መጋቢት 30 ፣ 2013

“ዱንጉዛ” የጋሞ የሸማ ጥበብ

City: Hawassaባሕል

ከሦስት ቀለማት (ቢጫ፣ ጥቁር፣ ቀይ) ተሸምኖ የሚቀርበው “ዱንጉዛ” የጋሞዎች መለያ የሆነ ባህላዊ ልብስ ነው።

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

“ዱንጉዛ” የጋሞ የሸማ ጥበብ

ባህላዊ አልባሳት አንደየሀረገሰቡ ባህል ወግ እና ልማድ የተወከሉበትን ማኅበረሰብ ሀገር-በቀል እውቀት፣ ዕደ-ጥበብ፣ እሳቤ እና የአኗኗር ዘዬ ያንጸባርቃሉ፡፡ በሸማ ፈትል ጥበባቸው የሚመርጧቸው ቀለማት ራሳቸውን ይገልጻሉ፡፡ የሸማ ጥበብ ሥራ እምብርት፣ የሰላም ተምሳሌት አባቶች መገኛ እንደሆነች የሚነገርላት የምድር ገነቷ አርባ ምንጭ በቀድሞው የሰሜን ኦሞ አስተዳደር እና የጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት አውራጃዎች ማዕከላዊ መቀመጫ ነበረች። በአሁኑ የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና ከተማ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።

የአርባዎቹ ምንጮች መፍለቂያ፤ የእግዜር ድልድይ፣ የመንታያዎቹ አባያ እና ጫሞ ስምጥ ሸለቆዎችን ተንተርሳ የከተመችው አርባምንጭ እንደ ባህሏ አከባቢዋም በተፈጥሮ መስህቦች የታጀበ ነው። ለአብነት ያህል የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክን፣ የአዞ እርባታንና ገበያን፣ የተፈጥሮ ጥቅጥቅ ደኖቿን ማንሳት ይቻላል፡፡

ጋሞዎች ወደነርሱ የመጣን እንግዳ ጥበብ ፈትለው ዱንጉዛ ሸምነው ማድመቅ ያውቁበታል። የብሄረሰቡ መለያ ቀለም የሆነው ይህን የባህል ልብስ ጋሞዎች ሐዴ (ዱንጉዛ) ይሉታል። ከምዕራብ አፍሪካዊ ሀገራት የባህል ልብሶች ጋር ቅርበት አለው። በቀደምት የጋሞ ብሄረሰብ ባህላዊ የአስተዳደር እርከን መሠረት የሹማምንቱ የማዕረግ ልብስ እንደነበር የእድሜ ባለፀጎች ያወሳሉ። ሹማምንቶቹም ከድንጉዛ የክብር ልብስ ውጪ ሌላ አልባሳትን እንዲለብሱ አይመከርም። ይሁን እንጂ ታላላቅ ሠዎች የሀገር ሽማግሌዎች በሞት ሲለዩ የለቅሶውን አውድ ለማድመቅ ሲባል ይለበስ እንደነበር ይነገራል።

በባህላዊ የሹመት እርከን ስርአት መሠረት ቀደምት ሹማምንቶች ለአዲሶቹ ጭንቅላታቸው ላይ ቅቤ ቀብተው የጀግንነት ማዕረግ አጎናፅፈው ወደ ሥልጣን መረከቢያው አውድ ያቀናሉ። በዚህ አውድ ቀደምት ሹማምንቶችም ሆኑ አዲሶቹ ከዱንጉዛ ውጪ ሌላ አልባሳትን እንዲለብሱ አይፈቀድም።

ቀደምት ጋሞዎች ባልዘመነው እና ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት ዘመን ከተፈጥሮ የሚያገኟቸውን ቀለማት በቂቤ በመቀቀል እና በመንከር ተፈላጊውን ቀለም የያዙ ክሮችን ይፈጥሩ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ክሮቹም ደርቀው ተፈላጊውን ቀለም ከያዙ በኋላ በሽመና በባለሙያ ይሸመናሉ። ከሦስት ቀለማት (ቢጫ፣ ጥቁር፣ ቀይ)  ተሸምኖ የሚቀርበው ይህ ዱንጉዛ በጋቢ፣ በቡሉኮ፣ በነጠላ፣ በባርኔጣ እና በልዩ ልዩ መልክ ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት ይቀርባል፡፡

በበዓላት ቀናት እና በማኅበራዊ ሁነቶች ላይ ብቻ ይዘወተር የነበረው በዱንጉዛ በአዘቦት ቀናትም መዘውተር ጀምሯል፡፡ ከዘመናዊ አልባሳት ጋር ተቀላቅሎ የዕለት ተዕለት ልብስ ወደመሆን እያደገ ይገኛል፡፡

 

አስተያየት