መጋቢት 09 ቀን 2013 ዓ.ም ዕለት በተደረገ ምርመራ በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከፍተኛው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል።በዚህም ምርመራ ከተደረገላቸው 8,055 ሰዎች መካከል በሽታው በ2,057 ሰዎች ላይ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ያወጣው መረጃ አመላክቷል።ይህ ማለት ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች ውስጥ 26 ወይም 25.5 በመቶው የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል ማለት ነው ያለው ኢንስቲትዩቱ "በማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ወቅት እንኳን ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር አልተመዘገበም" ብሏል።
በተያያዘም ቫይረሱን በ30 ደቂቃ ውስጥ መመርመር የሚያስችሉ 70 የምርመራ ማዕከላት እንደሚቋቋሙና ከነዚህ ውስጥ አስሩ ማዕከላት በትግራይ ክልል እንደሚሆኑ ተነግሯል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በስራ ላይ ያሉት የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያዎች ቫይረሱን ለመለየት ከ4 እስከ 7 ሰዓት ይፈጅባቸዋል ተብሏል።
ከሰሞኑ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ "በአስደንጋጭ ሁኔታ" እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የሰጧቸው መግለጫዎች ያመለክታሉ። ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በኢትዮጵያ እየተሰራጨ ቢሆንም አደጋውን ከግንዛቤ በማስገባት ተገቢውን የመከላከያ ጥንቃቄ "ከማድረግ ይልቅ መዘናጋት በሰፊው እንደሚታይ" የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተሳተፈባቸው የተለያዩ ስብሰባዎችና ዝግጅቶችን የታዘቡት የጤና ባለሙያዎች ችግሩ ሕብረተሰቡ ጋር ብቻ ሳይሆን መንግሥት የጤና ሚኒስቴር የሚያስቀምጣቸውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መመሪያዎች ለማስፈፀም ተነሳሽነት እንደሚጎድለው አስታውቀዋል።
በመላው አገሪቱ በጽኑ ለታመሙ ሰዎች እጅጉን አስፈላጊ የሆኑት የኦክስጅንና የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እጥረት በመከሰቱ በርካታ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ህይታቸውን አደጋ ላይ እንደሆነ መነገሩ የሚታወስ ነው።
የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ግን የቫይረሱ ጥቃት አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ ከመናገር አልተቆጠቡም። “ሁሉም የመተንፈሻ መሳሪያዎች በህመምተኞች ተይዘው ሌላው የጠናበት ህመምተኛ መሳሪያውን በሞት እና በሕይወት መካከል ሆኖ እየጠበቀ ነው” የሚሉት የጤና ሚኒስትሯ “በአዲስ አበባ 54 በመቶ በአገር ደረጃ ደግሞ 35 በመቶ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል (ማስክ) ተጠቃሚዎች ቁጥር እንደቀነሰ” መናገራቸው አይዘነጋም።
የጤና ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ላይ በ2 ተከታታይ ቀናት ብቻ 615 ሰዎች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል መግባታቸውን እና የ29 ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልፀው ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ ማሽን ውስንነት በመኖሩ አገልግሎቱ በወረፉ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ግዜ ድረስ በኢትዮጽያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 181,869 ደርሷል፤ 2,602 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። በፅኑ ህክምና ላይ ያሉና ከፍተኛ ክትትል የሚፈልጋቸው ታካሚዎች ቁጥር ደግሞ 600 ደርሷል ተብሏል።
ከአንድ አመት በፊት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በመስሪያ ቤታቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ ለመስጠት የተሰየሙት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ጃፓናዊ የ48 አመት ጎልማሳ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ከገለፁ በኋላ የተስተዋለው የጥንቃቄ ዕርምጃ አሁን ላይ በእጅጉ እንደቀነሰ አዲስ ዘይቤ ባደረገው ቅኝት ታዝቧል።