ሐምሌ 17 ፣ 2013

አሰልቺው የባንኮች የመንገድ ላይ ውትወታ

City: Dire Dawaአካባቢ

ከቁጥራቸው መጨመር ጋር ተያይዞ ባንኮች ደንበኛ ወደ እነርሱ እንዲሄድ መጠበቃቸውን አቁመው ወደ ደንበኛው የሚያስኬዷቸውን አማራጮች በመከተል በየቦታው የባንክ ደብተር እንዲያወጡ ከመነዝነዝ ባልተናነሰ መልኩ መጠየቃቸው ብዙዎችን አማሯል።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

አሰልቺው የባንኮች የመንገድ ላይ ውትወታ

የኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ የሚጀምረው በ1887 ዓ.ም. እንደሆነ አቶ በላይ ግደይ “ገንዘብ፣ ባንክ እና መድኅን በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በተጠቀሰው ዓመት የተቋቋመው የመጀመርያው ባንክ ስራ የጀመረው በ1901 ዓ.ም. መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ መረጃው እንደሚያሳየው 126 ዓመት ያስቆጠረው የባንክ ስርአት እድገት የእድሜውን ያህል እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የባንክ ተጠቃሚው ቁጥር አሁንም እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የባንኮቹ ቁጥርም ኢኮኖሚው እና የሕዝቡ ብዛት ከሚፈልገው አንጻር አነስተኛ ስለመሆኑ የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ አሁን ያሉን ባንኮች ልዩነት የስም ብቻ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ገበያው ላይ ያሉት ባንኮች በብድር አሰጣጥ፣ በወለድ ምጣኔ፣ በደንበኛ አያያዝ እና ሌሎች ጉዳዮች ያላቸውን ተመሳሳይነት ይተቻሉ፡፡ ተጠቃሚው እንደ ፍላጎቱ የሚቀላቀላቸው ባንኮች ባለመኖራቸው ባንኮቻችን ምርጫ እንጂ አማራጭ የላቸውም የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቁጥራቸው መጨመር ጋር ተያይዞ ባንኮች ልዩ ልዩ አሰራሮችን መከተል ጀምረዋል፡፡ ደንበኛ ወደ እነርሱ እንዲሄድ መጠበቃቸውን አቁመው ወደ ደንበኛው የሚያስኬዷቸውን አማራጮች እየተከተሉ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ከላይ እንዳነሳነው የባንኮች የውስጥ አሰራር ሁሉ ተመሳሳይነት ቢኖረውም ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር ግን የተለየ ነው፡፡

ለዚህ እንደ ምሳሌ የውጭ ሐገር ገንዘቦችን ለሚመነዝሩ የተለያዩ ማበረታቻዎች መስጠት፣ ቆጣቢዎችን በዓመታዊ እጣ መሸለም፣ ለቆጣቢ ሴቶች አበረታች ወለድ መክፈል፣ ከወለድ ነጻ አገልግሎት መስጠት፣ ደንበኛው የሚገኝባቸው አካባቢዎች በመገኘት አካውንት ማስከፈት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ደንበኛው ባንክ መሄድ ሳያስፈልው ባንኮቹ ወደ ንግድ ተቋሙ ሰራተኞች ልከው እለታዊ ገቢ የሚሰበስቡበት፣ ከስራ ቀንና ሰዓት ውጭ የሚሰሩበት፣ በስልክ ትእዛዝ ጥሬ ገንዘቡን ለደንበኛው የሚያቀብሉበት አሰራሮች ደግሞ ዛሬ ላይ እንደ ቅንጦት እየተቆጠሩ ያሉ ጥቂት ባንኮች የሚከተሏቸው አሰራሮች ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት መንገድ ላይ፣ በስራ ቦታ፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የባንክ አካውንት ለማስከፈት የሚጥሩ ባንኮችን የሚመለከት ነው፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ብቻ ሳይሆን መዲናዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም የሐገሪቱ ከተሞች እየተለመደ የመጣው በመንገድ ላይ ወይም በስራ ቦታ የባንክ አካውንት የማስከፈት ሂደት እንዳማረረው የነገረን ወጣት አቡበክር ሁሴን ይባላል፡፡ ነዋሪነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ አስተያየቱን የጀመረው አንድ አጋጣሚውን በማስቀደም ነው፡፡

‹‹አንድ ጊዜ ገንዘብ ለማውጣት ባንክ ሄድኩ፡፡ የባንክ ቡኬን ስላልያዝኩና ቁጥሩን በቃሌ ስላላወቅኩት በስልክ ቁጥሬ አውጡልኝ አልኩ፡፡ እሺ ብለው ሲያወጡልኝ ግን በእኔ ስልክ እና ስም 3 አካውንት ተገኘ፡፡ መቼ እንዳወጣሁት ለማወቅ ብዙ ማስታወስ ነበረብኝ›› ብሎናል፡፡ ሁኔታው እንዴት እንደተፈጠረ ሲያስረዳም “የአንድ ባንክ ቅርንጫፍ ቢሮ ለአገልግሎት ያመራ ደንበኛ የተመሳሳዩ ባንክ ደብተር ቢኖረው እንኳን የራሳቸው ቅርንጫፍ ላይ ድጋሚ እንዲያወጣ ያስገድዱታል፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች ሳያስቡት እና ጉዳያቸው እንዲያልቅላቸው ብቻ አካውንት እንዲከፍቱ አድርጓል” ሲል ሐሳቡን ነግሮናል፡፡

“በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ በየአካባቢው እየዞሩ ሰዎች የባንካቸው ደንበኛ እንዲሆኑ ይቀሰቅሳሉ፡፡ በማስረዳት እና በማባበል ጭምር ባንክ ደብተር ያስከፍታሉ፡፡ ይህ አሰራር ለባንኮቹም ሆነ ለደንበኞች የሚሰጠው ጠቀሜታ እንዳለ አይካድም፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት ባንክ መሄድ ያልቻለው ደንበኛ ካለበት ቦታ ሳይንቀሳቀስ የባንክ አገልግሎት የሚያገኝበትን እድል ያመቻችለታል፡፡ ባንኮችም በአጭሩ የደንበኞቻቸውን ቁጥር በረዥሙ የተቀማጭ ገንዘባቸውን መጠን ከፍ ያደርጉበታል፡፡ በተቃራኒው ባንኮቹ ይህንን መሰሉ ተደጋጋሚ ውትወታ ተጠቃሚውን ሊያሰለች እንደሚችል የዘነጉት ይመስላል፡፡” በማለት የሰጠንን አስተያየት ደምድሟል፡፡

የተሰላቸውን ተጠቃሚ የሚወተውቱት የባንክ ባለሙያዎችም ጫና ውስጥ ናቸው፡፡ በራሳቸው ገንዘብ መንገድ ላይ ላገኙት ተጠቃሚ አካውንት የሚከፍቱ ባለሙያዎች እንዳጋጠሟቸው ለዚህ ጽሑፍ ያነጋገርናቸው የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡

“አንድ ሰው በይሉንታም ይሁን ጭቅጭቁን ጥላቻ እስከ አምስት የተለያየ አካውንት ይኖረዋል በአምስቱም አካውንት ግን ይጠቀማል ማለት ከባድ ነው” ያለችን ደግሞ ራሄል ተክሉ ነች፡፡ የምትሰራበትን ቢሮ በቀየረች ቁጥር የባንክ አካውንት እንደምታወጣ የምትናገረው ራሄል ባንኮች በጋራ የሚሰሩበት አሰራር ቢኖር የማይጠቀሙበትን የባንክ ደብተር ከመሰብሰብ እንደሚያድን ሐሳቧን ሰጥታለች፡፡

የተለያዩ የንግድ ተቋማትንና ድርጅቶችን ተዘዋውረን ባነጋገርንበት ወቅት በባንኮች የአካውንት ክፈቱ ውትወታ እንደተማረሩ የሚገልፁ ብዙዎች ናቸው፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ኮፒ ቤት ያላት ናርዶስ እሸቱ የተባለች ወጣት እንደገለፀችው በሳምንት ከሦስት ጊዜ በላይ የተለያዩ ባንኮች ሰራተኞች የስራ ቦታዋ እየመጡ አካውንት እንድትከፍት ይጠይቋታል፡፡ ይበልጥ ያስገረማት ነገር ደግሞ ልጆቹ “አልፈልግም” ወይም “አለኝ” የሚል መልስ ሲሰጣቸውም ለመሄድ ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ነምበርዋን ሰፈር የምትኖረው ህይወት የፀጉር ቤት ባለቤት ነች፡፡ “ከደሀው ሕብረተሰብ ላይ ሀምሳ ብር መቀማት ነው የተያዘው፡፡ ሰው በሚያተርፈው ልክ በአንድ ባንክ ቤት ቢቆጥብ በቂ ነው፡፡ በይሉንታና በትውውቅ የማንጠቀምበትን አካውንት እንድንከፍት ያደርጉናል፡፡” ስትል ምሬቷን ታብራራለች፡፡

ሁኔታው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመግቢያ ሰሞኖች ላይ እንደሚባባስና ተማሪዎችም ባለማወቅ የማይጠቀሙባቸውን የባንክ ደብተሮች እንደሚሰበስቡ አጫውታናለች፡፡ 

ዐየሁ ሙላቴ የተባለች ተማሪ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዓመት ተማሪ ስትሆን ሁለት አካውንት ሳትፈልግ እንደከፈተች ገልጻ በተለይ ልክ እንደ እርሷ ብዙም የባንክ አገልግሎት ካልተስፋፋበት አካባቢ የሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎች እንደሚደናገሩና ላልሆነ ወጪ እንደሚዳረጉ ገልፃለች፡፡

አስተያየት