ሚያዝያ 15 ፣ 2013

"ክፍያ ካልተፈፀመልን የመራጮች መዝገብን አናስረክብም" - የምርጫ አስፈጻሚዎች

ምርጫ 2013ዜናዎች

የምርጫ አስፈጻሚዎች ክፍያ እንዳልተከፈላቸው እየገለፁ ነው።

"ክፍያ ካልተፈፀመልን የመራጮች መዝገብን አናስረክብም" - የምርጫ አስፈጻሚዎች

የምርጫ አስፈጻሚዎች ከምርጫ ቦርድ ጋር በገቡት ውል መሰረት በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ ክፍያ ካልተፈፀመልን ለ1 ወር ያህል መራጮች ሲመዘገቡበት የነበረውን መዝገብ ለምርጫ ቦርድ እንደማያስረክቡ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ-ከተማ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ የሚሰሩ የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደነገሩን ከሆነ "በስምምነታችን መሰረት ክፍያ እንዲፈፀምልን በተደጋጋሚ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ብናቀርብም ተፈፃሚ አልሆነም፤ ስለዚህ ይህንን አማራጭ ለመውሰድ እንገደዳለን" ብለዋል።

የመራጮች ምዝገባ በተገባደደ በ10 ቀን ውስጥ የአከባቢው የወረዳ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት እና የምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት የሚከናወነው የመዝገብ ርክክብ “የስራችንን ክፈሉን" ጥያቄ ሳይመለስ ተግባራዊ እንደማይሆን የሚናገሩት የምርጫ አስፈጻሚዎች "አሁን የተፈጠረው የምርጫ ቦርድ አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት ተጨምሮ ርክክቡ ከተከናወነ በኃላ ሙሉ በሙሉ ክፍያው ሳይፈፀም ቢቀርስ የሚል ስጋት እንዳላቸው” ለአዲስ ዘይቤ አስታውቀዋል።

ይህንን ስጋታችንን ያናረውና በምርጫ ቦርድ ዕምነት እንድናጣ ያደረገን አንዱ ጉዳይ “የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ አስቀድሞ በነበረ የ2 ቀን ስልጠና ወቅት ሊከፈለን የሚገባው አበል ወዲያውኑ እጅ በእጅ ይደረጋል ከተባለ በኋላ ለአንድ ወር ቆይቶ ከ3 ቀናት በፊት ለግማሽ ያህክል ተሳታፊዎች ብቻ መሰጠቱ ነው” ሲሉ አማረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት (ሚያዝያ 15) ከ5 ሺህ የአዲስ አበባ የምርጫ አስፈፃሚዎች ውስጥ ለ1444 ያህሉ አስፈጻሚዎች ከአጠቃላይ ክፍያ ውስጥ የመጀመሪያውን ዙር ማለትም 15 በመቶ (ከመጋቢት 16 እስከ መጋቢት 23 ቀን የሰሩበትን የ7 ቀን) ክፍያ ለመፈጸም የስም ዝርዝር አውጥቷል።

የምርጫ አስፈፃሚዎቹ በወቅቱ መከፈል የነበረበትን ይህን ክፍያ 22 ቀናት ከተቆጠሩ በኃላ አሁን ላይ ይከፈላል መባሉ፣ ሙሉ በሙሉ ሁሉንም አስፈጻሚዎችን አለማካተቱ እና በዛሬው ዕለት ማግኘት ከሚገባቸው 30 በመቶ ግማሽ ያህል መሆኑ ይበልጥ ቅሬታ ውስጥ ከቶናል ብለዋል።

እስካሁን ድረስ በቀድሞው ሃሳባቸው እንደፀኑ የነገሩን የምርጫ አስፈጻሚዎች "በውላችን መሠረት ማግኘት የሚገባንን ሙሉ በሙሉ ካላገኘን መዝገብ ያለማስረከቡን ሃሳብ አናቆምም" ሲሉ ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ በስራ ገበታ ላይ የሚገኙት እና የሌሉትን የማጣራት ስራ በማከናወን መክፈል ጀምሬያለሁ፤ በቀጣይም እከፍላለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው።

በዛሬው ዕለት የሚጠናቀቀው የመራጮች ምዝገባ መራዘሙ አይቀሬ እንደሆነ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

አስተያየት