ሚያዝያ 6 ፣ 2013

አወዛጋቢው የኮሮና ቫይረስ ክትባት እና የቅድመ ላብራቶሪ ምርመራ አስፈላጊነት

ኮቪድ 19ትንታኔወቅታዊ ጉዳዮች

ክትባቱን ለማግኘት የቅድመ ምርመራ ለምን እንደማያስፈልግ አዲስ ዘይቤ የጤና ሚኒስቴርን እና ባለሞያዎችን አነጋግልሯል።

Avatar: Rehobot Ayalew
ርሆቦት አያሌው

Rehobot is a lead fact-checker at HaqCheck. She is a trainer and a professional who works in fact-checking and media literacy.

አወዛጋቢው የኮሮና ቫይረስ ክትባት እና የቅድመ ላብራቶሪ ምርመራ አስፈላጊነት

በዩኔስኮ ፣ በአለም ጤና ድርጅት እና በሌሎችም ተቋማት የሚመራውን የኮቭድ-19 ክትባት ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት የሆነውን ኮቫክስ አስትራዜኔካ ክትባት ከተቀበሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች።

የክትባቱ መርሃ ግብር የተጀመረው መጋቢት 4 2013 ሲሆን የጤና ባለሞያዎች ተቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መጋቢት 23 ባወጣው መግለጫ ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው እንዲሁም ከ55 እስከ 64 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ተጓዳኘ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ከመጋቢት 27 ጀምሮ ክትባት መውሰድ እንደሚጀምሩ ገልጿል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶር ሊያ ታደሰ መጋቢት 5 ቀን በሰጡት ሌላ መግለጫ “የኮቪድ 19 ክትባትን ለማግኘት ምንም ዓይነት የኮቪድ 19 ቅድመ ላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ አያስፈልግም!” ሲሉ አስረግጠዋል።

ክትባቱን ለማግኘት የቅድመ-ላብራቶሪ ምርመራ ያስፈልጋል እና ሌሎች ክትባቱን በተመለከተ የሚነገሩት ነገሮች ሀሰት መሆናቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ሰለሆነም ህብረተሰቡ ከአላስፈላጊ ወጪ አልፎም ከሚፈጠረው ትርምስና አካላዊ ንክኪ እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርበዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ክትባቱን ለማግኘት የኮቪድ 19 ቅድመ-ላብራቶሪ ምርመራ እንደማያስፈልግ የተሰጠውን መግለጫ ተከትሎ  የተነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን እና ስጋቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት አዲስ ዘይቤ የጤና ባለሞያዎችን አነጋግሯል።።

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከል ማዕከል (ሲ.ዲ.ሲ) ዘገባ እንደሚያመለክተው የኮቪድ -19 ምልክቶች የታዩባቸው እንዲሁም ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቁ ሰዎች ከበሽታው እስኪያገግሙ መጠበቅ አለባቸው። ይህ መመሪያ የመጀመሪያ ክትባታቸውን ከወሰዱ በኋላ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎችም የክትባቱን ሁለተኛ ዙር ለመውሰድ እስኪያገግሙ ድረስ መጥበቅ እንዳለባቸው ይመክራል። የሲዲሲው ምክር የሚያሳየው አንድ ሰው ቫይረሱ ኖሮበት ክትባቱን ለመውሰድ በሚሄድበት ጊዜ ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ስለሚችል ወደ ውጭ መውጣት እንደሌለበት እና እስኪያገግሙ ድረስ እራሱን አግልሎ እንዲቆይ ከማሳሰብ አንጻር ነው።

በእንግሊዝ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት እንደሚለው በቫይረሱ የተያዘ ሰው የኮቪድ ክትባት ከመውሰዱ በፊት 28 ቀናት መጠበቅ አለበት። ይህም 28 ቀን የሚለው፤ የኮቪድ ምልክቶች ከታየበት ቀን አንስቶ ወይም ምልክት ካላሳየ ደግሞ ምርመራ ካደረግክበት ቀን አንስቶ ነው። እንዲህ አይነቱ ትልቅ የክትባት መርሃ ግብር የማካሄድ ሂደቱን የተሳለጠ እንዲሆን የኮቪድ ቅድመ ምርመራዎች ማድረግ እንደ ወሳኝ መስፈርት አይታይም።

አዲስ ዘይቤ የቅድመ ላብራቶሪ ምርመራ ለምን እንደማያስፈልግ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር መሠረት ዘላለምን ጠይቋል፡፡ እርሳቸውም “ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመመርመር አቅም የለንም። የአለም ጤና ድርጀትም ቢሆን እንዲህ ባለው ሁኔታ ማለትም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሰው መከተብ ሲያስፈልግ ቅድመ ምርመራ ሳይደረግ መከተብ እንደሚቻል ይፈቅዳል።” በማለት መልሰዋል። አክለውም ይህ መመሪያ ለኮቪድ -19 ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ወረርሽኞችም ጥቅም ላይ እንደሚውል አስታውሰዋል።

የአለም ጤና ድርጅት ታህሳስ 30 2013 ፍቃድ ያገኙ ክትባቶችን ማን መውሰድ እንደሚችል ለመግለጽ ባወጣው ጽሁፍ ክትባቱን ለመውሰድ ቅድመ ምርመራ አስፈላጊ እንዳልሆነ አስነብቧል።

በአዲስ አበባ ከተማ ግንባር ቀደም የኮቪድ ህክምና እና ክትትል ከሚያደርጉ የጤና ባለሞያዎች አንዱ የሆነው ዶ/ር እዮስያስ ከበደ እንደሚለው "አንድ ሰው ክትባት ለማግኘት የላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚታይ አይደለም። የአለምጤና ድርጅትን የመሳሰሉ ድርጅቶች መመሪያ እንደሚነግሩን በቫይረሱ ተይዞ ክትባቱን መውሰድ ልዩ የሆነ አደጋ የለውም ሆኖም እንደ ትኩሳት ፣ ራስ ምታት እና ድካም ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች በቀጣዮቹ ቀናት የተለመዱ ናቸው።”

አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው ሌላኛው የጤና ባለሙያ አክለውም ቫይረሱ ያለባቸው በእድሜ የገፉ ሰዎች ቢከተቡም እንኳን አሳሳቢ የሚሆን ጉዳት የለውም። ከዛ በዘለለ ቫይረሱ በውስጣቸው ከሌለ ደግሞ እራሳቸውን የመከላከል እድል ያገኛሉ ብለዋል።

“ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ካሉ?” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር መሰረት በሰጡት መልስ በቫይረሱ ተይዞ ​​ክትባትን ከመውሰድ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል የታወቀ አደጋ እንደሌለ ተናግረው የክትባቱ የተለመዱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሁልጊዜ ይጠበቃሉ ብለዋል። በመቀጠልም ከክትባቱ በፊት መከተል ያለበት የአሠራር ሂደት እንዳለም ጠቁመው ፣ ይህም ግለሰቡ ምን እንደሚሰማው ቅድመ ግምገማ ማድረግ ነው ብለዋል። አንድ ሰው ክትባት ለመውሰድ ሲሄድ የሚደረገው የመጀመሪያው ነገር ግለሰቡ ትኩሳት፣ ድካም ወይም ሌላ የህመም ምልክቶች ካሉት መጠየቅ ነው። የኮቪድ 19 ምልክቶችን ካሳዩ በተቻለ ፍጥነት የላብራቶሪ ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን ምልክቶቹ ከኮቪድ -19 ጋር የማይዛመዱ ሆነው ግን ግለሰቡ ጥሩ ስሜት የማይሰማቸው ከሆነ ሲሻላቸው እንዲመለሱ ይነገራቸዋል።

እስካሁን ድረስ በኮቫክስ መርሃግብር 2.2 ሚሊዮን ክትባቶች ለኢትዮጵያ እንዲቀርቡ ተደርጓል። ከዛም በተጨማሪ የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ያደረገውን 300 ሺህ ዶዝ ሲኖፋርም የተሰኘው ክትባት መጋቢት 21 ወደ ሀገሪቷ ገብቷል። በሀገሪቷ እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደተከተቡ ግልፅ ባይደረግም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እስከ ሚያዚያ 4 ባለው ጊዜ የህክመና ባለሞያዎችን እና እድሜያችው ከ55 በላይ የሆኑ ሰዎችን ጨምሮ ከ72 ሺህ 600 በላይ ሰዎች ክትባቱን መውሰዳቸው ተዘግቧል። 

ክትባቱን የተከተቡ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለበት የ58 ዓመት ሰው ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጹት የጤና ባለሙያዎቹ ክትባቱን ከመስጠታቸው በፊት የቅድመ ምዘና እንዳደረጉ ገልጸው በምዘናውም ክትባቱን ለመውሰድ በሄዱበት ወቅት ምን አይነት ስሜት እየተሰማቸው እንዳለ እንዲሁም ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ የትኛውም አይነት ህመም ምልክቶች ማሳየታቸውን መጠየቃቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም የክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ግልፅ በሆነ መንገድ እንደተብራራላቸው አክለዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው ሌሎች የጤና ባለሙያዎች፤ ክትባቱን ለመውሰድ ጥሪ የቀረበላቸው የህብረተሰቡ አካላት በክትባቱ ዙሪያ የሚነሱ ወሬዎችን እና አሉባልታዎች ወደ ጎን በመተው እንዲከተቡ ጥሪ አቅረበዋል። በመጨረሻም መረጃዎችን ከሚታመኑ ምንጮች ብቻ እንዲወስዱ እና ሁሉንም የኮቪድ -19 መከላከያ መንገዶች እንዲከተሉ አሳስበዋል።

አስተያየት