ሚያዝያ 15 ፣ 2013

ፌደራሊዝምና የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም

ምርጫ 2013ፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ በሕዝብ ድምጽ ተመርጠው ሥልጣን ከያዙ የሚመሰርቱት የፌደራሊዝም አወቃቀር ምን ይመስላል?

ፌደራሊዝምና የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም

በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ በሕዝብ ድምጽ ተመርጠው ሥልጣን ከያዙ የሚመሰርቱት የፌደራሊዝም አወቃቀር ምን እንደሚመስል ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጽያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴኅ) እና የኢትዮጽያ ነጻነት ፓርቲን አዲስ ዘይቤ አነጋግሯል።

"የፓለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መንስኤ ሕገ-መንግስቱ ነው። በተለይም አንቀፅ 8 መግቢያው ላይ ያለውን እንቀይረዋለን" የሚሉት የኅብር ኢትዮጵያ ሊቀ-መንበር ግርማ በቀለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት አገሪቱ እየተከተለች ለምትገኘው ፌደራሊዝም በቋንቋ ላይ የተዋቀረ እንዲሆን እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገሩ በእኩልነት እንዳይኖር ማድረጉን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 "የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው" ሲል ያስቀምጣል።

"ጨቋኝ ብሔረሰብ ሳይሆን ስርዓት ነው፤ ትላንት የነበረው ስርዓት እንጂ ብሔር አይደለም" የሚሉት ግርማ ሊቀ-መንበሩ በቋንቋ የተዋቀረውን ክልል መቀየር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው በምርጫ ድምፅ ካገኘ የፌደራል ስርዓቱን የሚያዋቅረው በቦታ አቀማመጥ፣ ስነ-ልቦና፣ የኢኮኖሚ ግንኙነት፣ ቋንቋ እና በዳበረው የባህል ግንኙነት መሠረት ይሆናል። በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1987 ተጠንቶ የነበረውን የመስተዳድሮች ቁጥር እንደመነሻ በመጠቀም ክፍለ አገር እንደሚያዋቅሩም ነግረውናል።

"ይህ አወቃቀር አሁን ካለው የሕዝብ ብዛት እና የተቀየሩ ሌሎች ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ ይለወጣል፤ ትክክለኛ ቁጥሩ የተወሰነ ባይሆንም ቢያንስ ግን 50 ክፍለ አገራት ይኖራሉ" የሚል ሃሳብ እንዳላቸው የፓርቲው አባል ይልቃል ጌትነት (ኢ/ር) አክለው ነግረውናል።

እነዚህ ክልልሎች ሲዋቀሩ በመላው አገሪቱ የስራ ቋንቋ አማርኛ ይሆንና በአፍ መፍቻ ቋንቋ ከ1-4ኛ ክፍል ትምህርት እንዲሰጥ ይደረጋል ይላሉ የፓርቲው ሊቀ-መንበሩ ግርማ።

"በአገሪቱ ውስጥ የፓሊስ ኃይል እና መከላከያ ብቻ እንጂ የክልል ልዩ ኃይል አይኖርም" የሚሉት ሊቀ-መንበሩ የክልል ሰንደቅ አላማ እና መዝሙር ግን ኅብረተሰቡ ከፈለገ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው የኮከብ ምልክት አይኖርም፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ብቻ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

"አሁን ያለውን ሰንደቅ አላማ ህዝቡን በማነጋገር (በአብላጫ ድምፅ) ባለበት እንዲቀጥል ወይም እንዲቀየር እናደርጋለን" ያሉት የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግዛቸው አመራ ሲሆኑ “የክልል ሰንደቅ ዓላማ ግን አያስፈልግም” በማለት ተናግረዋል።  

"ኅብረተሰቡ ይወክለኛል የሚለው ሰንደቅ ዓላማ የማድረግ ፍላጎት ቢኖረውስ?" ብለን እንደ ምሳሌ በአሜሪካ ያለውን የግዛቶች ሰንደቅ ዓላማ ጠቅሰን ላቀረብንላቸው ጥያቄ "እኛ በምናዋቅራቸው ክፍለ-አገራት ኅብረተሰቡ ከፈለገ መለያ አርማ ይኖረዋል እንጂ የክልል ሰንደቅ ዓላማ አይኖርም፤ ኢትዮጽያ አንድ አገር በመሆኗ አንድ ሰንደቅ አላማ ነው የሚኖራት እንጂ ትንንሽ አገራት እንዲኖሩ አንፈልግም። እንደ አሜሪካ ለማድረግ ገና የእነርሱ ደረጃ ላይ ስንደርስ" በማለት መልሰዋል።

የቋንቋ ፌደራሊዝም እንደማይቀበሉ ገልፀው በቦታ አቀማመጥ፣ በባህል፣ በኑሮ ዘይቤ እና በኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም እንዲኖር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

"የክፍለ-አገራቱን ቁጥር አልወሠንም በጥናት ይወሰናል" የሚሉት አቶ ግዛቸው ስያሜው ግን "ክፍለ-አገር ወይም አውራጃ" ይሆናል ብለው ለምሳሌ ያህል ሰሜን አውራጃ ወይም ደቡብ ክፍለ-አገር በማለት ጠቅሰዋል።

"በሚቋቋሙት ክፍለ-አገራት ልዩ ኃይል የማይኖር ሲሆን ተሰማርተው የሚገኙት ልዩ ኃይሎች ምን ይደረጋሉ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። እናም ወደ ፌደራል ፓሊስ ወይም መከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀሉ ይደረጋሉ" ብለዋል። በተጨማሪም በየክፍለ-አገራቱ የፓሊስ አባላት ከአንድ ክፍለ-አገር ወደ ሌላ ክፍለ-አገር በአወቃቀር እና ስርዓት በሚመራ መልኩ ሕግ ለማስከበር መንቀሳቀስ እንድሚችሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ በምርጫ ካሸነፈ ሕገ-መንግስቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይር፣ ብሔራዊ ቋንቋን አማርኛ እንደሚያደርግ፣ በየክፍለ-አገሩ የስራ ቋንቋ በአብላጫው የአካባቢው ነዋሪ የሚወሰን ሲሆን  የአፍ መፍቻ ቋንቋ በመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት አይነት የመስጠት ሃሳብ እንዳላቸው ሊቀ-መንበሩ ይናገራሉ።

“በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር እና መዳኘት መብት ነው እንዲሁም ብሄራዊ ቋንቋ ማብዛት እንፈልጋለን” የሚሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ) ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ “ቋንቋን መሠረት ያደረገ ብቻ አወቃቀር ትርጉም የለውም” ብለው ነገር ግን አሁን ያለው ፌደራሊዝም መለወጥ ካለበት የሚለወጠው በህብረተሰቡ ውሳኔ መሆን አለበት ይላሉ። 

“ፓርቲው አሁን በተዋቀረው የክልል አደረጃጀት ተከትሎ በውስጡ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ይጥራል እንጂ አዲስ አወቃቀር አይዘረጋም” ያሉት ሊቀ-መንበሩ “የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሰው ወደዚህ ክልል ግባ ተብሎ ያለበትን መሬት ወደተለያየ አቅጣጫ ከመከፋፈል ባለበት ቦታ በእራሱ ቋንቋ እንዲማር እና እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

“የኢትዮጽያ የአስተዳደር ሁኔታ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ይዋቀራል” ያሉት የኢዴህ ሊቀ-መንበር “ኢትዮጽያ ቋሚ ሰንደቅ ዓላማ አልነበራትም የሚደረጉት አርማዎች የፓርቲ ናቸው” ካሉ በኋላ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከፓርቲ የተለየ መሆን እንደሚገባው ይህም በህብረተሰቡ ፍላጎት የሚወሰን መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲያቸው በሚኖረው የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ "ልዩ ኃይል አይኖርም" የሚሉት ሊቀ-መንበሩ እንደ አጠቃላይ ግን ብሔራዊ መግባባት ይቀድማል ውሳኔውም የህዝብ ይሆናል ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ገልጸዋል።

ነገርግን ፓርቲው "አገሪቱን በፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ከዳር እስከዳር ችግር ውስጥ የሚከት ጎጂ ሃሳቦችን አይቀበልም" ሲሉ አክለዋል።

አስተያየት