የፊት ቆዳን ውበት ለመጠበቅ ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸውን ንጥረ-ነገሮች መጠቀም ይመከራል፡፡ ኬሚካል የተቀላቀለባቸው የፋብሪካ ምርቶች ጥቅም እንዳላቸው ሁሉ የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በሐገራችን በተለያዩ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች እና የውበት መጠበቂያዎች መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ፊትን፣ ጸጉርን፣ የሰውነት ቆዳን፣ የእጅ እና የእግር ጥፍርን እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ለማስዋብ የሚያገለግሉ ባህላዊ መዋቢያዎች አሉ፡፡ መዋቢያዎቹ በዱቄት፣ በፈሳሽ እና በጭስ መልክ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ መዋቢያዊቹ ለምግብነት የሚያገለግሉ ወይም ለመዋቢያ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በየሀገሩ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ ነገሮችን መጠቀም የተለመደ ሲሆን በበረሀዋ ንግሥት ድሬዳዋ ደግሞ “ቀሲል” እና እርድን መጠቀም በስፋት የተለመደ ነው፡፡ ቀሲልን በብዛት የሚጠቀሙት በጅግጅጋ እና ድሬዳዋ ነው፡፡ የፊታችን ቆዳ በተለያየ ምክንያት ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ለምሳሌ እንደነዚህ ዓይነት ጉዳቶች በሚያጋጥምበት ወቅት በአንድ ጊዜ የሚመጣ ለውጥ ባለመኖሩ ይህን ተፈጥሮአዊ የሆነ የመዋቢያ ንጥረ ነገር በተደጋጋሚ በሳምንት፣ በሁለት ሳምንት ገፋ ካለ በወር አንድ ጊዜ የምንፈልገውን ለውጥ ለማምጣት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ከሻጮች እና ከተጠቃሚዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
“ቀሲል” በገበያዉ ላይ ያለው የዱቄት ምርት መጠሪያ ሲሆን ቃሉ ሶማልኛ ነው፡፡ የቀሲል ምርት መገኛ በቆላ አካባቢ የሚበቅል “ቁርቁራ” የተሰኘ ዛፍ ነው፡፡ ቁርቁራ አነስተኛ ፍሬዎች ያሉት ሐገር በቀል ዛፍ ሲሆን በሰሜን ጎንደር እና በትግራይ አካባቢዎች “ገባ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በኢትዮጵያ ቆላ ምድር ሁሉ የሚገኝ ሲሆን የጂጂጋ ሰዎች ውበታቸውን ለመጠበቅ የበለጠ ያዘወትሩታል፡፡
ለአዘገጃጀቱ የቅጠሉ ለጋና ጠንካራው ክፍል ይለይና እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ ጅግጅጋ በሚገኝ የተዘጋጀለት ልዩ ወፍጮ ይፈጫል፡፡ በኩንታል እየተሞላ ለሀገር ውስጥ ገበያ ተጭኖ ይጓጓዛል፡፡ ቀሲል ከእርድ ጋር ተቀላቅሎ በውሀ በጥብጦ ጥቅም ላይ ሲውል ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ ተጠቃሚዎቹ ያምናሉ፡፡ ከተጠቃሚዎቹ መካከል ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ወዛም የፊት ቆዳን በብጉር ከመጠቃት እንደሚያስጥል፤ ዳግመኛ ብጉር እንዳይከሰት እንደሚያደርግ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በብጉር ወይም በሌላ ምክንያት የተጎዳን ፊት ያጠራል ብለውናል፡፡ እርድም ልክ እንደ ቀሲል ለብዙ ሺህ ዘመናት ለውበት እንዲሁም ለመድኃኒትነት የሚውል ቅመም ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እርድን መመገብ የካንሰርና የስኳር በሽታን ለመከላከል እንደሚረዳም የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከእዚህ ባለፈ እርድን በቀሲል ደባልቆ መጠቀም ቆዳን ከማስተካከሉ በተጨማሪ የተሰነጣጠቀ ተረከዝን ለማስተካከልና ለፀጉር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
“ፀጉር እንደሌላው የሰውነት ክፍላችን በቂ እንክብካቤ ልናደርግለት ይገባል፡፡ የፀጉር መሳሳት ወዝ ማጣት፣ መሰባበር፣ እና መነቃቀል እንዲሁም የራስ ቆዳ በፎሮፎር በተለያዪ የፈንገስ ዓይነት እና በቆሮቆር መጎዳት እንዲሁም የራስ ቆዳ መድረቅ ዋና ዋና የፀጉር ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሮቹን ከሚያባብሱብን ነገሮች ደግሞ ዋነኞቹ ንፁህ ባልሆነ ውሀ መታጠብ፣ ተስማሚ ያልሆነ ቅባት እና ሳሙና ወይም ሻንፖ መጠቀም፣ በማይመቸን የፀጉር ቀለም መዋብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሌላው በቂ ንጥረ ነገር ያልው ምግብ በተለይ ፕሮቲን፣ ቫይታሚን እና ማዕድናት አለማግኘት እና ፀጉር በፀሐይ ሙቀት በከፍተኛ ሁኔታ ሲጎዳ ነው፡፡ ታዲያ ለእነዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ የሚያሻዎት ከሆነ ይህንን ተፈጥሮአዊ ንጥረ ነገር በተደጋጋሚ በመቀባት መፍትሄ ማግኘት ይችላሉ” ያለችን የጸጉር ውበት ባለሙያ የሆነችው ወ/ሮ አስቴር መክብብ ነች፡፡ አስቴር ደንበኞቿ ከዘመናዊ የውበት መጠበቂያዎች በተጨማሪ በባህላዊ ቅመሞች ውበታቸውን እንዲጠብቁ እንደምታበረታታም ነግራናለች፡፡
ሀይማኖት አየለ የተባለች ወጣት ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ይህንን የቀሲል ማስክ እጠቀማለሁ ያለችን ሲሆን ለፊቷ ጥራት እንደጠቀማትና ፊቷ ላይ ጥቋቁር ነጠብጣቦች እንደነበረባት እና እርሱን ለመሸፈን ዘመናዊ የፊት መሸፈኛ ሜክአፕ ትጠቀም እንደነበረ ነግራናለች፡፡ ቀሲል እና እርድን በመቀላቀል መጠቀም ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ ግን በፊቷ ላይ ለውጥ ማየቷን አጫውታናለች፡፡ ተፈጥሯዊው ቅመም ጉዳት ካለማስከተሉ በተጨማሪ ፍቱን መሆኑንም ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡
ድሬደዋ ውስጥ ቀሲል የሚሸጠው አሸዋ ተብሎ በሚጠራው የገበያ ስፍራ ሲሆን የቀሲልና የእርድ ገበያው የተጧጧፈ እንደሆነ ሂስ የተባለች የቀሲል ነጋዴ አጫውታናለች፡፡ በተለይ የቀሲልን ጥቅም የሚያውቁት በአብዛኛው የሶማሌ ሴቶች እንደሆኑና አብዛኛዎቹ ደንበኞቿ እነሱ እንደሆኑ ገልፃ ነገር ግን ሁሉም የድሬደዋ ነዋሪ ቀሲል የሚሰጣቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ቢረዳ መልካም እንደሆነ ትገልፃለች፡፡
ብዙ ሰዎች የተለያዩ የውበት ሳሎኖች ጎራ ብለው ፌሻል፣ ስቲም ወይም ሌላ ነገር ፊታቸውን መሰራታቸው በቂ እንደሆነ ያስባሉ ነገር ግን ቤታቸው ተፈጥሮአዊ በሆኑ ንጥረ-ነገሮች እራስን መንከባከብ እንደሚገባ የገለፀችው በራይት የውበት ሳሎን ውስጥ የፊት ባለሞያ የሆነችው ስንታየሁ በተለይ ቀሲል ለማግኘት በጣም ቀላል ስለሆነና ዋጋውም ተመጣጣኝ በመሆኑ ሌሎች ኬሚካል ያለባቸውን ንጥረ ነገሮች ከመጠቀም ተቆጥበን ተፈጥሮአዊ የሆኑ ነገሮችን መጠቀም እንደሚገባ ትመክራለች፡፡