"ሁሌም የቴዎድሮስን የመቅደላ ስንብት ቀን ስናስብ የንጉሠ ነገሥቱ ሀገራዊ የአንድነትና የሥልጣኔ ህልሞች ተሳኩ ወይ ብለን መጠየቅ አለብን" የታሪክ መምህሩና ተመራማሪው ረ/ኘሮፌሰር ግርማ ታያቸው።
ዳግማዊ አፄ ቴዎደሮስ በኢትዮጵያ ታሪክ ገናና ስም ካላቸው ነገሥት መካከል አንዱ ናቸው። በመሳፍንቱ በእኔ እበልጥ አንተ ታንስ ፉክክር ተከፋፍላ የነበረችው ኢትዮጵያ ጠንካራ ማእከላዊ መንግሥት እንዲኖራት ባደረጉት ከፍ ያለ ጥረት ይታወቃሉ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከቋራ እስከ መቅደላ ለሐገር አንድነትና ሥልጣኔ ሲባክኑ ያሳለፉት እድሜ የተቋጨው ከ153 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ነበር፡፡
ዘመናዊት ኢትዮጵያን፣ በሕብረቷ አንድነቷን ያስመሰከረች ኢትዮጵያን የማየት ህልማቸው ሳይሳካ በወርሃ ሚያዝያ 6ኛ ቀን መቅደላ አምባ ላይ ወደማይቀርበት ሄደዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በተቀሰቀሰባቸው ተቃውሞ የእንግሊዝን ጦር ተፋልመው በ1860 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ክብር ራሳቸውን ሰውተዋል፡፡
"ካሳ ካሳ - የቋራው አንበሳ!"
ካሳ ኃይሉ (አፄ ቴዎድሮስ) በ1811 ዓ.ም. አባታቸው ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ በሚያስተዳድሩት ቋራ ተወለዱ፡፡ እናታቸው ወይዘሮ አትጠገብ ናቸው፡፡ በሱዳኖች እና በግብጾች ተደጋጋሚ ወረራ ይደርስበት የነበረው ቋራ በምዕራብ ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡
አጎታቸው ዳጃዝማት ክንፋን አኩርፈው የሸፈተቱት የያኔው ካሳ የኋላው ቴዎድሮስ ለሀገራዊ ህልማቸው መነሻ የሆነ ክስተት የገጠማቸው ቋራ ነበር። ወጣቱ ካሳ ኃይሉ የመጀመሪያውን በዘመናዊ ጦር መሳሪያ የታገዘ ውጊያ ያካሄደው በዚህ ቦታ በደጃዝማችነቱ ወራት ነበር፡፡
ደባርቅ ላይ ሰፍሮ የነበረውን በሙሃመድ አሊ የሚመራ የግብጽ ወራሪ ኃይል ለማጥቃት ከ16,000 ሠራዊት ጋር መጋቢት 1840 ዓ.ም. ላይ ዘመተ፡፡ ምንም እንኳ የርሱ ኃይሎች ብዛት ከግብጾቹ ቢልቅም፣ በግብጾቹ የዘመናዊ ጦርመሳሪያና አመራር ብልጫ ምክንያት ተሸነፈ፡፡ ክስተቱ ደጃዝማች ካሳን በእጅጉ ያስደነቀ ኩነት ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍሯል፡፡
ከዚህ በኋላ ደጃች ካሳ ዘመናዊ ጦር መሳሪያን ለማግኘትና ዘመናዊ የጦር ስልትን ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት አደረበት። ይህ አጋጣሚ በስርአት የሚመራ፣ የሰለጠነ ዘመናዊ ሰራዊት አስፈላጊነትን እንዲያውጠነጥን ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
"ዳኘን ዳኘን - አንድ ህልም ዐሳየን!"
በጎንደር ዩንቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪው ረደት ኘሮፌሰር ግርማ ታየቸው "የቴዎድሮስ ህልም ሀገራዊ አንድነትን የሚጠብቅ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት መፍጠር እና ሀገርን ማዘመን ነው" ይላሉ። የአፄው መነሻና መድረሻ የሀገሪቱን አንድነት መጠበቅና ሀገሪቱን የማሰልጠን ጉዞ መሆኑን ይገልፃሉ።
የቴዎድሮስ መነሳት የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ጅማሬ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ያመጧቸው ለውጦች ስለመሆናቸው ብዙዎች ይስማማሉ። የወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ ንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መሳፍንትን ለማጥፋት እንዲነሳሱ አደረገ። በጊዜው የነበረው የእንግሊዙ ‘ቆንጽላ’ ‘ዋልተር ፕላውዴን’ ንጉሠ ነገሥቱ የኢትዮጵያን ቀደምት ታላቅነት ለመመለስ ዋና አላማ እንዳላቸው ሳይመዘግብ አላለፈም፡፡ በ’ፕላውዴን’ አስተሳሰብ ይህ የንጉሡ ተቀዳሚ ዓላማ ነበር።
ከዚህ አንጻር የቴዎድሮስ የንግሥና መጀመሪያ ዓመታት በብሄራዊ ፍትሕ፣ ርህራሄና የደሃ አደጎችን ህይወት በማሻሻል ላይ ያተኮረ ነበር። እንደ ረ/ኘሮፌሰር ግርማ ገለፃ ማዕከላዊ መንግሥት ያላትና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን የመፍጠር ህልማቸው ተሳክቷል።
በተለይ ለዓድዋ ድል መገኘት እርሾ የሆነው ብሔራዊ ስሜት መሰረቱ የተጣለው በእርሳቸው ነው። በሌላ በኩል ዘመናዊና የሰለጠነች ሀገርን በመፍጠር ሀገራዊ ክብርን የመቀዳጀት ውጥናቸው እስካሁን እንዳልተሳካ ይናገራሉ።
"በጎሳ ፓለቲካ ብዙ የተፈተነችው ኢትዮጵያ አሁንም የአንድነትና የመሰልጠን ህልምን ከቴዎድሮስ ወስዳ ልትጠቀምበት ይገባል" ባይ ናቸው።
‹‹የቴዎድሮስን ህልም ፍለጋ!›› የጎንደር ዩንቨርሲቲ ከባለድርሻዎች ጋር በመሆን ደግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መስዋዕት የሆኑበትን 150ኛ ዓመት በብሔራዊ ደረጃ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አስቧል። በዚህ ዝግጅት አነሳሽነትም ከመቅደላ የተዘረፋ ቅርሶችን የሚያስመልስ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር። በመሀል የንጉሠ ነገሥቱ ሹርባ (ቁንዳላ) እንዲመለስ መደረጉ ይታወሳል።
በመነሻቸው ቋራ የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል። ከቋራ አስከ መቅደላ ቴዎድሮስ በተጓዙባቸው ታሪካዊ ስፍራዎች ጉዞ በማድረግ አካባቢዎቹ ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ ተሞክሯል። የዚህ የቴዎድሮስን ህልም የመፈለግና የመኖር ንቅናቄ አካል የሆነ ኘሮጀክት ደግሞ ከሰሞኑ ይፋ ተደርጓል፡፡
ጎንደር ዩንቨርሲቲ የአጼ ቴዎድሮስን የታሪክ አሻራ ስፍራዎች በመጠበቅና በመንከባከብ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል የ5 ዓመት የልማት ፕሮጀክት አዘጋጅቶ የኘሮጀክት ማስተዋወቂያ መርሀግብር አካሂዷል። የታሪክና የቱሪዝም ምሁራን፣ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰዎችና የሕብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት ይፋ የተደረገው ኘሮጀክት ለ8ሺህ ወገኖች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶበታል።
“የቋራ መቅደላ ማኅበረሰብ አቀፍ ኢኮ-ቱሪዝም” በሚል ስያሜ የሚተገበረው ኘሮጀክቱ ከአጼ ቴዎድሮስ የትውልድ ስፍራ ቋራ መስዋዕት እስከሆኑበት መቅደላ አምባ ድረስ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የሚያስችል ነው ተብሏል።
ቋራን፣ ደረስጌ ማርያምን፣ ጋፋትን፣ መቅደላን ያካተተው ፕሮጀክቱ የአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ አሻራ የሆኑትን ቅርሶች በመጠበቅና በመንከባከብ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ዓላማ ያደረገ ነው።