ሐምሌ 19 ፣ 2013

ጉብኝት እና ግብይት፤ ከቁልቢ እስከ ሐዋሳ ገብርኤል

ባሕልንግድ

በክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሰዎች ራቅ ወዳለ ቦታ ተጉዘው ከሚያከብሩባቸው በዓላት ውስጥ አንዱ ሲሆን ከበዓሉ የዋዜማ ቀናት አንስተው እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ደብሮቹ የሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ ይጓዛሉ፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ጉብኝት እና ግብይት፤ ከቁልቢ እስከ ሐዋሳ ገብርኤል
Camera Icon

Photo credit : CamelKW, Flicker, St. Gabriel Ethiopian Orthodox Church, Hawassa, Ethiopia

ለሃገር ውስጡም ሆነ ለዓለም አቀፉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተግዳሮት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሃገራት ከሌሎች ሃገር ዜጎች ሊጎበኟቸው የሚመጡ ዜጎች ቫይረሱ ያገኛቸው እንዳይሆኑ በመስጋት በራቸውን ዘግተዋል፡፡ ጎብኚዎቹም የጉዞ ፍላጎታቸውን በቫይረሱ ስጋት ምክንያት አቅበዋል፡፡ ቱሪዝሙ ከወራት ቆይታ በኋላ በጥቂቱም ቢሆን የመነቃቃት እንቅስቃሴ በማሳየት ላይ ያለ ይመስላል፡፡ በሐገር ውስጥ የየብስ ትራንስፖርት ላይ የተተገበረው በግማሽ ተጓዥ እጥፍ ክፍያ መመሪያ መነሳቱን፣ ወደ ልዩ ልዩ ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የጉዞ ገደብ ከኮቪድ እንቅስቃሴ ጋር መፈቀዱን፣… ተከትሎ የሐገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ይገኛል፡፡

ከቱሪዝም ዘርፎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሐገር ውስጥ ቱሪዝም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከፍ ያለ አስቷዋጽኦ እንደሚያበረክት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሰዎች ከመደበኛ የመኖርያ አድራሻቸው ርቀው ወደሌሎች አካባቢዎች በሚጓዙበት ጊዜ እግረ መንገዳቸውን ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሐይማኖታዊ የሆኑ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶችን ይጎበኛሉ፡፡ የሐገር ውስጥ ጎብኚዎች የጉዞ ምክንያታቸው የተለያየ ቢሆንም በእግረ-መንገድ ወይም እንደ ሁለተኛ ምክንያት በተጓዙበት ሥፍራ የሚገኙ መስህቦችን ጎብኝተው፣ የአካባቢዎቹን ምርት ገብይተው ይመለሳሉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሐገር ውስጥ ጉብኝቶች የጉዞ ምክንያት ቤተሰብ ጥየቃ፣ ማኅበራዊ ክንውኖች (ቀብር፣ ሰርግ) ወይም ሐይማኖታዊ ጉዞዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በዛሬ እለት በክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሰዎች ራቅ ወዳለ ቦታ ከሚጓዙባቸው በዓላት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የሐይማኖቱ ተከታዮች ከበዓሉ የዋዜማ ቀናት አንስተው እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ደብሮቹ የሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ ይጓዛሉ፡፡ ዘብር ገብርኤል፣ ቁልቢ ገብርኤል፣ ሐዋሳ ገብርኤል ከመሐል ሐገርም ሆነ ከአጎራባች አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ለመሳለም፣ ሐይማኖታዊ በረከት ለማግኘት፣ ስለታቸውን ለማድረስ እና ለሌሎችም ምክንያቶች ይጓዛሉ፡፡ ሐዋሳ እና ድሬዳዋ የሚገኙ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተሮቻችን በየአካባቢያቸው ያለውን የበዓል አከባበር ድባብ እንዲህ ቃኝተውታል፡፡

ሐዋሳ

የእጅ አምባር ጨሌ፣ የአንገት እና የተለያዩ ባህላዊ መጊያጊያጫ ቁሳቁሶችን የሚሸጠው ወጣት ተስፋሁን መና በተለይ ባለመስቀል የጨሌ የእጅ አምባሮች እና የአንገት ሀብሎች በብዛት ይዞ ቀርቧል። ‹‹እነሱን እንግዶቹ ይፈልጓቸዋል›› ይላል። በተለይ ባለ ጨሌ የእጅ አምባሮች ከዚህ ቀደም ከ25 - 40 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረው አሁን ላይ እንደአመጣጣቸው ከ30- 50 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል። የዘምባባ ባርኔጣ እና የሀመር ባለብረት የእጅ አምባሮችንም በስፋት እንግዶች የሚገዟቸው ነገሮች እንደሆኑ ይናገራል።

“እኔም ወደ ከተማዋ ክብረ-በዓሉን ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች ጌጣጌጦቼን ይዤ ለመቅረብ ተዘጋጅቻለሁ።›› ሲል ለአዲስ ዘይቤ አብራርቷል።

የቅዱስ መኝታ ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ፍላጎት አክሊሉ በበከላቸው ‹‹ለክብረ በዓሉ በሚመጡ እንግዶች ከተማ ውስጥ ያሉ ሆቴል እና መኝታ ቤቶች ሙሉ ይሆናሉ። ይህም ምዕመኑን እንደ ሻሸመኔ ያሉ የሀዋሳ አጎራባች አከባቢዎች ላይ ሄዶ እንዲያርፍ ያስገድደዋል። እኛም ይህን ለመቅረፍ ባሳለፍነው ዓመት ከነበሩን መኝታ ክፍሎች በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ መኝታ ቤቶችን ቀድመን አዘጋጅተናል›› ብለዋል። ይህም ከበዓሉ አንድ እና ሁለት ቀን ቀደም ብለው በዋዜማው ለሚመጡ እንዲሁም የበዓሉን እለት ጨምሮ ማረፍ ለሚፈልጉ ዝግጁ የተደረጉ ናቸው ብለዋል።

ወይዘሮ ገነት ማዳ በተለምዶ በሀዋሳ አሮጌው ገበያ በጥሬ ቡና ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚነግዱ ሲሆን የሲዳማ ቡናን ጨምሮ የከፋ እና የጅማ ቡናዎችንም ይሸጣሉ። የኛን የነጋዴዎች የኢኮኖሚ ደረጃ የሚያሻሽልልን ትልቅ በዓል ነው ብለዋል። ለክብረ በዓሉ በሚመጡ እንግዶች አማካኝነት በቀን ከአንድ እና ከሁለት ማዳበርያ በላይ ቡና እንሸጣለን። ይህም በኪሎ እንደ ቡናው ጥራት ከ160 -200 ብር ድረስ ይሸጣል ብለዋል።

አሳ ገበያ በተለምዶ አሞራ ገደል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአሳ ንግድ የሚተዳደሩት አቶ ሌጣ ያሬድ ቦታው እንግዶች አሳ ለመመገብ ሲሉ በብዛት የሚጎርፉበት መሆኑን ጠቅሶ ከዚህ ቀደም ለጥብስ የሚቀርበው አሳ (ቆሮሶ) ተጠብሶ ከ25 - 30 ብር ድረስ ይሸጥ ነበር አሁን ላይ ወቅቱም የቅዝቃዜ እንደመሆኑ መጠን አሳዎቹ ይደበቃሉ፤ አሳ አስጋሪውም የማጥመድ አቅሙ ይቀንሳል። በእነዚህ እና የመጥበሻ ዘይት፣ ማገዶ ዋጋ መጨመር ምክንያት አንዱን አሳ ጠብሰን ከ35 -40 ብር ድረስ እየሸጥን እንገኛለን ሲል ገልጧል።

በሀዋሳ የሚገኙ ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻ ሆቴሎች ሌዊ ሪዞርት፣ ሄሮን ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ ሌክ ቪው እና ኦሲስ ኢንተርናሽናል ሆቴሎች ለክብረ በዓሉ በሚመጡ እንግዶች ከበዓሉ በፊት በማስያዛቸው ሞልተዋል። ኃይሌ ሪዞርት እና ሮሪ ሆቴል እስከአሁን ድረስ ባለው ወደ ከተማዋ በሚመጡ እንግዶች አማካኝነት የማረፊያ ክፍሎቻቸው ከ75 በመቶ በላይ ተይዘዋል።

ድሬዳዋ

ሌላዋ የቁልቢ ገብርኤልን ክብረ-በዓል ተከትሎ ድሬዳዋና አካባቢዋ ያሉ ከተሞች ይደምቃሉ።  ለበዓሉ የሚመጡ ታዳሚዎች ድንች እና ፉል በብዛት ይመገባሉ። አብዛኛው ሰው በግለሰብ ደረጃ ነግዶ የሚያተርፍበት ሲሆን እንደ ከተማ ግን ቁልቢ ላይ ብዙ እንግዶች ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን ተከትሎ ከተማዋን ከማስዋብ አንፃር ምንም እንዳልተሰራ ለመታዘብ ችለናል። ቁልቢ ገብርኤል በዓል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር የገብርኤል ንግሥ ክብረ በዓል ሲሆን በዚህ የንግሥ በዓል ላይ ለመታደም ከ100,000 በላይ ህዝብ በተለያየ የእድሜ ደረጃ ውሰጥ የሚገኙ ከተለያዩ የኢትዮጵያ የሀገር ክፍል የሚገኙ ሰዎች የሚገኙበት እንዲሁም ከተለያዩ የዓለማችን ክፍል ይህንኑ ክብረ-በዓል ለመታደም የሚመጡበት የቱሪስት መዳረሻም ነው።

ከሀይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ በጣም ብዙ ህዝብ ወደ ስፍራው በመምጣቱ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪውና በዚያ አካባቢ በወቅቱ በንግድ ላይ የሚሰማሩ ግለሰቦች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ያገኙበታል። በዚህ ጊዜ ከንግድ እንቅስቃሴው የሚጠቀሙት በቁልቢ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ከድሬዳዋና ከሀረርም ለንግድ የሚሄዱ ሰዎች በእጅጉ ይጠቀማሉ። በተለይ ከድሬዳዋ የምግብ አገልግሎት ለመስጠት፣ ጧፍ፣ ሻማ፣ ቲሸርት እና የመሳሰሉትን ነገሮች የሚነግዱት ከድሬዳዋ የሚሔዱ ነጋዴዎች ናቸው። የአከባቢው ነዋሪ በብዛት የሚጠቀመው ባዶ መሬት እና ቤት በማከራየት ነው። በሌላው ጊዜ ቢከራዩ ለወር የሚከፍሉትን በወቅቱ ለ3 ቀን ያስከፍላሉ።

ይህ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ ታህሳስ 19 እና ሀምሌ 19 የሚከበር ሲሆን በሁለቱም ወቅት በጣም ይደምቃል ነገር ግን በሀምሌው ገብርኤል ከቅዝቃዜው በተጨማሪ ዝናብም ስለሚሆን የኪራይ ዋጋ ይጨምራል። ከድሬዳዋ የተለያዩ ነገሮችን ከሚነግዱት መካከል የተለያዩ የቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች በዚህ ንግድ ላይ ከሚሳተፉት አካላት ይጠቀሳሉ። በታህሳስ ገብርኤል ወቅት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሰንበት ተማሪዎች ባዶ ትንሽ መሬት በ5000 ብር ለ3 ቀን የተከራዩ ሲሆን ቁርስ ሰዓት ፖስቲ፣ አንባሻ፣ ድንች፣ ፍርፍር እንዲሁም ሻይ እና ቡና ሲሸጡ ምሳ ደግሞ በየዓይነት እና የመሳሰሉትን ሸራ በመወጠር እንደሚቀርብ የሰንበት ት/ቤቱ ጸሐፊ ዘአማኑኤል ሳምሶን አጫውቶናል። ሌላው በድሬዳዋ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ደግሞ ቤት የተከራዩ ሲሆን ለ3 ቀን ቆይታ 20,000 ብር እንዳስከፈሏቸው የሰንበት ት/ቤቱ አባል የሆነችው ኑሀሚን አበበ ገልፃለች።

አብዛኛው የበዓሉ ታዳሚ ለቁልቢ ከተለያዩ አካባቢ ሲመጣ ወደ ድሬዳዋ በመምጣት ሰልባጅ ልብሶች፣ ጫማ፣ ብርድ ልብስ ምንጣፍና ሰሌን በብዛት የሚገዙ ሲሆን ከምግብ ደግሞ ጣፋጭ ምግቦች (ሀለዋ፣ ሙሸበክ፣ ባቅላባ…) እንዲሁም ድንች እና ፉል በብዛት ይመገባሉ። አብዛኛው ሰው በግለሰብ ደረጃ ነግዶ የሚያተርፍበት ሲሆን እንደከተማ ግን ቁልቢ ላይ ብዙ እንግዶች መምጣታቸውን ተከትሎ ከተማዋን ከማስዋብ አንፃር ምንም እንዳልተሰራ ለመታዘብ ችለናል።

የኮቪድ ስጋት

ከኮቪድ አንፃር ሊፈጠር የሚችለውን ስጋት ታሳቢ በማድረግ አዲስ ዘይቤ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዶክተር ዋዜማ ውቤን አነጋግራለች። መቀራረብ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አለማድረግ እንዲሁም ሰዎች የሚበዙባቸው ቦታዎች ዋነኛ የበሽታው ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው ክብረ በአሉን አስበው ለመዋል ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች ባለመዘናጋት የተለመደውን ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነው ሲል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

                    •ጎብኝ እና ገቢ የነጠፈባት ባህር ዳር

አስተያየት