ራሷን ካሳታት በኋላ አስገድዶ የደፈራትን ሴት ምስል በፎቶና ቪድዮ አስቀርቶ ገንዘብ የጠየቀው ግለሰብ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ፡፡
አብርሃም አበበ የተባለው ተከሳሽ አስገድዶ በመድፈር፣ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ባህርይ በማሳየት እና በማስገደድ ወንጀሎች ሦስት ክሶች የተመሰረቱበት ሲሆን፤ የባህርዳር ከተማ ፍርድቤት መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
የወንጀል መዝገቡ እንደሚያሳየው ተከሳሹ፡ ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ባህርዳር ከተማ ቀበሌ 15 የግል ተበዳይን ትምህርት ቤት ውላ ቤቷ ስትመለስ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ውስጥ አንገቷን አንቆ አስገብቷታል፡፡ ወደ ‹ፔንስዮን› ወስዶ ህሊናዋን ካሳታት በኋላም ደፍሯታል፡፡ የተበዳይዋን ራቁት በፎቶና በቪድዮ አስቀርቶ ለማስፈራራት ተጠቅሞበታል፡፡ ገንዘብ የማትሰጠው ከሆነ ፎቶ እና ቪድዮውን በምትኖርበት አካባቢ እንደሚያሰራጭ በጽሑፍ እና በቃሉ አስፈራርቷታል፡፡
አብርሃም አበበ በዚህ ድርጊቱ በ1996 ዓ.ም. የወጡትን ሦስት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግጋት ተላልፏል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ ቁጥር 620/1፣ አንቀጽ ቁጥር 641፣ አንቀጽ ቁጥር 582 ላይ የተደነገጉትን በመተላለፉ፣ የባህርዳር ከተማ ፍርድቤት በአስራ አንድ ዓመት ጽኑ እስራትና በሦስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
መጋቢት 9 ፣ 2013
ባህርዳር፡ በራቁት ምስል ያስፈራራውና የደፈረው ግለሰብ ተቀጣ
ራሷን ካሳታት በኋላ አስገድዶ የደፈራትን ሴት ምስል በፎቶና ቪድዮ አስቀርቶ ገንዘብ የጠየቀው ግለሰብ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ፡፡