ሚያዝያ 13 ፣ 2013

የካርድ አውጡ እና ካርድ አልቋል ተቃርኖ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

አዲስ አበባ ካሏት 1ሺህ 848 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ምዝገባ ማካሄድ የጀመሩት 1ሺህ 662 ብቻ መሆናቸውን ከ5 ቀናት በፊት የወጣ መረጃ ያመለክታል፡፡

የካርድ አውጡ እና ካርድ አልቋል ተቃርኖ

አዲስ አበባ ካሏት 1ሺህ 848 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ምዝገባ ማካሄድ የጀመሩት 1ሺህ 662 ብቻ መሆናቸውን ከ5 ቀናት በፊት የወጣ መረጃ ያመለክታል፡፡ በአጠቃላይ ሐገሪቱ ካሉት 50ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ግማሽ ያህሉ ማለትም 25 ሺህ 151 ምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር የመራጮች ምዝገባ ማካሄድ ያልጀመሩትን ሶማሌ እና አፋር ክልሎችን የሚጨምር ነው፡፡

ጥቂት በማይባሉ የአዲስ አበባ ከተሞች ደግሞ ተቃራኒ ሐሳቦች ተሰምተዋል፡፡ የመጀመሪያው መራጩ ሕዝብ በሚያስፈልግ መጠን የምርጫ ካርድ አለመውሰዱን የሚገልጸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የምርጫ ጣቢያዎች ካርድ ጨርሰዋል የሚሉት ናቸው፡፡

image.png

የመራጭነት ማረጋገጫ የሆነው፣ መራጮች መመዝገባቸውን የሚያረጋግጡበትና ለመምረጥ የሚያስችላቸው ካርድ ማለቁ ከተነገረባቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች መካከል የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አንዱ ነው፡፡ በክፍለ ከተማው የካ-አባዶ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የሚገኙ 4 የምርጫ ጣቢያዎች ካርድ መጨረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ዋጋዬ ጥሩነህ ‹‹አዳማ ቁጥር 2›› እና ‹‹13›› ተብለው የሚጠሩ አካባቢዎች ላይ ካርድ ማውጣት አልቻሉም፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት እና ከሦስት ቀናት በፊት ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ ቢያመሩም ካርድ አልቋል በመባላቸው ምክንያት ካርድ ማውጣት እንዳልቻሉ የሚናገሩት ወ/ሮ ዋጋዬ ‹‹በአንድ በኩል ምርጫ ካርድ ውሰዱ ይላሉ፤ በሌላ በኩል ካርድ አልቋል ይሉናል፤ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው›› ብለዋል፡፡

በአከባቢው የልማት ኮሚቴ የሆኑት እና ‘’ሕብረተሠቡ ካርድ እንዲያወጣ በመቀስቀስ እናስተባብራለን’’ የሚሉት አቶ ከፍያለው ደርቤ እርሳቸው ባሉበት አከባቢ ካርድ ካለቀ 3 ቀናት አልፈዋል ያሉ ሲሆን "እስከ ወረዳ ድረስ እየተጉላላን ነው፡፡ ምንድንነው ችግሩ ብዬ ጠይቄያለሁ መፍትሄ የሚገኘው ከምርጫ ቦርድ እንደሆነ እና "ካርዱ ከተጨመረልን ይመጣል ጠብቁ" የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

"መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን ይህንን ሀሳብ በምናገርበት ሰዓት እንኳን 5 ሰዎች አገልግሎቱን ሳያገኙ ተመልሰዋል" ሲሉ በስልክ የሰጡንን ሐሳብ ደምድመዋል፡፡

በ6ኛው ሐገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የፊታችን አርብ ሚያዝያ 15 የሚጠናቀቀው የመራጮች ምዝገባ እጥረት ላጋጠማቸው አካባቢዎች ድጋፍ እንዲሆኑ አዳዲስ ንዑስ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ሚያዝያ 11 ባወጣው መግለጫ በቀደሙት ጣቢያዎች አቅራቢያ አዳዲስ ጣቢያዎች ይከፈታሉ፡፡ በመመሪያው መሰረት አንድ ምርጫ ጣቢያ መመዝግብ የሚችለው 1ሺህ 500 መራጮችን ብቻ ነው፡፡

አስተያየት