“ዮንሴ ግሎባል የጤና ማዕከል” በ1.7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከ40 ሚልዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ለማከናወን ከጤና ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመው በያዝነው ወር መጀመርያ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡ ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል የሚተገበረው ፕሮጀክቱ ከኮሪያ ዓለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን የፕሮጀክቱ ዓላማ የተዋልዶ ጤና እና የፆታ እኩልነትን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረግ፣ የእናቶች ሞት ምጣኔን እንዲሁም ያልተመጠነ ቤተሰብን መቀነስ እንደሆነ ተቋሙ ለአዲስ ዘይቤ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርቷል።
የፕሮጀክቱ አተገባበር
ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል ያስቀመጣቸውን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማል። በዚህም የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮችን (ቴሌቪዥን፣ ሬድዮ፣ እና ጋዜጦች)፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን፣ የማኅበረሰብ መሪዎችን፣ የሀይማኖት አባቶችን፣ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ስለቤተሰብ ዕቅድ፣ ስለ ወንዶች የኮንዶም አጠቃቀም እና ስለ ዘመናዊ የሴቶች የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ያስተምራል።
ፕሮጀክቱ የተለያዩ በተዋልዶ ጤና እና የወሊድ መከላከያ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ በተጨማሪ ለጋዜጠኞች፣ ለጤና ባለሙያዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለማኅበረሰብ መሪዎች እና ለክልል የጤና ቢሮ ሠራተኞች ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተዋልዶ ጤና እና በቤተሰብ ዕቅድ እንዲሁም በወሊድ መከላከያ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ያካሄዳል።
ኮይካ እና ዮንሴ ማን ናቸው?
ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚያደርገው ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ ያደረገ፤ በኅብረተሰብ ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ኢንስቲትዩት ነው፡፡
ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በሚገኘው ዮንሴ ዩኒቨርሲቲ ዎንጁ ካምፓስ ውስጥ የተመሰረተና በዓለምአቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ኢንስቲትዩት ሲሆን ዓለምአቀፍ ድህነት እንዲቀንስ እና በዓለምአቀፍ የሕዝብ ጤና ላይ ከ2030 የልማት ግቦች ጋር በተገናዘበ መንገድ አስተዋፅኦ ማድረግን ዓላማው ያደረገ ተቋም ነው።
ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል በደቡብ ኮሪያ ከሚገኙና በሕዝብ ጤና ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ከሚሰሩ የመንግስት ተቋማት እና የትምህርት ክፍሎች እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ደግሞ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ለትርፍ ካልተቋቋሙ ድርጅቶች ጋር አብሮ የሚሰራ ተቋም ነው። ቀጣይነት ያለው የልማት ዕቅድ የገንዘብ ቋት (ፑል ፈንድ)፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ጥምር ፕሮግራም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብ ፈንድ፣ የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል በጋራ ትብብር ከሚሰራባቸው ተቋማት መካከል ተጠቃሾች ናቸው። በዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል ውስጥ የሚሰሩና ከአገር ውስጥ እንዲሁም ከዓለምአቀፍ አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች ዮንሴ የቆመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይሰራሉ።
ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ያቀረበው የኮሪያ ዓለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) መጋቢት 23 ቀን 1983 ዓ.ም. የተመሰረተና ከደቡብ ኮሪያ ለታዳጊ አገራት የሚደረጉ የተለያዩ መንግስታዊ ርዳታዎችንና የቴክኒክ ድጋፍ ፕሮግራሞችን ውጤታማነት ለማሳደግ ያለመ መንግሥታዊ ተቋም ነው።
የኮሪያ ዓለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ በአፍሪካ ትልቁ ስለመሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ተካቷል፡፡ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ኮይካ በኩል ደርግ ከወደቀበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2018 እ.ኤ.አ ድረስ ብቻ ከ170 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለይፋዊ የልማት ድጋፍ ፕሮግራም ወጪ ማድረጉን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት 2021 ለሁለትዮሽ ፕሮጀክቶች፣ ለባለብዙ ወገን የትብብር ፕሮጀክቶች እንዲሁም መንግስትና የግሉ ዘርፍ በጋራ ለሚያከናውኗቸው የትብብር ፕሮጀክቶች ከ18.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የልማት ድጋፍ በጀት ይዣለሁ ያለ ሲሆን፤ የዚህ ዓመቱ በጀት ከአምናው 2020 ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ጭማሪ አለው።
ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል ተግባራዊ እያደረገው የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት በ12 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር እየተተገበረ የሚገኘው ጥቅል ፕሮጀክት አካል ነው። የዚህ ፕሮጀክት ሌላኛው ክፍል በልማት ዕቅድ ፑል ፈንድ አማካኝነት በኦሮሚያ እና ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ስድስት ወረዳዎች እንዲሁም በጌዴኦ እና ጉጂ ዞኖች ውስጥ በመተግበር ላይ ነው። የዚሁ ፕሮጀክት ሌላኛው ክፍል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብ ፈንድ በተመደበለት 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት እየተተገበረ ይገኛል።
ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል ይህንን ፕሮጀክት እንደሚተገብር አካል ከልማት ዕቅድ ፑል ፈንድ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕዝብ ፈንድ ጋር በጋራ ይሰራል፤ ስራዎችንም ይቆጣጠራል። ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚሆነው ከኮይካ በተገኘ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በአዲስ አበባና ድሬዳዋ የከተማ አስተዳደሮች እና በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊያ፣ ትግራይ እንዲሁም የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ውስጥ የሚተገበር ነው።
ጥቂት ስለፕሮጀክቱ
የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ የስነ-ተዋልዶ ጤና እና የፆታ እኩልነትን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር፣ የእናቶችን ሞት ምጣኔ እንዲሁም ያልተመጠነ ቤተሰብን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡ አነስተኛ፣ ደስተኛ እና ውጤታማ የሆነ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ለመፍጠር ዮንሴ ዓለምአቀፍ የጤና ማዕከል ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከኮሪያ ዓለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ጋር በጋራ በመሆን “በኢትዮጵያ ውስጥ የተመጠነ፣ ደስተኛ እና ውጤታማ የሆነ ቤተሰብ ፕሮጀክት ክፍል ሁለት” ብለው በሰየሙት ፕሮጀክት አማካኝነት ሴቶች ስለ ስነ-ተዋልዶ ጤና እና የቤተሰብ ምጣኔ ያላቸውን ግንዛቤ እና መብት እንዲያጎለብቱ ለማስቻል ይሰራሉ።