ቀደምት ከሆኑት ጥንታዊ ባለታሪክ የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው ባገኘነው የከተማው አሃዛዊ መረጃ መሰረት ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ይዛለች፡፡ የቆዳ ስፋቷ በማደግ ሂደት ውስጥ አሁናዊ መሰረቷ 5,600 ሄክታር ነው። ነዋሪዎቿ እና ጎብኚዎቿ “ኢትዮጵያዊቷ ፓሪስ” ብለውም ይጠሯታል። ዶላር እንደቀላል ከሚታይባቸው ብቸኛ የሰሜን ከተሞች መሃከል ናት፡፡ የሐገራችን የመጎብኘት ፀጋ እና ከ250 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ከተሞችን ታሪክ አቅፋ ይዛለች፡፡ ጎንደር የሕዝብ ቁጥሯ በፈጣን ሁኔታ እየጨመረ ከመጡ ከተሞች አንዷ ናት። የሀገር ውስጥ መረጃ ብቻ ሳይሆን የዓለም ባንክ የ2018 መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች ውስጥ በሕዝብ ቁጥር ብዛት ሁለተኛ ነች። የሕዝብ ቁጥሯ የጨመረው በተለያየ ምክንያት ሲሆን አንዱ ከውልደት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገርላታል።
በመቶ ኪሎ ሜትር ውስጥ ሦስት በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉባት ከተማ ናት። ከእነዚህ መካከልም ቀዳሚው የፋሲል ግንብ አብያተ መንግሥታት ሲሆን ቀጣዩ የሰሜን ተራራ ብሄራዊ ፓርክ፣ እና ሦስተኛው የእንስሳትና ዕፅዋት ብዝኃነትን የተመለከተው ነው። ከሦስቱ ባሻገርም ባህል፣ ታሪክና ሐይማኖታዊ ትውፊት ጎልቶ የሚወጣባት የንጋት ጀምበር ከተማ ነች።
በኢትዮጵያ የምህንድስና ታሪክ ውስጥ ከአንድ ድንጋይ ብዙ ህንፃዎችን ፈልፍሎ የመቅረጽ የረቀቀ ጥበብ ልህቀት የታየባትና ተፈጥሮ የዚሁ ታሪክ መዳረሻ እንድትሆን ያደለቻት ውብና የማትጠገብ ከተማ ናት። በአብዛኛው የታሪኳ መነሻ የሚያደርገው ከ1632 ከአፄ ፋሲል ንግሥና በኋላ ያለው ነው። 400 ዓመት እየተባለ የሚጠራውም ወቅት ከአፄ ፋሲል ንግሥና በኋላ ያለው ዘመን ነው። የ44 ታቦታት መገኛ እንደመሆኗ የሚማልበት የነዋሪው የእምነት ምህላ 44ቱን ታቦታትን ጠርቶ ነው። መሃል ሐገር ለማግኝት የሚከብዱ አለምዓቀፍ ተወዳዳሪ ሆቴሎች እና የውጭ ምንዛሬ ትስስሮሹ ብዙ ነው፡፡ የዶላር ሪሚታንስ፣ የቀጥታ የሰሊጥ እና የጥጥ ምርቶች የውጭ ሃገር ሽያጭ እንጂ ጎንደር ቀይና ጥቁር ወርቅ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ሰሊጥ ዓይነትም መገኛና፣ ከቱሪዝሙ ጋር ተዳምሮ ዶላርን ከኢትዮጵያ መገበያያ ቀጥሎ አርሶ አደሩ ሳይቀር የሚገበያይበት ነው፡፡
የቀድሞው የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ “ግንኙነቷ እንደ ሀገር ሲቃኝ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚያገናኛት የመሰረተ ልማት ያላት ከተማ ናት። ይህም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩሳት መለኪያ እና ከሚወሰድባቸው ከተሞች አንዷ ለመሆኗ ማሳያው ብዙ ነው፡፡” ይላሉ፡፡
የመሬት ግብይት በዶላር …
የጎንደርን መሬት ስናስብ በኢትዮጵያ የከተሞች እድገት ታሪክ ያላትን ድርሻ መዘከር ግድ ይላል፡፡ በሐገራችን በከፍተኛ ሁኔታ የኢንቨስትመንት ጥያቄ ከሚቀርብላቸው ከተሞች መካከል አንዷ ናት፡፡ ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና የኗሪውን የቤት መስራትም ሆነ የኢንቨሰትመንት ጥያቄ ለመመለስ የከበዳት ከተማ ናት፡፡
‹‹እዚህ መሬት በዶላር ነው፡፡›› ያለኝ ጎንደር ተወልዶ ያደገው ወጣት ዓለማየሁ አያናው ‹‹ሊዝ በሚባል የመንግሥት ኪስ ማደለቢያ ስርዓት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያለን ኗሪዎቿን ማስተናገድ አልቻለችም›› ሲል ይወቅሳል፡፡
‹‹አንድ ክላሽ ይዘህ ካልሆነ ቤትህ ሰርተህ አትኖርበትም፡፡›› ያለው ሌላው ኗሪ ዘላለም በለጠ በሽዎች የሚቆጠሩ ቤቶች እና በርካታ የጎንደር ዙሪያ መንደሮች የተመሰረቱት በሕገ ወጥ መንገድ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕጋዊውን ስርዓት ማለፍ ከባድ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ እየተደራጀ መሳሪያ እየገዛ ከአርሶ አደሩ ጋር እየተረዳዳ መሬት እየተቀበለ የጎንደርን ዙሪያ ከከተማ አሰተዳደሩ ድንበር ተከትሎ ለመስፈር ተገዷል፡፡›› ይላል፡፡
አሁን ጎንደር በ2 የተከፈለች ናት የመሃል ከተማዋ ጎንደር መሬት በዶላር የምትገበያይባት ናት፡፡ ሁለተኛዋ ጎንደር ከተማ በኢኮኖሚ አነስ ያለው ነዋሪ ጥሏት ወጥቶ በአርሶ አደር ማሳ በመስፈር ሌላ ከተማ የመሰረተባት መሃሏን ለመንግሥት እና ለ‹ባለዶላሮች› ሰጥቶ ከአርሶአደሩ መንደር የተገኘ ከተሜ የሚኖርባት ናት፡፡
የሊዝ መወደድ እና የከተማ መሬት ጡዘት በእርግጥ ገበሬውን መሬቱን እንዲሸጥ እያስገደደው እና ከእርሻ ወደከተማ ኗሪነት ያለምንም ቅድመ ዝግጅት እንዲቀየር አስገድዶታል፡፡ በዚህም የጎንደር ከተማ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የፍትሕ ጥያቄዎች ከመሬት ጋር የተያያዙ እንደሆነ የጎንደር ከተማ አሰተዳደር የቀድሞው ከንቲባ ዶ/ር ሙሉቀን ያብራራሉ፡፡
የነዋሪዎች አሰተያየት
‹‹መልማቱ ጥሩ ነው ከቦታው የሚፈናቀለው አርሶ አደር ግን የሚጠቅም ነገር ማግኘት አለበት፣ የባለሀብት ዘበኛ አርገው ማስቀረታቸው እንጅ ክፋቱ›› የሚለው የጎንደር ዙሪያ ኗሪው አበባው ታከለ በሊዝ አዋጁ ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት መሬት ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶውን ለመኖሪያ ቤት መስሪያ አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸውም ያስገድዳል፤ ይህም የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይረዳል ቢባልም በጎንደር ግን እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም ይላል።
ድሃን ታሳቢ ያላደረገ አዋጅ ነው፡፡ ይህንን አዋጅ የህዝብ ጆሮና ዐይን የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ ያደርገዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡
ያዕቆብ ክንፉ እንደሚለው ‹‹የመሬት ከበርቴ ድሮ የት አለ አሁን ብሶበታልና አንዱ ስግብግብ ባለሀብት አምስት ስድስት ቦታ ሲኖረው አንዱ ድሀ መሸሸጊያ ጥላ ቦታ የለውም ኡኡኡኡኡኡ መንግሥት ካለ ጣልቃ ይግባ ካልሆነ ይግባኝ፡፡›› ሲል በጎንደር ያለውን የመሬት ሁኔታ ይገልፃል፡፡ እኔን የሚገርመኝ የሚለው አቶ ገላነህ ሰላሙ እስካሁን ከ10 ዙር በላይ ሰነድ ለሽያጭ ቀርቧል ነገር ግን መንግሥት ሠራተኛውም ሆነ ድሃው ሕብረተሰብ ከጨረታ ዋጋ ንረት /ከበርቴዎች ዋጋ በመስቀላቸው/ ምክንያት ቦታ ማግኘት አልቻለም በየዙሩ ከ5 እስከ 10 ቦታ የሚያገኙ ብር ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው እስከ 70 ቦታ አንድ ሰው መያዝ ይችላል ደሀው ሕብረተሰብ ምን ይሁን ማን ያስብለት? ሲል የሕጉን አፈፃፀም ከጎንደር ተሞክሮ የሊዝን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡
ንገረኝ ካልከኝ የሚለው አቶ ላቀው ወንድምአገኝ ‹‹የሊዝ አዋጅ የዜጎችን ተጠቃሚነት ሳይሆን የመንግሥን ተጠቃሚነት ነው የሚያረጋግጠው፡፡ አስገባሪ ስርአት ነው ዜጎች በአገራቸው እንደዜጋ በነፃ መሬት የመጠቀም መብታቸውን የነጠቀ አዋጅ ነው፡፡ መንግሥት ሊያስብበት ይገባል፡፡›› ሲል አፈፃፀሙ ለዜጎች ተጠቃሚነት ጠብ ያለነገር እንደሌለ ይመሰክራል፡፡
‹‹እውነት ለመናገር ሊዝ ወይም መኖሪያ ሆነ መሥሪያ ቦታ በኪራይ ከሚል አዋጅ ወዲህ የኔ የምለውን ሀገር ያሣጣ ከተማ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎችንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ለጎዳና ያዳረገ አንዱን ለሞት ሌላውን ያለ ምንም እሴት ሚሊየነር ያደረገ ከልማቱ ይልቅ ሀገር ፍቅር አልባ ትውልድ የፈጠረ በመሆኑ ከአገሪቱ ሕግ ሊሠረዝ ይገባል:: በእውነት ለደሃው ዜጋ ካሰባችሁ:: ጎንደር እንኳን በሊዝ ሆኖ ሕጉ ተከብሮም አልቻልነው›› ይላል፡፡
መሬት የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ /ሰብአዊ / ነው እንጂ መንግሥት ባለበት አገር በአንድ ከተማ ውስጥ የአከባቢው ተወላጅ ሆኖ ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ የሆነውን መጠለያ ያጣል??? ሲሉ የሚተቹት ኗሪዎች የሊዝ አፈፃፀም ችግሮች ምንድን ናቸው? የከተማ አስተዳደሩ አፈፃፀም በሊዝ መሬት ላይ ምን ይመስላል ሲል ዝግጅታችን ዳሰሳውን ቀጥሏል፡፡
ሊዝ እና ጎንደር
የሊዝ መሬት ሽያጭን በተመለከተ በጎንደር በስፋት የሚታየው ችግር የተሸጡ መሬቶች ፋይሎች መሰወር ወይም መጥፋት፣ ፋይሉን ወደ ገቢዎች ጽ/ቤት አለማስተላለፍ፣ ከአሸነፈው ውጭ የሊዝ ቦታዎችን ማስተላለፍ፣ ሰነዶችን መሰረዝ፣ ሰነዶችን በአግባቡ አለመያዝ፣ አለመሙላት፣ የሊዝ ክፍያን በአግባቡ አለመሰብሰብ፣ ያልተገባ እፎይታ መስጠት እና ህጋዊ ስርዓቱን በአግባቡ አለመተግበር፣ በሊዝ ቦታ ተሸጦ ደንበኞች ባሸነፉበት ጠ/ዋጋ ውል መያዝ ሲገባ ውልን አሳንሶ በመያዝ እና ሌሎችም ናቸው፡፡ ለአብነትም ከ60 ሚልየን ብር በላይ የያዘ 120 የመኖሪያ ቤትና ወደ 15 ሚልየን ብር የሚጠጋ 10 የንግድ ድርጅት በጥቅሉ ከሰባ አምስት ሚልየን ብር በላይ የያዙ ብዛታቸው 130 የሊዝ ደንበኞች ውል ውስጥ የጎንደር ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ፋይላቸው ያልተገኙ የሊዝ ሂሳብ ባለ ዕዳዎች መካከል 31 ያህሉ ብቻ እየከፈሉ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን ሌሎቹ 99 ፋይሎችን ግን ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ አላውቃቸውም ሲል አረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ በሊዝ አግባብ የተላለፉ ቦታዎች የያዙ ፋይሎች 11 የመኖሪያ ቦታ፤ ብር 4,494,661.00 የገንዘብ መጠን እና አንድ የንግድ ፋይል፤ የያዘው በ2,850,849.00 የገንዘብ መጠን ብር 7,345,510.00 የሊዝ ፋይል ሊገኙ ባለመቻላቸው ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ባለፉት 12 በጀት ዓመታት በጎንደር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ላይ ዓመታዊ የሊዝ ክፍያ ያልከፈሉት የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በየደረጃው ሊሰጣቸዉ የሚገባ ከ1-3 ዓመት የሆናቸዉ ደንበኞች ብዛት 865 ሲሆኑ ያልተሰበሰበ ዉዝፍ ሂሳብ ከአምስት ሚልየን ብር በላይ እንዲሁም ቦታቸዉን ሊነጠቁ የሚገባ ከ4 ዓመት በላይ የሆናቸዉ 357 ደንበኞች ሲሆን ያልተሰበሰበ ዉዝፍ ሂሳብ ብር ከ7 ሚልየን ብር በላይ በአጠቃላይ ወለድና ቅጣትን ሳይጨምር በድምሩ ከ12 ሚልየን ብር በላይ በጽ/ቤቱ ውዝፍ የሊዝ ተሰብሳቢ ሂሣብ እንዳለ አረጋግጠናል፡፡
አንድ የከተማ ነዋሪ ለመኖሪያ አገልግሎት በጨረታ ቦታ ሲያገኙ የቦታ ስፋት 150 ካ.ሜ፣ አሸንፈው ለካሬ ሜትር የተሞላው ዋጋ ብር 7555 የቦታው ጠቅላላ ዋጋ ብር 1,133,250.00 ሲሆን ቅድሚያ ክፍያ ብር 124,657.50 ተቀንሶ ቀሪ ክፍያ ብር 1,008,592.50 ሆኖ ዓመታዊ ክፍያ ብር 25,214.81 በየዓመቱ እስከ 40 ዓመት እየተከፈለ እንደሚጠናቀቅ ዉል መያዝ ሲገባው በየዓመቱ ብር 20,171.85 የሚከፈል ተብሎ ዉል ስለተያዘ ልዩነት 5,042.96 ከዓመታዊው ክፍያ የሚቀር ሲሆን ለ40 ዓመት ብር 201,718.40 ከውሉ ሰነዱ ላይ ዓመታዊ ክፍያው ተቀንሶ ውል በመያዙ ሳይከፈል ቀርቷል፡፡
ሌላው ለንግድ አገልግሎት የሚውል 641 ካ.ሜ ቦታን ለአንድ የግል ሪል ስቴት ማህበር ለካ.ሜ በብር 2,500 ሂሳብ ጠቅላላ ዋጋ ብር 1,602,500 ውል ተይዞ መተላለፍ ሲገባው ውሉ ላይ የተቀመጠው የቦታ ስፋትና ለካ.ሜ የቀረበው ዋጋ ምንም ዓይነት ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ጥቅል ዋጋውን ብር 1,328,500 በማድረግ ቅድመ ክፍያውን ብር 132,850 እንዲሁም ብር 47,826 በየዓመቱ እንዲከፍል በሚል ውል በመያዙ የ109.6 ካ.ሜ ቦታ ዋጋ ብር 274,000.00 ውል ሳይያዝ ከ5 ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡
ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል ለ1 የመለያ ኮድ ቁጥሩ፤ 200 ካ.ሜ ቦታ በጥቅሉ በብር 322,200.00 ተጫራቹ አሸንፎ ቀሪ ክፍያውን በ25 ዓመት ውስጥ አጠቃሎ ለመክፈል ውል በመግባቱ በየዓመቱ ብር 10,310.40 መክፈል እንዳለበት የውል ፎርሙ ተሞልቶ ውሉ መያዝ ሲገባው አሸናፊው ለካ.ሜ ባቀረበው የጨረታ ዋጋ ብር 1,611 በየዓመቱ እየተሰላ እንዲከፍል ተብሎ ውል በመያዙ የሊዝ ውሉን በዓመት በብር 8,699.40 በአጠቃላይ 217,485.00 በማሳነስ ውል ተይዟል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከተሞች ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያ በሊዝ ቦታ ተሸጦ ደንበኞች ባሸነፉበት ጠ/ዋጋ ውል መያዝ ሲገባ ውልን አሳንሶ በመያዝ ከ3 የጨረታ አሸናፊዎች ብር 1,465,000.00 ውል አልያዘም፡፡ ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል ቦታን ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በአዘዞ ድማዛ ክ/ከተማ የቦታው ኮድ አዘዞ ድ.ክ.ከ 911/10 የቦታ ስፋት 200 ካ.ሜ ለአንድ ካ.ሜ በብር 4,505.00 ዋጋ የቦታው ጠቅላላ ዋጋ ብር 901,000.00 አሸንፈው ቅድመ ክፍያ ብር 90,100.00 የከፈሉ ሲሆን ቀሪ ክፍያ ብር 810,900 የጎንደር ከተማ አስ/ከተማ ልማት/ኮን/መምሪያ ግለሰቡ ቦታውን ተረክቦ እያለ ከ3 ዓመት በላይ የሊዝ ውል ከደንበኛው ጋር ሳይያዝና ፋይሉም ወደ ገቢዎች ጽ/ቤት ሳይተላለፍ በመቆየቱ ገቢው እየተሰበሰበ ካለመሆኑም በላይ ኦዲት ሲደረግ ባይደረስበት ኖሮ ሙሉ ገቢው ሳይሰበሰብ የመንግስት መሬት ለግለሰብ መጠቀሚያ ሆኖ እንደሚቀር አመልካች ነው፡፡
አዘ/ማረ.ክ/ከ/07/02 የቦታ ኮድ ቁጥር የተሰጠው ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል 214 ካ.ሜ የሊዝ ቦታን ለካ.ሜ የተሞላው ዋጋ ብር 3,202.00 ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በጥቅል ዋጋ ብር 685,228.00 አሸንፈው ቅድሚያ ክፍያ ብር 71,500.00 ከፍለው ቀሪ ክፍያ ብር 613,728.00 በየዓመቱ ብር 13,948.36 ዓመታዊ ክፍያ ለ44 ዓመት ሊከፍሉ ውል ወስደው የያዙትን የሊዝ ቦታ በቀን 10/10/2011 ዓ.ም ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ስም ያዛወሩ መሆኑ የጎንደር ከተማ አስ/ከ/ል ኮንስትራክሽን መምሪያ ከቦታ ስፋት በስተቀር ሌሎች አስፈላጊ ማስረጃዎችን ማለትም ቀሪ የሊዝ ክፍያ፣ዓመታዊ ክፍያ፣ ክፍያው የሚጠናቀቅበት ዓመት፣ የቦታው መለያ ቁጥር እና ለአንድ ካ.ሜ የቀረበው ዋጋ በትክክል በውሉ ቅጽ ላይ ሳይሞላ ባዶ የውል ወረቀት አዘጋጅቶ ከገዥዋ ጋር ተፈራርሞ ቦታውን አስተላልፎ ተገኝቷል፡፡
ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በሊዝ ጨረታ ለመኖሪያ አገልግሎት የሚውል የቦታ ኮድ ቁጥር በአዘዞ ድማዛ 08/259 የቦታ ስፋት 200 ለአንድ ካ.ሜ ብር 1,700.00 ዋጋ የቦታው ጠቅላላ ዋጋ ብር 340,000.00 አሸንፈው ቅድመ ክፍያ ብር 34,000.00 የከፈሉና ቀሪ ክፍያ ብር 306,000.00 በየዓመቱ ብር 6,120.0 ከፍለው በ50 ዓመት ውስጥ ሊያጠናቅቁ በቀን 10/05/2008 ዓ.ም ውል ገብተው የያዙ ሲሆን የ2012 ዓ.ም አመታዊ ክፍያ በቀን 13/09/2011 ዓ.ም በደረሰኝ ቁጥር 1212190 ብር 6,120.00 ከፍለው ስመ-ንብረቱን በቀን 10/10/2011ዓ.ም ለአንድ የሊዝ ደንበኛ የስም ዝውውር ሲደረግ በገዥ ስም ቀሪ ክፍያ ብር 281,520.00 ሳይሞላ፣ ውሉን በስንት አመት ከፍሎ እንደሚያጠናቅቅ ሳይሞላ እና የውል ፎርሙ አስፈላጊው መረጃ ሁሉ በአግባቡ ሳይሞላ ውል ሰጭና ውል ተቀባይ ተፈራርመው ስመ-ንብረቱ ተላልፎ የተገኘ ሲሆን ቀሪው የሊዝ ዋጋ በቀጣይ ክትትል ተደርጎ እንዳይሰበሰብ ሆን ተብሎ በውሉ በዝርዝር ተሞልቶ አልተያዘም፡፡ በዚህም የሊዝ ገቢው እንዳይሰበሰብ ተመቻችቶ ተገኝቷል፡፡
ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውል የሊዝ ቦታ በቀበሌ 20 አዘዞ አየር ማረፊያ ክፍለ ከተማ የቦታ መለያ ኮድ A03 የቦታው ስፋት 200 ካ.ሜ ለካ.ሜ የተሞላው ዋጋ ብር 1,210.00 በማሸነፍ የቦታው ጠቅላላ ዋጋ ብር 242,000.00 ሆኖ ቅድመ ክፍያ ብር 24,200.00 ከፍሎ ቀሪ ክፍያ ብር 217,800.00 ተብሎ የሊዝ ውላቸውን በ45 ዓመት በየዓመቱ ብር 4,840.00 እንዲከፍሉ በቀን 24/8/2005 ዓ.ም ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ውል የያዙ ቢሆንም ስመ-ንብረቱ በቀን 13/04/2012 ዓ.ም ለአንድ የሊዝ ደንበኛ የስመ ንብረት ዝውውር በመምሪያው ባለሙያ በተያዘው ውል በገዥ ስም ቀሪ ክፍያ ሳይሞላ፣ ውሉን በስንት አመት ከፍሎ እንደሚያጠናቅቅ ሳይሞላ እና የውል ፎርሙ በአግባቡ ሳይሞላ ውል ሰጭና ውል ተቀባይ ተፈራርመው ስመ-ንብረቱ ተላልፎ በመገኘቱ በዚህ ኦዲት ባይደረስበት ኖሮ መረጃውን በመሸፋፈን ቀሪ የሊዝ ገቢው ሳይሰበሰብ እንዲቀር ተመቻችቶ ተገኝቷል፡፡
በአንደኛ ዙር የመኖሪያ አገልግሎት የሚውል ቦታን በጨረታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ አዘዞ አየር ማረፊያ ክ/ከተማ የቦታ ኮድ ቁጥር አዘ.ማረ.ክ 07/07 የቦታ ስፋት 299.19 ካ.ሜ ለአንድ ካ.ሜ ብር 2,700.00 በጥቅል ዋጋ በብር 807,813.00 አሸንፎ ቅድመ ክፍያ ብር 80,781.00 ከፍለው ቀሪ ክፍያ ብር 727,032.00 ተብሎ ውል መያዝ ሲገባው ውሉ ላይ ለካ.ሜ ብር 2,700.00 የተሞላውን ዋጋ በመሰረዝና ዋጋውን በመቀነስ ብር 1,800.00 በማድረግ አጠቃላይ ዋጋ ብር 540,000.00 ቅድመ ክፍያ ብር 80,781.00 ቀሪ ክፍያውን ብር 459,219.00 በየዓመቱ ብር 11,480.47.00 ከፍለው በ40 ዓመት ውስጥ ሊያጠናቅቁ በቀን 13/09/2007 ዓ.ም የመምሪያው ባለሙያ ቀሪ የሊዝ ገቢውን በብር 267,813.00 አሳንሶ አላግባብ ውል በመያዝ ገቢው እንዳይሰበሰብና ለግል ጥቅም እንዲውል ሆን ብለው ሰነድ በመሰረዝ አጭበርበርው ተገኝተዋል፡፡
ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ለንግድ አገልግሎት የሚውል የቦታው መለያ ቁጥር ማራኪ ቀበሌ 03 የቦታው ስፋት 520 ካ.ሜ ለአንድ ካ.ሜ በብር 3,006.00 በአጠቃላይ በብር 1,563,120.00 አሸንፎ በቀን 24/8/2005 ዓ.ም ውል የወሰደ ቢሆንም በወቅቱ በገባው ውል መሰረት ወደ ስራ ባለመግባቱ በቀን 02/12/2009 ዓ.ም ቦታውን ሲነጠቅ ከጥቅል ዋጋው ላይ የሚታሰብ 7% ቅጣት ብር 109,418.40 እና እስኪነጠቅ ባለው ጊዜ ያልከፈለው አመታዊ የሊዝ ክፍያ የ4 ዓመት ብር 187,574.40 ከወለድ ውጪ በድምሩ ብር 296,992.80 ቦታው እስኪነጠቅ ከሚፈለግበት ጠቅላላ ዕዳ ላይ አስቀድሞ የከፈለው ቅድመ ክፍያ ብር 156,312.00 ተቀንሶ ልዩነቱ ብር 140,680.80 ሳይከፍል በክልሉ ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 103/2004 ዓ.ም አንቀጽ 37 ንኡስ አንቀጽ 5(ሀ) በመጣስ ውሉ ተቋርጧል፡፡
በ1ኛ ዙር የመኖሪያ አገልግሎት የሚውል ቦታ በጨረታ ለአንድ የሊዝ ደንበኛ በአዘዞ ማራኪ ክፍለ ከተማ የቦታ ኮድ ቁጥር አዘ/ማ/ክ/ከ 07/34 የቦታ ስፋት 200 ካ.ሜ ለካ.ሜ በብር 1,120.00 ጠቅላላ የቦታ ዋጋ ብር 224,000.00 ቅድሚያ ክፍያ ብር 25,000.00 በመሙላት የተወዳደረውን ተጫራች አንደኛ አሸናፊ በማለት የጨረታ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቃለ-ጉባኤ አጽድቀው ለህዝብ ይፋ ካደረጉ በኋላ ከደንበኛዋ ጋር የሊዝ ውሉ ሲያዝ ግን ዋጋውን አላግባብ ከብር 1120.00 ወደ ብር 900.00 ዝቅ በማድረግ ማለትም በብር 900.00 ሲባዛ 200 ካ.ሜ ጠቅላላ የቦታ ዋጋ ብር 180,000.00 ላይ ቅድሚያ ክፍያ ብር 18,000.00 ተቀንሶ ቀሪ ክፍያ ብር 162,000.00 በማድረግ አላግባብ ውል ተይዞ ተገኝቷል፡፡ ይህም ተወዳዳሪዋ ለማሸነፍ ከሞላችው የሊዝ ጨረታ ዋጋ ላይ በድምሩ በብር 44,000.00 በማሳነስ ውል ተይዞ ተገኝቷል፡፡
በመጨረሻ ማሳያ ያደረግነው ለአንድ የሊዝ ደንበኛ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውል የሊዝ ጨረታ ቦታ በቀበሌ 20 አዘዞ አየር ማረፊያ ክፍለ ከተማ የቦታ መለያ ቁጥር C03 የቦታ ስፋት 200 ለካ.ሜ አንደኛ አሸናፊው በጨረታ የሞላው ዋጋ ብር 1,732.00 (200 ካ.ሜ ሲባዛ በብር 1,732.00) ጠቅላላ የቦታው የሊዝ ዋጋ ብር 346,400.00 ሆኖ በቃለ-ጉባኤ ጭምር በግልጽ የተመለከተ ቢሆንም፤ በቀን 08/8/2005 ዓ.ም የኮሚቴ ሰብሳቢው በፃፉት ደብዳቤ ብር 1,601.00 በመሙላት ሁለተኛ የወጣውን ተጫራች አንደኛ አሸናፊ እንደ ሆነ ተደርጎ ውል እንዲይዝ በአድራሻ በተጻፈለት መሰረት በቀን 30/8/2005 ዓ.ም ውል ሲያዝ ብር 1,601.00 ሲባዛ 200 ካ.ሬ ጠቅላላ የቦታው የሊዝ ዋጋ ብር 320,200.00 በማለት የቅየሳና ካርታ ዝግጅት ኦፊሰር ውል ይዘዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሊዝ ዋጋው ላይ አላግባብ ብር 26,200.00 (ብር 131.00 ሲባዛ በ200 ካ.ሜ) ውል ሳይያዝበት በመቅረቱ በመመሪያ ቁጥር 1/2005 አንቀፅ 26 /5/ መሰረት ትክክለኛነቱ ሳይረጋገጥ ውሉ ጸድቆና 1ኛ የወጣውን ተጫራች ኢፍተሃዊ በሆነ አሰራር ወደ ጎን በመተው ቦታውን የመንግስትን ገቢ ባስቀረ ሁኔታ ለ2ኛው ተወዳዳሪ መሬቱ ተላልፎለታል፡፡ በአጠቃላይ በከተማው በድምሩ ከተገቢው መጠን በታች (በማነስ) ውል የተያዘበት ብር 4,560,845.20 ሆኖ ተገኝቷል፡፡