በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄድ ከጀመሩ ሦስተኛ ቀን ተቆጥሯል፡፡ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ወልድያ፣ እንጅባራ እና ባህርዳር በርካታ ሕዝብ አደባባይ ከወጣባቸው የክልሉ ከተሞች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የጀመረው ዓመጽ በባህርዳር ከተማም ቀጥሏል፡፡ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ያልነበረበት፣ በርካታ ሰዎች አደባባይ የወጡበት ተቃውሞ ዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ የትላንት ሐሙስ የሦስተኛ ቀን የባህርዳር ከተማ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ እንደምን ውሎ እንዳመሸ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከባህርዳር ያስቃኘናል፡፡
ትላንት ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የባህርዳር አገልግሎት ሰጪዎች ዝግ ሆነው የዋሉበት ነው፡፡ ከመድሃኒት ቤቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ የግል ሱቆች እና አገልግሎት ሰጪዎች በራቸውን ለተገልጋይ አልከፈቱም፡፡ በከተማዋ መንገዶች የአማራ ልዩ ኃይል እና የፖሊስ ተሽርካሪዎች መንደሮችን እየቃኙ ሲመላለሱ ታይተዋል፡፡
እንዳለፉት ሁለት ቀናት ሁሉ ሰልፉ የተጀመረው ከ‹‹ፓፒረስ›› ሆቴል አካባቢ ነው፡፡ ማለዳ ሦስት ሰዓት የጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ጊዮርጊስ አደባባይ እየተንቀሳቀሱ ተቃውሞ በሚያሰሙ የማኀበረሰብ ክልሎች ተሞልቷል፡፡ ከዚህ ቀን በፊት ተቃውሞውን በይፋ ያልተቀላቀሉት የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ተማሪዎችም የሰልፉ አካል ሆነዋል፡፡ ‹‹ፔዳ›› ተብሎ ከሚጠራው ከዩንቨርሲቲው ግቢ ተነስተው ወደ ፓፒረስ በማቅናት ተቃውሞውን የደገፉት ተማሪዎች የተጻፉ መልእክቶችን በማሳየት እና መፈክር በማሰማት ሰልፈኞችን ተቀላቅለዋል።
የተቃውሞው "በቃን" በሚል መፈክር የታጀበ ነው፡፡ በማንነታቸው ምክንያት ለሞት እየተዳረጉ ያሉ ዜጎችን ሰቆቃ መስማት ይብቃን የሚሉ ድምጾች በአያሌው ተደምጠዋል፡፡ "የፌዴራል መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ያስጠብቅ፣ የአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ ነው" የሚሉት መፈክሮችም በብዛት ከተደመጡት መካከል ናቸው፡፡
በሺዎች የሚቆጠር የከተማዋ ነዋሪ የተሳተፈበት የተቃውሞ ሰልፉ የማኅበራዊ ሚድያውም ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ውሏል፡፡ ሰዎች በሚጠቀሟቸው ማኅበራዊ ድረ-ገጾች ውሏቸውን፣ የሚገኙበትን ሁኔታ እና ሐሳባቸውን አስፍረዋል፡፡
ሐሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ የገለጹትን ሰልፈኞች በተመለከተ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ሳይቀር "ሞት በቃ ለማለት ሳር አንኳን ሳይረግጥ በሰላም ሀሳቡን መግለጹ ተቀባይነት ያለው ነው" ሲሉ የሕዝቡን ጨዋነት አድንቀዋል፡፡
ጥዋት ሦስት ሰዓት አካባቢ የጀመረው ሰልፍ በአደባባዮች እና በዋና ዋና ጎዳናዎች ተካሂዷል፡፡ በየመሐሉ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበረም የዐይን እማኞች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡ በተኩሱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት የሰልፉ ተሳታፊ የነበሩ እማኞች እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ አልፎ አልፎ የሚሰማ የተኩስ ድምጽ ነበር ብለዋል፡፡ የዐይን እማኞች ይህንን ቢሉም ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ በሰልፉ ምክንያት የተጎዳ ሰው ስለመኖሩ ከታወቀ አካል የተባለ ነበር የለም፡፡
ሰዓታት እየገፉ ሲመጡ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ምልክቶች ዕየታዩበት የመጣው ሰላማዊ ሰልፉ በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝብ መተላለፊያ መንገዶችን በድንጋይ በመዝጋት፣ የአስፋልት መንገድ አካፋዮችን በመንቀል፣ ጎማ በማቃጠል እና በመሳሰሉት መንገዶች ቀጥሎ ሲውል የኦሮምያ ኢንተርናሽናል ባንክ ጣና ቅርንጫፍ ሕንጻ የፊትለፊት መስታወት በሰልፈኞቹ መሰበሩን የዚህ ዘገባ አዘጋጅ ተመልክቷል፡፡
የባህርዳር ከተማ ሰላማዊ ሰልፈኞች ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ በአብዛኛው ወደመጡበት ተመልሰዋል፡፡ መደበኛ እንቅስቃሴአቸውንም ጀምረዋል፡፡ ባህርዳርን አቋርጠው የሚጓዙ ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችም ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡
ማምሻውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር የክልሉን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በሰልፍ እና አመጹ የመንግሥት መዋቅሩ ተሳታፊ ነበር ካሉ በኋላ ይህ ሁሉ ውድመት ሲከሰት የጸጥታ ኃይላችን የት ነበር? የመረጃ እና የደሕንነት መዋቅራችን የት ነበር? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የሚገባውን እንዳልሰራ በተነገረው መዋቅር ዙርያ ማጣራት እየተደረገ ስለመሆኑም አቶ አገኘሁ ተናግረዋል፡፡