ሐምሌ 21 ፣ 2013

ከ400 ዓመታት መለያየት በኋላ የተገናኙ ህዝቦች

City: Assosaማህበራዊ ጉዳዮች

በሀገራችን ለ400 ዓመታት ያህል ተለያይተው የቆዩት የጎንጋ እና የሺናሻ ህዝቦች 'የጎንጋ ሕዝቦች ሕዝብ ለሕዝብ ፎረም' በማለት በካፋ ዞን አዘጋጅነት በቦንጋ ከተማ በደማቅ ስነስርዓቶች በመታጀብ የተረሳሱት ወንድማማቾች መገናኘት ችለዋል፡፡

ከ400 ዓመታት መለያየት በኋላ የተገናኙ ህዝቦች

ታሪክ መመዝገብ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ እስካሁን ድረስ የሰው ልጆችን ካጋጠሙዋቸው ፈተናዎች ሁሉ በስፋት ወደር የለሹ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ቀውሶችን ተቋቁሞ መቆየት ነው፡፡

በእነዚህ ችግሮች መነሻም ብዙዎች በማንነታቸው ምክንያት በርካታ ተጽዕኖዎች ደርሶባቸዋል፡፡ ማንነታቸውንም እስከ መርሳት እንደደረሱ ይነገራል፡፡ ቋንቋቸው እና ባህላቸው በሌሎች ተጽዕኖ ሥር ውድቆ የቆዩትም በርካቶች ናቸው፡፡

ይህንንም መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያም የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር በርካታ እልህ አስጨራሽ ትግሎች አካሂዳለች፡፡ በዚህም በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በአሁኑ ሰዓት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን፣ ለመንከባከብና ለማበልፀግ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሕገ-መንግሥቱ ሙሉ እውቅና ሊሰጣቸውም ችሏል፡፡

በመሆኑም በሀገራችን ለ400 ዓመታት ያህል ተለያይተው የቆዩት የጎንጋ እና የሺናሻ ህዝቦች ዛሬ ጊዜው የሰጣቸውን እድል በመጠቀም የጎንጋ ሕዝቦች ሕዝብ ለሕዝብ ፎረም በማለት በካፋ ዞን አዘጋጅነት በቦንጋ ከተማ በደማቅ ስነስርዓቶች በመታጀብ ለ400 ዓመታት ተለያይተዉና ተረሳስተዉ ከነበሩት ከቤኒሻንጉሉ የሺናሻ ወንድሞቹ ጋር ተገናኝቷል፡፡

"የጎንጋ" ሕዝቦች በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የሚገኙ የካፋቾ እና የሻክቾ ብሔረሰብን እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ የቦሮ ሺናሻ ብሔረሰቦችን የሚጨምር ሲሆን ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ተጽዕኖዎች ሥር በመውደቅ ለ4 ምዕተ ዓመታት ያህል ተለያይተው ለመኖር እንደተገደዱ ይነገራል፡፡

የጎንጋ ሕዝቦች ታሪካዊ ግንኙነትና ትስስር ያላቸው ሲሆን በታሪካዊ አመጣጥ፣ በባህል፣ በቋንቋና በጂኦግራፊያዊ አሰፋፈር እና በሌሎችም ነገሮች ህብር ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡

ታሪካዊ መረጃዎች እንደሚገልፁት ከሆነ ከዓባይ ወንዝ በሰሜንና በአብዛኛው በደቡብ እስከ ስምጥ ሸለቆ ባለው ሰፊ ምድር የጎንጋ ሕዝቦች ሰፍረዉ እንደነበር አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊያን ይገልፃሉ፡፡ እንደ የታሪክ ጸሐፊያኑ አገላለጽ የጎንጋ ሕዝቦች የሚባሉት በዋናነት የዛሬዎቹን የካፋ፣ የሸካና የቦሮ ሺናሻ ሕዝቦችን የሚያካትት ሲሆን "ጎንጋ" የሚለው ጥሬ ቃል ከአንድ ጥንታዊ የጎንጋ አባት ስም ስያሜ እንደመጣና የእነዚህም የመጀመሪያ የጎንጋ አባት ስማቸው "ሐማቲ" ይባሉ እንደበረ እነዚህ የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ "ሐማቲ" የሚለውን መጠርያ የሽናሻ ብሔረሰብ አባት መጠሪያ ስያሜ ሲሆን ለብዙ ዘመናትም ይህንን ስያሜ ሲጠቀሙበት እንደነበር እነዚህ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ የተለያዩ መጽሐፍት እንደሚያስረዱት የጎንጋ ህዝቦች ቋንቋ በዓባይ ወንዝ ወዲህና ወዲያ ማዶ ማለትም በደቡብና በሰሜን እስከ ካፋ (Keffa) ድረስ ሲነገር እንደነበረ በመጥቀስ በአጠቃላይ ጎንጋ የሚለው ስያሜ ወይም መጠርያ የሚወክለው በደቡብ ምዕራብ አካባቢ የሚኖሩትን የአሁኖቹን የካፋ፣ የሻካ፣ የቦሻ እና አናሮ እንዲሁም አንፊሎ በምዕራብ ወለጋና ሽናሻ በዓባይ ሰሜናዊና ደቡባዊ ክፍል የሚኖሩትንም የሚጨምር ነው፡፡

ሐማቲ ወይንም የጎንጋ ህዝቦች አባት አራት ልጆች የነበራቸው ሲሆን እነርሱም ጎንጋ፣ ዝገት፣ ዱራና ጉማ ይባሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ጎንጋ ማለት ከሽናሻ የዘር ግንዶች መካከል አንዱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህም በአባታቸው ሐማቲ መሪነት ከምድረ ከነዓን ተነስተው ወደ ግብጽ ሲገቡ የግብጽን ጥበብ ተምረው ባገኙት እውቀትና ብልሃት ግብጾችን በተለይ በመድኃኒት ቅመማ ሙያ ሲፈታተኗቸው ግብጾች ጠብ በማንሳታቸው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት አራቱ ልጆች በየነገዳቸው በየሰፈሩበት ቦታ ለመጠራት ችለዋል ይላሉ መዛግብቶቹ፡፡

ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ የተሻገሩት እነዚህ "የጎንጋ" ሕዝቦች የቀይ ባህርና ጥቁር ዓባይ ወንዝን በመሻገር የዓባይን ወንዝ በመከተል ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን በወቅቱ የአማራና የኦሮሞ ብሔረሰቦች መኖሪያ ወደ ነበረው የሸዋ ምድር ላይ ለመስፈር ቻሉ፡፡ ሸዋ ውስጥም ለረጅም ዓመታት ከኖሩ በኋላ በመሬት ጥበት ምክንያት እና በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩት ሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ግጭት በመቀስቀሱ ምክንያት በሦስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወይንም አቅጣጫዎች  ለመሰራጨት እንደቻሉ ጽሁፎች ያሳያሉ። 

ከዚህም የመጀመሪያዎቹ ከሸዋ ተነስተው ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አድርገው በዛሬው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ወደሚገኙ የካፋና የሸካ ዞኖች የሰፈሩ ሲሆን ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ከሸዋ ተነስባይን አቋርጠው በወለጋና ምስራቅ ጅማ አካባቢ ሰፍረዋል፡፡

ሦስተኛው ቡድን ደግሞ ዓባይን ተሻግሮ ጎጃም ውስጥ ቡሬዳሞት ወረዳ ሺንዲ በሚባል ቦታ እስከ ጉግሣን እንዲሁም በወንበራ፣ በቡለን፣ በድባጢ፣ በዳንጉርና ጉባ ወረዳዎች ላይ ለመስፈር ችለዋል፡፡

የጎንጋ ሕዝቦች በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ በራሳቸው መንግሥት ሲተዳደሩ የኖሩ ቢሆንም በተቃራኒው ለሕዝቦች አንድነትና ትብብር ምቹ ሁኔታ በማይፈጥሩ በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ ሥርዓቶች ምክንያት በጨቋኝ ሥርዓት ጫና ውስጥ በመውደቅ ማንነታቸውን ደብቀው ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያዳብሩ ተደርገው ቆይተዋል ይላሉ እነዚህ መዛግብት፡፡

በመሆኑም እነዚህ መንግሥታት ከተወገዱ እና ዘመናዊ ትምህርት በሃገሪቷ ከተስፋፋ በኋላ የእነዚህ ከ"ጎንጋ" ሕዝቦች አብራክ የወጡ ተማሪዎች የራሳቸውን ባህልና ታሪክ እያነበቡ እና የታሪክ ድርሳናትን እያገላበጡ በየሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚፈጥሯቸው ግንኙነቶች አማካይነት የዘር ሀረጎቻቸውንና ለበርካታ ዘመናት የተለያዩትን የዘር ግንዶቻቸውን ለማግኘት እንደቻሉ ይነገራል። በመሰረቱ ይህ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን አማካይነት የመፈላለጉ ጉዳይ የተጀመረው ከ197ዐዎቹ ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን በዚህ መነሻነት በ1983 ዓ.ም. የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም የባህል ፖሊሲ ሕዝቦች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማጥናት፣ ማልማትና መጠቀም እንደሚችሉ ዋስትና ከሰጠ በኋላ እነዚህ ሲፈላለጉ የነበሩ ሕዝቦች አዲስ አበባ ላይ ከተደረገው ግንኙነት በተጨማሪ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ከ4 በላይ ትላልቅ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ፎረሞችን ለማካሄድ ችለዋል፡፡

በዚሁም መሰረት በመጀመሪያ የጎንጋ ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ፎረም በካፋ ዞን በቦንጋ ከተማ፣ በመተከል ዞን በቡለን ወረዳ፣ በሻካ ዞን ማሻ ከተማ እንዲሁም ለ4ኛ ጊዜ ደግሞ በቦንጋ ከተማ እና በተለያዮ ከተሞች ላይ ፎረሞቹን በማጠናከር ለመገናኘት ችለዋል።

ይህ ፎረም ወይንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሂደቱ ከታሪክ አልፎ ማኅበራዊ ትስስሮችን ከመፍጠሩና ከማጠናከሩ በተጨማሪ በእነዚህ ክልሎች መካከል መልካም የኢኮኖሚ እና የልማት ትስስር እንዲኖር ስለሚያደርግ ፎረም ከምንግዜውም በበለጠ ሲቀጥል ኑሯል።

ከዚህም አልፎ ተተኪው ትውልድ የራሱን የታሪክ መነሻዉንና ማንነቱን እንዲያውቀው ከማድረጉም በላይ ዘመኑ ያጎናፀፋቸውን መብቶች በመጠቀም በሀገሪቱ የልማት ጉዞ ላይ አንድነታዊ ትስስር ለማስፈን አመቺ ሁነታዎችን ስለሚፈጥር ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥም ትልቅ ድርሻ ስለሚኖረው ከምንጊዜውም በበለጠ መጠናከር አንዳለበት ብዙዎች ያሳስባሉ።

አስተያየት