የወጣቶች ስራ አጥነት እየፈተነኝ ነው ሲል ያስቀመጠው የ2009 ዓ.ም. ፖለቲካዊ ግምገማ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ መጠኑ ከሌሎች የበጀት መደቦች ላቅ ያለውን 10 ቢሊዮን ብር መደበ፡፡ ኢትዮጵያ ለወጣቶች ብቻ የተመደበ ፈንድ አዘጋጅታ እርሱን የሚያስተዳድር ተቋም የመሰረተችው ከአምሰት ዓመታት በፊት ነው፡፡ የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተለው መንግስታዊ ተቋም ኢንዱስትሪዎችን እና አነስተኛ ድርጅቶችን ለመደገፍ ከተመሰረቱ አቻ መስሪያ ቤቶች ጋር ጥምረት ፈጥሮ በጥቃቅን እና አነሰተኛ፣ የከተማ እና የገጠር ወጣቶች የእድገት ፓኬጅ የወጣቶች ድጋፍ ፈንዶችን ሲመራ ቆይቷል፡፡
ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ የማምረት አቅም ተጠቅመው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን እንዲችሉ እና ተደራጅተው ለሚያካሂዱት የገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት በ10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲቋቋም መወሰኑ ይታወቃል፡፡
ውሳኔው ድንገት ሰበር ዜና ሁኖ የተገለፀው ከቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ለተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶችን የ2009 ዓ.ም. የስራ ማስጀመሪያ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር መንግስት የወጣቶች የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን አሳውቀው ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅን ተወያይቶ አፅድቋል፡፡
ሃገር በፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ በምትታመስበት የ2008 መገባደጃ የ2009 መባቻ ወቅት በመንግስት ላይ ሰፊ ቅሬታ ያደረበት የነበረውን ወጣት ጥያቄ ለመመለስ እና ቅሬታውን ለመፍታት ወጣት የመንግስት ግምገማ የወጣቶች ቀዳሚና መሰረታዊ ፍላጎት የስራ እድል ጥያቄ መሆኑን በማመን የተወሰነ እንደነበር የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በምክር ቤቶቹ ያስሙት ንግግር ይታወሳል። መንግስት በተለይ ወጣቱ የሰራ አጥነት ችግር እንዳለበት፣ በዚህ ምክንያት ያደረበት ቅሬታና ወደተቃውሞ መሸጋገሩም ተገቢ መሆኑን ተቀብሎ ችግሩን ለመፍታት አቅዶ መነሳቱን ያሳየበት ነበር። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዓመቱ የስራ መክፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር ይህን በይፋ አሳውቀዋል።
የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በህዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የ2009 ዓ.ም የመንግስት የስራ ክንውን የሚገልጽ እና የመክፈቻ ንግግር፣ ሐገሪቱን የወጠራት የስራ አጥነት ፈተና መፍትሄ እንደያዙ የሚያመላክት ነው፡፡
ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና ተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአፈፃፀም ብቃት መጓደልና በስነ ምግባር ጉድለቶች ሲደነቃቀፉ የወጣቱ ትውልድ ቅሬታ እንደሚባባስ ታይቷል። በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በመሰረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች የራሱን የወጣቱን ትውልድ በቀጥታና በዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጥ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በምክር ቤቶቹ የስራ ዓመት መጀመሪያ የጋራ ስብሰባ ላይ የወጣቶችን ጥያቄ መፍታት የወቅቱ የፖለቲካው መሰረታዊ መነሻ ብለውታል።
የሃገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት እድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል። ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን የግድ ይላል ብለዋል፡፡
በዚህ ፈንድ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ከ18 እስከ 34 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ሲሆኑ፤ ወጣቶቹ በጥቃቀን ኢንተርፕራይዝ ስር መደራጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፈንዱ የተዘዋዋሪ ፈንድ ስርዓትን መሠረት በማድረግ ለተጠቃሚ ወጣቶች በብድር የሚተላለፍ ሲሆን፤ ከፈንዱ ብድር ለማግኘት የንብረት ዋስትና ማቅረብ ሳያስፈልግ እርስ በእርስ ዋስ በመሆን መበደር እና ገንዘቡን ለተፈለገው ዓላማ ማዋል እንደሚገባ አዋጁ አስቀምጧል፡፡
ስራ አጥነትን በመፍታት ረገድ መሬት አልባ የሆነው በገጠር የሚገኝ 1.7 ሚሊዮን በላይ ወጣት ስራ አጥ እና በከተማ በተለያዩ ትምህርት ደረጃዎች አልፎ ቤቱ የተቀመጠውን 1.5 ሚሊየን ወጣቶች በጥቅሉ ከሶስት ሚልየን በላይ ወጣቶች የዚህ ፈንድ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እቅድ ተይዞ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው የወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ችግር ለመፍታት የታቀደውን ተግባርም እንዳለ አንስተዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህን አስመልክተውም፤-
ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት እድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል። ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን የግድ ይላል። በዚህ መሰረት፣ መንግስት በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል፡፡ ለዚህም ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ አሥር ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። ነበር ያሉት፤
ከፈንዱ ብድር የሚጠይቁ ወጣቶች በክልል ወይም የከተማ አስተዳደር (እስከ ወረዳ) የወጣቶች ጉዳይ በሚመለከተው አካል ድጋፍ ያገኙ የገቢ ማመንጫ የንግድ ስራ ፕሮጀክቶች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፈንዱን በፌዴራል መንግስት ስም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያስተዳድረው ሲሆን፤ ለወጣቶች ብድር ማቅረብ የሚችሉት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው ፡፡
አነስተኛ የፋይናስ ተቋማት በሌሉባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድሩን የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያው አዋጅ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን በመንግስት ስም ያስተዳድር ዘንድ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊነቱን ሰጥቶታል፡፡ ሆኖም ብድሩን የማቅረቡን ስራ የሚያከናውኑት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ የአዋጁ መግለጫ ለዚህ የሰጠው ምክንያት “በዚህ ፈንድ ተጠቃሚ የሚሆኑ ድርጅቶች በጥቃቅን የሚፈረጁ በመሆናቸውና ለእነዚህ ዓይነቶቹ ድርጅቶች ብድር ማቅረብ የሚችሉት ደግሞ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ስለሆኑ” የሚል ነው፡፡
እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት በሌሉባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እነርሱን ተክቶ ይሰራል፡፡
በፈንዱ የተቀመጠውን 10 ቢሊዮን ብር የየክልሉን የወጣቶች ብዛት መሰረት በማድረግ የመደልደል ስልጣን በአዋጁ የተሰጠው ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ ለክልሎች የተከፋፈለውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቀብሎ ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የማስተላለፍ ሚና የተሰጠው ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋምነት የተመዘገቡ 33 ድርጅቶች አሉ፡፡ ተቋማቱ ለደንበኞቻቸው የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ፡፡
የወጣቶች ተቃራኒ አስተያየቶች ስለፈንዱ
ፀሐይ የሱፍ የተባለ ወጣት ፈንዱ በደቡብ ክልል የዞን መዋቅርን ያላካተተ መሆኑ ዘርፉን በብቃትና በጥረት ለመወጣት ተግዳሮት ነበር ሲል ይገልፃል፡፡
ግርማ ዘለቀ በበኩሉ ከተማ ግብርናን፣ አርሶአደርን አላከተተም፤ ሴፍትኔት በሚል ስም ተረጅ የሆኑ አካላትን ወደስራ እንዲቀየሩ እድል እንዲፈጥር ብንጠብቅም አሁንም በአፈፃፀም ችግር ተጠቃሚነታችንን አላረጋገጠም ይላል፡፡
በተለይ በአማራ ክልል ከዘርፉ ተጠቃሚ ነበሩ የተባሉ እነደስታ መንግስቱን የመሰሉ ወጣቶች በርካታ ችግሮችን ይዘረዝራሉ፡፡
“ከምንም በላይ በቢሮክራሲ የታጠረ የአማራ ክልል ብድርና ቁጠባ ተቋም አሰራር ቶሎ ሂደቱ አጠናቆ ለኛ ለማስተላፍ ችግር ነበር፡፡ በጣም በተራዘመ አድካሚ አሰራር እና መዘግየት አሰልችቷቸው የተውት እንደነበሩ ትናገራለች”።
ሌላው አሰተያየት ሰጭ ወጣት ሳለአምላክ ብርሃኑ የሚያበድሩበት ዋጋ ወለድ ከህግ ባፈነገጠ መልኩ በተቋማቱ ደረጃ እንጅ ለዚህ አላማ ተብሎ በተተመነው የወለድ መጠን አልነበረም ሲል ይናገራል፡፡ የሚሰጡንም ገንዘብ መጠንም በጣም አነስተኛ ነው፡፤ ይሄ ችግር አለባቸው” ሲሉ የተፈጠረውን የአተገባባር ችግር ይናገራል፡፡
በተቃራኒው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ፍሬ አፍርቷል ሲሉ ማሳያዎችን የሚያቀርቡ በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ተጠቃሚ በመሆን ዉጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ሲሉ የሚከራከሩ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አመራሮችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዚህም በወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ተጠቅመዉ ዉጤታማ ከሆኑ ኢንተርፕራይዞች መካከል በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር የሚገኘዉ፤ ባዩ እስራኤልና ጓደኞቻቸዉ የወተት ልማት ኢንተርፕራይዝ አንዱ ነዉ፡፡
የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ባዩ፤ በእንስሳት ሳይንስ ተመርቆ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጣሪ ነበር፡፡ መንግስት የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ለወጣቶች ሲመድብ የመንግስት ስራ በመልቀቅ ተመርቀዉ ስራ ያልነበራቸዉ ጓደኞቹን በማሰባሰብ የኢንተርፕራይዙን እንዲመሰረት ማድረጉን ይናገራል፡፡
የኢንተርፕራይዙ ሰብሳቢ ወጣት ባዩ እንደሚናገረዉ ከተዘዋዋሪ ፈንድ 360 ሺህ ብር ከተለቀቀላቸዉ በኋላ በፍጥነት ወደ ስራ በመግባት አሁን ላይ ስራቸዉን በጥሩ ሁኔታ እየከወኑ ይገኛሉ፡፡ እጅግ ዉጤታማ ከመሆናቸዉ የተነሳ የተበደሩትን ብድር በአግባቡ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ በአሁን ወቅት ኢንተርፕራይዙ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ተመላሽ አድርጓል፡፡
በተመሳሳይ ሻለቃ ሰላምና ጓደኞቻቸዉ የብሎኬት ማምረቻ ማህበር፤ በዚሁ ሸዋሮቢት ከተማ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ተጠቅመዉ የስራ እድል ተጠቃሚ ወጣቶች ያቋቋሙት ኢንተርፕራይዝ ነዉ፡፡ ይህ ኢንተርፕራይዝ 60 ሺህ ብር ቅድመ ቁጠባ በማድረግ ከተዘዋዋሪ ፈንድ 560 ሺህ ብር በመዉሰድ በድምሩ በ 6 መቶ ሺህ ብር ወደ ስራ ገብተዋል፡፡
መንግስት ባደረገላቸዉ የማምረቻ ሼድ፣ የመብራት፣ ዉሃ እና የመሳሰሉ ድጋፎች ታግዘዉ የብሎኬት ምርት በማምረት ለከተማ ነዋሪዉ በመሸጥ ላይ ናቸዉ፡፡ በዚህም ብድሩ ከወሰዱ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ምንም ሳይቆራረጥ እዳቸዉን እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ኢንተርፕራይዝ ከአስራ አምስት በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠርም ችለዋል፡፡
የፈንዱ እንከኖች
የፌዴራል መንግስት እስካሁን ወደ 8 ነጥብ 4 ቢልየን ብር የሚጠጋ ብድር ለተጠቃሚዎች በክልሎችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አስፈፃሚነት ቢያቀርብም መመለስ የነበረበት ብድር እስካሁን አልተመለሰም፡፡ በዚህም ለኦሮምያ 3 ነጥብ 4 ቢልየን ብር፣ አማራ 2 ነጥብ 6 ቢልየን ብር፣ ደቡብ 1 ነጥብ ስምንት ቢልየን ብር ክልሎች የብድሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሰነዶች ዝርዝር መረጃ ያሳያል፡፡ አዲስ አበባ 418 ሚልየን ብር እና ድሬዳዋ 43 ነጥብ 9 ሚልየን ብር ከፌድራል መንግስት ወስደዋል፡፡
ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ተብሎ በ2009 ዓ.ም የተመደበውን የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲያስተዳድር በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕጋዊ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱና በዚህም ምክንያት ፈንዱ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ በኦዲት ማረጋገጥ ባለመቻሉ፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የባንኩ አመራሮች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አመለከተ።
ለአዲስ ዘይቤ በደረሰው ሰነድ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 995/2009 አንቀጽ 9/1 እና 2 መሠረት ተዘዋዋሪ ፈንዱን በየክልሎቹ የሚገኙ ወጣቶችን ቁጥር በማገናዘብ በአነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት በኩል እንዲተላለፍ ማድረግ ሲገባው፣ ኦዲቱ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ የተመደበውን ከ9.1 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያስተላለፈው በአዋጁ ከተገለጸው ውጪ ውክልና በተሰጣቸው በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮዎች በኩል መሆኑን ያብራራል።
ከደደቢት ማይክሮ ፊይናንስ ኩሓ ቅርንጫፍ ማይ አንበሳ ንዑስ ቅርንጫፍ በተዘዋዋሪ ፈንድ ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍትሔ ለመጠየቅ ለደደቢት ማይክሮ ፊይናንስ ዋና መ/ቤት ለኦፕሬሽን ክፍል በቀን 31/08/2018 በተፃፈ ደብዳቤ ቁጥር DC/MAS/Q/1539/2018 ከተላከው ሰነድ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፡-
• ማህበራት ከፈንዱ የወሰዱትን ብድር ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣
• የማህበራቱ አባላት አንድ በአንድ ከማህበሩ እንደወጡ ወይም እንደተሰናበቱ የሚያሳይ ደብዳቤ እያመጡ መሆናቸው፣
• በክሬቸር ምርት ተደራጅተው ብድር የወሰዱ ማህበራት ውል እንዲዋዋሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢጠየቁም ፌቃደኛ አለመሆናቸው፡፡
ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም አ/ማ በኩል ከተገኘ የሰነድ ማስረጃ በተዘዋዋሪ ፈንድ ዙሪያ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች በተመለከተ በተለይም ተጠቃሚዎች ለብድሩ ብቻ ተብለው ከሌላ አካባቢ መጥተው መደራጀትና ብድሩን ከወሰደ በኋላ አካባቢውን ለቀው ይጠፋሉ፡፡ ብድር የሚወስዱ ወጣቶች በአግባቡ ስልጠና የማይሰጣቸው ወይም የማይወስዱ መሆኑ፤ ብድር የሚወስዱ ወጣቶች በተዘጋጀው የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ላይ ጥሩ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ እና በአግባቡ ስራ ላይ መዋል የማይችሉ መሆናቸው በአማራ ክልል ተመላክቷል፡፡
አንዳንድ የኦሮምያ አካባቢዎች የተቋሙ ሰራተኞች የብድር ክትትልና ብድር የማስመለስ ስራ በሚሰሩበት ወቅት ማስፈራራት እና ዛቻ መኖሩን ገልፀዋል። በተመሳሳይም ብድሩን የወሰዱ ወጣቶች (ማህበራት) ለመክፈል ፍላጎት ቢኖራቸውም ሌሎች ብድሩን ለመክፈል ፍላጎት በሌላቸው ወጣቶች ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ለአዲስ ዘይቤ የደረሰው ከኦሮምያ ክልል የተገኘው በፌደራል የተጠቃለለ ሪፖርት ያሳያል፡፡
በሃረሪ ሕዝብ ክልል መንግስት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽ/ቤት በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በከተማ ዙሪያ ወረዳዎችን ያቀረቧቸው ችግሮች ለፈንዱ ውጤታማነት ተግዳሮት ነው ያሉት “የሚሰጠው ብድር ለስራው የሚያስፈልገውን ዕቃ ከመግዛት ይልቅ በካሽ እንዲሰጣቸው መፈለጋቸው፣ ተደራጅተው ብድር የወሰዱ ማህበራት ባለመግባባት ምክንያት እና ብሩ ተካፍለው የሚበተኑ መሆናቸው፣ ብድር የወሰዱ ወጣቶች ገንዘቡ ወደአካውንታቸው ቢገባላቸውም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ስራ ሳይገቡ በመቅረታቸው ለወለድ እዳ እየተዳረጉ መሆናቸው” ተዘርዝሯል፡፡
በተለይም የገበያ ችግር የስራ ፈጣሪዎች ፈተና እንደነበሩ ትብለጥ ጌታቸው እና ኤልያስ ቢያድግልኝ ተናግረዋል፡፡ አሰተማማኝ የሆነ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ ያመረቱትን ምርት የሚገዛቸው ማጣት በገበያ ለመቆየት እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡
ታደለ አዳነ የመብራት ችግር ባለመቀረፉ ሊሰሩ ያሰቡትን የጠጠር ማምረት ስራ ሊያከናውኑ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ እያያው ሞላልኝ በበኩሉ የሼድ አቅርቦት፣ በዳቦ ዱቄት እጥረት የተመጋጋቢ የገበያ ሰንሰለት ባለመኖሩ ስራ አለመጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ ደምስ ዝጋለ በበኩሉ የግብዓት እጥረት ስራ እንዳንሰራ ምክንያት ሆኖናል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አስታውቀዋል፡፡
ብድር ወስደው በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በሼድ /በመስሪያ ቦታ/፣ በግብአት እጥረት እና በማሽነሪ አቅርቦት ችግር ለበርካታ ወራት ስራ ያልጀመሩ ኢንተርፕራይዞች
በገበያ ትስስር ችግር ምክንያት ውጤታማ ያልሆኑ ኢንተርፕራይዞች / ለማሳያነት 16 ኢንተርፕራይዞች/
በዚህ ተግባራዊ በሆነው ፈንድ ወጣቶችን የግድ ተደራጁ ማለቱ ገዳቢ ነው ሲሉ የህግ ባለሙያው አቶ ገብረሚካኤል ተስፋሁን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ከወጣቶች ፈንድ መበደር መፍቀድንም እንደአማራጭ መቀመጥ እንደነበረበት ባለሙያው የአዋጁን ክፍተት፣ ለግለሰቦች፣ የግል ኩባንያዎች፣ የህብረት ስራ ማህበራት እና ቡድኖች በወጣቶች እስከተቋቋሙ ድረስ ከፈንዱ ለመበደር ገዳቢ መሆኑ ለውጤታማነቱ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ፈንድ በስራ ጥረት ውስጥ ያሉ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች እና አዟሪዎች ጭምር ከገንዘቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ የባከነ ጅምር እንደነበር ማየት በቂ ነው ሲሉ አቶ ገብረሚካኤል ያጠቃልላሉ፡፡
ፈንዱ የመጣበት አግባብ ነው ስኬታማነቱን የቀማው ሲሉ አሰተያየቱን ያካፈለን ወጣት ስለዓባት ፈንቴ “ፈንዱ የፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃ፣ የወጣቱን ጩህት ማስወገጃ፣ የመንግስትን ተጠያቂነት ማስረሻ ነበር እንጂ በትክክል ማጣት ያሰራቸውን እጆች ከአዕምሮ እስከ ሙያ ነፃነት ሚሆናቸው አልነበረም” ይላል፡፡
ነገር ግን በፈንዱ የነበሩ መልካም ቱርፋቶች ተብሎ ከሚወሳው ውስጥ ፈንዱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች በሚል ከሚጠቅሳቸው ውስጥ በኢትዮጵያ ብድር ለማግኘት የማይቻልባቸው የነበሩት የኮሚዩኒኬሽን፣ የፊልም፣ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፎች እና ኢንፎርሜሽንን ያቀፈ ነበር፡፡