የኮቪድ 19 ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባቱ በይፋ ከተነገረበት ሚያዚያ 04፤ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በማሻቀብ ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ሕበረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ከሆነ ይህ ጽሁፍ እሰከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ2,599,462 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎ 260,139 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸዉ የተረጋገጠ ሲሆን 3,795 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸዉ አልፏል፡፡ የኮቪድ ወረርሽኝ እያስከተለ ካለዉ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የጤና ጉዳት በተጨማሪ ለተለያዩ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡
የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ዉስጥ በማስገባት በከተሞች መስፋፋት እና ሙያዊነት ላይ ትኩረቷን ያደረገችዉ አዲስ ዘይቤ ዲጂታል የዜና አውታር በስድሰተኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኮቪድ-19 ስርጭትን እና በወረርሽኙ ሳቢያ የተከሰቱ ተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታት እና በመቆጣጠር ላይ ያላቸውን እቅድ ለህዝብ የሚያስተዋዉቁበትን መድረክ ለመፍጠር ያለመ ክርክር ግንቦት 03፤ 2013 ዓ.ም. በሳፋየር አዲስ ሆቴል ማዘጋጀቷ ይታወቃል፡፡
በዚህም በ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ተሳታፊ ለሆኑት ፡ የብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ማሕበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ ሕብር ኢትዮጵያ፣ ባልደራስ ለእዉነተኛ ዴሞክራሲ እና እናት ፓርቲ በክርክር መድረኩ ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ የቀረበላቸዉ ሲሆን ሕብር ኢትዮጵያ፣ የብልጽግና ፓርቲ እና ባልደራስ ለእዉነተኛ ዴሞክራሲ ግብዣዉን ተቀብለዋል፡፡ ነገር ግን እናት ፓርቲ በፕሮግራም መደራረብ ምከንያት ግብዣዉን መቀበል አለመቻሉን የገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ማሕበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ኮቪድ 19ን በሚመለከት ያዘጋጀነዉ ፕሮግራም የለም በተጨማሪም ለክርክር የተመረጠዉ ጥያቄ ለገዢዉ ፓርቲ ያደላ እና ገዢዉ ፓርቲን የሚጠቅም ነው በማለት ግብዣዉን ዉድቅ አድርጓል፡፡