የመቐለ 104.4 ጋዜጠኞችና ሠራተኞች መሥሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ መታገዳቸው ተሰማ፡፡
በያዝነው ወር መጀመርያ ከቤት ያለመውጣትና የንግድ ተቋማትን ያለመክፈት አድማ በተደረገበት ወቅት ሥራ ገበታችሁ ላይ አልተገኛችሁም በሚል የታገዱት ሰራተኞች ቁጥር ከ50 በላይ እንደሚገመት ለአዲስ ዘይቤ መረጃውን የሰጡ ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዘገባ ላይ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ሠራተኞች ሥራ ያልገባው ሰው በሙሉ አድማውን ደግፎ እንደቀረ መታሰቡ ስህተት ነው፡፡ አጼ ዮሐንስ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኘው መቐለ ኤፍኤም ለመድረስ ታክሲ ወይም ባጃጅ መጠቀም ግድ የሚሆንብን ሰራተኞች ሥራ ያልገባነው ለደህንነታችን በመስጋት ነው ብለዋል፡፡
በራድዮ ጣቢያውና በመቐለ ዩንቨርሲቲ ትብብር በዓመት ሁለት ሰዎች በሚያገኙት የትምህርት እድል ተጠቃሚ የሆኑት 4 ሰራተኞች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውንም የሪፖርተራችን ዘገባ ያመላክታል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የጣቢያውን ሰራተኞች የግል ማህደር በማጣራት ላይ መሆኑን መስማታችን ስጋታችንን አባብሶታል የሚሉት ጋዜጠኞችና የአስተዳደር ሰራተኞች የከተማዋንም ሆነ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ የማያስገባ ውሳኔ እንዳይወሰን እንደሚሰጉ ተናግረዋል፡፡