ሚያዝያ 26 ፣ 2013

“ምርጫ ቦርድ የማሸጊያ ቁሳቁስ ጭማሪ ባለማድረጉ የምርጫ ጣቢያ ዘግተናል” - የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ

ምርጫ 2013ወቅታዊ ጉዳዮች

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ የሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ማሸጊያ ቁሳቁስ በማለቁ የምርጫ ጣቢያው እንደተዘጋ የጣቢያው የምርጫ ኃላፊ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

“ምርጫ ቦርድ የማሸጊያ ቁሳቁስ ጭማሪ ባለማድረጉ የምርጫ ጣቢያ ዘግተናል” - የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ የሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ማሸጊያ ቁሳቁስ በማለቁ የምርጫ ጣቢያው እንደተዘጋ ስሜን አትጥቀሱ ያሉ የጣቢያው የምርጫ ኃላፊ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ጣቢያው ከተዘጋ ከ5 ቀን በላይ እንደሆነው የነገሩን ኃላፊዋ አስቀድሞ የተመደበው ቁሳቁስ ለ30 ቀናት ብቻ የሚያገለግል በመሆኑ የመራጮች ምዝገባ መራዘም እጥረት ፈጥሮብናል ብለዋል።

የመራጮች ምዝገባ ከተራዘመበት ዕለት ጀምሮ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ለማቀረብ ጥረት አድርገው ምላሽ ለማግኘት መቸገራቸውንም አክለዋል። "ብሉ ቦክስ" ተብሎ የሚጠራው ሳጥን የመራጮች ካርድ፣ መዝገብ፣ ማህተም እና የመሳሰሉትን ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች የሚቀመጡበት ሲሆን የሚታሸገውም ለዚሁ በተዘጋጀ ቁስ ነው።

“ከምርጫ ጣቢያ ለምሳም ሆነ ጨርሰን ስንወጣ በተዘጋጀው ቁስ እያሸግን እና ስንመለስ እየቀደድን ነው የምንጠቀመው። አንድ ብሉ ቦክስ 4 የማሸጊያ ቁስ ያስፈልገዋል ስለዚህ በቀን 8 እንጠቀማለን፤ የተሰጠን ደግሞ ለ1 ወር የሚያገለግል 240 ቁሳቁስ ነበር” ሲሉ የነገሩን ኃላፊዋ “ሚያዝያ 20 ቀን አራት ብቻ ሲቀር አሽገው እና ጣቢያውን ዘግተው መውጣታቸውን ይናገራሉ።

በምርጫ ጣቢያው ከ1500 የመራጭ ካርዶች ውስጥ 100 ያህል መቅረቱን ገልፀው ነገር ግን ለእያንዳንዱ የማሸጊያ ቁስ ቅፅ ሞልተው በኃላፊነት መስራት ስለሚገባቸው እንዲሁም ስርቆት ቢፈፀም ተጠያቂ በመሆናቸው ስራውን ለመቀጠል አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

"የመራጮች ምዝገባ ላይ የቀናት ጭማሪ መደረጉን እንደማንኛውም ሰው ከመገናኛ ብዙኃን ነው የሠማሁት" ያሉት የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ “የስራ ውል ሳይታደስ (ሳይራዘም) ስራውን መቀጠላቸውን” ተናግረዋል።

“ከምርጫ ቦርድ አካላት ጋር የቀጥታ ግንኙነት የለንም፤ ችግሩን ለመናገር ስንደውልም አያነሱም” በማለት የአካባቢው ወረዳ የተሻለ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን እና ጣቢያው እንዲከፈትም ከወረዳው ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል።

“የምርጫ ጣቢያውን ሚያዚያ 26 ቀን ቢከፈትም አስፈላጊው ግብዓት እስካልተሰጠን ድረስ ምዝገባ ለማካሄድ እንቸገራለን” ሲሉ ኃላፊዋ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ የምርጫ ክልል ውስጥ የመረጃ አስተባባሪ በበኩላቸው የመራጮች ምዝገባ ከተራዘመ በኋላ በቂ የማሸጊያ ቁሳቁስ ከምርጫ ቦርድ መረከባቸውን እና ማከፋፈላቸውን ይናገራሉ። ከሚያዝያ 20 ጀምሮ ማሸጊያ ማለቁን ላሳወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ቦታው ድረስ በመሄድ በማረጋገጥ እያከፋፈሉ እንደሚገኙ ገልፀው “አንድም ጣቢያ ጠይቆ ያልተሟላለት የለም” ብለዋል።

የተራዘመው የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ 3 የስራ ቀናት ብቻ ይቀሩታል።

አስተያየት