ሚያዝያ 8 ፣ 2013

የኮሮና ቫይረስ እና የከተሞች እንቅስቃሴ

ኮቪድ 19ወቅታዊ ጉዳዮች

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የኮሮና ቫይረስ ለ3,285 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

የኮሮና ቫይረስ እና የከተሞች እንቅስቃሴ

በአንድ ጃፓናዊ የ48 ዓመት ጎልማሳ አማካኝነት ከአንድ ዓመት በፊት የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኮሮና ቫይረስ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ ለ3,285 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ገባ በተባለበት ወቅት ሰዎች ያደርጉት የነበረው አይነት ጥንቃቄ አሁን ላይ ላለመኖሩ አስረጂ ከሚሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ ቅናሽ እየታየበት ሳይሆን እየጨመረ መምጣቱ ነው።

በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት ላይ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት መመሪያ ቁጥር 30 ቢወጣም የአተገባበሩ ሁኔታ ግን በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ከጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ጀምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትም ጭምር በተደጋጋሚ ተናግረዋል፤ በመናገር ላይም ይገኛሉ።

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል መደረግ ያለበት ጥንቃቄ በምን ያህል መጠን እየተተገበረ ነው ስንል የየከተማዎቹን ነዋሪዎች አነጋግረናል።

ከአዲስ አበባ 279 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሐዋሳ ከተማ የጥንቃቄ ጉድለት ያለው በኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን በሕግ አስከባሪዎችም ጭምር እንደሆነ የከተማው ነዋሪ ቢኒያም ታደሰ ይናገራል። እንደ ቢኒያም ገለጻ ከሆነ ሁሉም ባይሆኑ የተወሰኑት የሕግ አስከባሪዎች ያለ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ተሰባስበው መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

የሕግ አስከባሪ አካላት ያላከበሩትን ሕግ ሌላው ዜጋ ሊያከብረው ያዳግታል የሚለው ቢኒያም ሕግ አስከባሪዎች አርአያ ከመሆናቸው እና ሌላውን ለማስተካከል ካላቸው ኃላፊነት አንፃር አነሳሁት እንጂ የኅብረተሰቡ ችግር የጎላ ነው ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። እንደ እርሱ አገላለጽ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የግንዛቤው እጥረት ከፍተኛ ሲሆን በተለይም ወጣት እና ተምሯል ተብሎ የሚታሰበው ላይ ይጎላል።

የኮቪድ መከላከያ መንገዶችን እምብዛም የማትጠቀመውና በሻሸመኔ ከተማ የመጀመሪያ ድግሪዋን በማኔጅመንት እየተከታተለች የምትገኘው የምስራች ኤርሚያስ በበኩሏ ሻሸመኔ የንግድ ከተማ በመሆኗ የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያዎችን መተግበር አስቸጋሪ እንደሆነ ትናገራለች።

የምስራች በምትማርበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋምና በባንኮች  ሕጉ በተነፃፃሪነት ተግባራዊ ይደረጋል የምትለው የምስራች በትራንስፖርት ቦታ ላይ ግን ትራፊክ ካለ ብቻ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ተግባር ላይ እንደሚውል ገልጻለች።

"አብዛኛው ሰው ጭምብሉን አያደርግም ቁጥጥርም አይደረግም፤ መመሪያው ቢተገበር ጥሩ ነው ነገር ግን አኗኗራችን አያመችም። በሽታውን በተወሰነ ለመከላከል ብቸኛው አማራጭ በቤት ውስጥ መቀመጥ ይመስለኛል። ዋነኛው መፍትሄ ግን ከፈጣሪ ነው" ስትል የምስራች ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።

ሌላኛዋ በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ኤደን ዘርፉ የምስራችን ሃሳብ ትጋራለች። በደብረብርሃን ከተማ መመሪያውን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ፣ ከኅብረተሰቡ ጋር ለመመሳሰል እና ጭምብል ሳይደረግ ያለውን ነፃነት ለማግኘት በሚል የማያደርገው ሰው ቁጥር ቀላል እንዳልሆነና እርሷም ይህ ችግር እንዳለባት ነግራናለች።

"መመሪያው ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ተግባራዊ አይደረግም" ያለው ሌላኛው ከደብረማርቆስ 15 ኪ.ሜ ጉዞ በኋላ በምትገኘው ፈንድቃ ከተማ ውስጥ የሚኖረው ሳሙኤል ዋጋው ነው። ከተማዋ ትንሽ በመሆኗና ነዋሪውም ያን ያህል ወደ ሌሎች ከተሞች ስለማይንቀሳቀስ ፈንድቃ ውስጥ ኮሮና የለም ይላል። እንደ ሳሙኤል ገለጻ ከሆነ በሚኖርበት ከተማ በቫይረሱ የተያዘ ሰው እንዳለ ሰምቶ ባለማወቁ እዚህ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ የሚኖረውና የሕክምና ባለሙያ የሆነው ስሜን አትጥቀሱብኝ ያለ አንድ የሕክምና ባለሙያ እንደነገረን ከሆነ ደግሞ በቀብሪደሃር አካባቢ የሚኖረው አብዛኛው ማኅበረሰብ በሽታው የለም ብሎ ያምናል፤ ነገር ግን በኮቪድ የተያዘ ሰው ናሙና አለመኖር ለበሽታው መጥፋት ማረጋገጫ አይሆንም ሲል ይናገራል።

እንደ ሕክምና ባለሙያው ገለጻ የመመርመሪያ መሳሪያ ያለው በውስን ቦታ ስለሆነ ምልክት አሳይቷል ተብሎ የተጠረጠረ ሰው የሚታከመው በግምት በመሆኑ በይፋ በሽታው አለባችሁ ያልተባሉ እና የሞቱ ሰዎች ያልተገለፁባቸው ቦታዎች ከበሽታው ነፃ ናቸው ለማለት አያስችልም ይላሉ። የህክምና ባለሙያው እንደነገሩን ቀብሪደሃር ያለው አኗኗር (ከፍተኛ ሙቀት) መመሪያዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ቢከብድም ሙሉ በሙሉ መተው ግን መፍትሄ አይሆንም።

ሌላኛው በድሬደዋ ከተማ በሹፍርና ስራ ላይ የተሰማራው ወንድወሰን መልካሙ እንደ ቀብሪደሃሩ የሕክምና ባለሙያ ሁሉ በከተማዋ ከአየር ንብረት ሙቀት ጋር ተያይዞ  ጭምብል ማድረግ እንደሚከብድ ይናገራል። "እኛም ኅብረተሰቡም ከትራፊክ ቅጣት ለመዳን ነው መኪና ውስጥ ጭምብል የምናደርገው። ከእነርሱ ዕይታ ከራቅን በኃላ ግን እናወልቃለን" የሚለው ወንድወሰን ከመዘናጋት እና ከሙቀቱ የተነሣ ቸልተኝነት መፈጠሩን ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

"በድሬዳዋ ትራንስፖርት የሚገኘው በወረፋ (በሠልፍ) በመጠበቅ ስላልሆነ አካላዊ ርቀት መጠበቅ አልተቻለም፤ የሕግ አስከባሪ አካላት ቁጥጥርም ቢሆን ወጥ አይደለም፤ እራሳቸውም ጭምር ሕጉን አያከብሩትም" ሲል ወንድወሰን ነግሮናል። "ለእኔ መዘናጋትም ሆነ ለሁሉም መፍትሄ የሚሆነው አንድ ጊዜ ብቻ የሚደረግ ክትትል ሳይሆን ያልተቆራረጠ አሠራር ቢኖር ጥሩ ነው" ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

"ስለ ኮቪድ ጨርሶ አይታሰብም፤ የህክምና ተቋማትም ለዚህ በሽታ ህክምና እየሠጡ አይደለም" ያለችው የሽረ ከተማ ነዋሪ ሜላት ፋንታሁን ስትሆን በከተማዋ የስደተኞች እንቅስቃሴ በመኖሩና ስደተኞች ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ግብዓቶችን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት  ውስጥ ነዋሪውም ተሳታፊ በመሆኑ በሽታውን ለአፍታ እንኳን ለማስታወስ የሚቻልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም ስትል ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።

በመመሪያ 30 አተገባበርና በተቀናጀ ስራ አስፈላጊነት ላይ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፡ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ ኮቪድ-19 የሚያደርሰው ጉዳት እየከፋ በመምጣቱ ለህግ ማስከበሩ በጋራ ልንቆም ይገባል ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የኮቪድ-19 መስፋፋትና የአደጋው መብዛት የብዙዎችን ህይወት ከመቅጠፉ ሌላ ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት ለሚመጡ ሰዎች የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ ለመስጠት የማንችልበት ደረጃ ላይ እየደረስን ነው ያሉት ወ/ሮ አለምፀሃይ መመሪያ 30 ከወጣ የቆየ ቢሆንም በኅብረተሰቡ መዘናጋት ምክንያት ችግሩ እየተባባሰ በመሄዱ የህግ አማራጮችን ተጠቅሞ ህብረተሰቡን ከወረርሽኙ መታደግ አማራጭ የለውም ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው መመሪያ 30 በመላው ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን መመሪያውን ተላልፎ የተገኘ ሁሉ እንደሚቀጣ ይገልጻል።

አስተያየት