ላይ የዋጋ ጭማሬ አድርጓል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ከገበሬ ዩኒየኖች እና የነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ በዚህም እንደ መንግሥት ዩኒየኖችን በመደገፍ፣ መሰረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላት ለነጋዴው ሕብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን እንዲያስረክቡ፤ ነጋዴዎች በገቢ ዝቅተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማይጎዱበት መልኩ ግብይት መፈፀም እንደሚገባቸው ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

አስተያየት