ሰኔ 5 ፣ 2010

የሁለት ጥበባት ወግ፡ “እመነኝ” እና “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ”

ኑሮሙዚቃ

እንደ መግቢያእንደሚታወቀው አንዳንድ ፊልሞች ማጀቢያ ሙዚቃዎች (soundtracks) አሏቸው፡፡ የናቲ ማን (ናትናኤል አያሌው) “እመነኝ” ዜማ የፊልም…

እንደ መግቢያእንደሚታወቀው አንዳንድ ፊልሞች ማጀቢያ ሙዚቃዎች (soundtracks) አሏቸው፡፡ የናቲ ማን (ናትናኤል አያሌው) “እመነኝ” ዜማ የፊልም ሳይሆን የኢትዮጵያውያን አሳዛኝ ኑሮ (tragic life) ማጀቢያ ሙዚቃ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ይህ አሳዛኝ ኑሮ አጥንት ድረስ በሚገባ ድህነት የተሞላ፣ በዚህ ላይ ደግሞ የገዢዎች ችላ ባይነት ያጠቃው፣ ወገናዊ መተሳሰብ የራቀው እንደሆነ ሊመጸውቱን ሀገራችን ለሚመጡ ፈረንጆች “ሰር ማዳም” እያልን እናስረዳቸው ይሆናል እንጂ ማናችንንም አይጠፋም፡፡ ናቲ በ“እመነኝ” ጠንከር አድርጎ ላሳሰበን አሳዛኝ ኑሮ መፍትሔ ይሰጣሉ የተባሉት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኛ ልሂቃን፣ ባለጸጋዎችና ፊደል የቆጠሩት ወንድም ጋሼና እህት አባባ ከነልጆቻቸው  መስሚያ፣ መስማሚያ ያላቸው አይመስልም፡፡ ጥንት ነገሥታቱ በሊጋባው አንደበት አዋጅ ሲያስለፍፉ  “ስማ! ስማ! መስማሚያ ይንሣው ያድባርን ያውጋርን ጠላት….መስማሚያ ይንሣው የማርያምን ጠላት…መስማሚያ ይንሣው የጌታችንን ጠላት” ብለው  እርግማንና መረጃ ቀላቅለው ያወጡ ነበር፡፡ እኔም “እመነኝ”ን ሰምቼ እንዳበቃሁ “ስማ! ስማ! መስማሚያ ይንሣው የደሃን ጠላት” ብያለሁ፡፡  ያጎደልኩት እርግማን ካለ የዘመኑ ፕሮፌሽናል ሰባኪዎች ይሙሉበት፡፡ናቲ ማን አዲስ ካሳተመው የሙዚቃ አልበም  ውስጥ “እመነኝ”ን ካዳመጥኩ በኋላ ሥሜቴን ወጥሮ ይዞት ሥራ እስክፈታ ድረስ በነገሩ ተብሰልስያለሁ፡፡ በዚህ ዘፈን አንድ ደሀ ለልሂቁ በግልም በወልም ልመናውን ያቀርባል፤ ልሂቁን ይቆጣዋል፣ ይቆጣቸዋል፣ የሰላ ትችቱንና ትዝብቱን ይነግረዋል፣ ይነግራቸዋል፡፡ “እመነኝ” ዘፈን ከወቅቱ እውነተኛ ገጠመኝ የተቀዳ እንደመሆኑ ልሂቃኑ ደሀውን እንደማያዩ፣ እንደማይሰሙ እንረዳለን፡፡ ግን ደግሞ ልሂቅ ሁሉ ጡር የማይፈራ፣ ሰበብ እየደረደረ ችላ ባይነቱን በመደበቅ የሚመጻደቅ ሀበሻም ፈረንጅም መሆን ያልቻለ ሞልፋጣ አይደለም፡፡ ለደሃው ኑሮ ባሳየው ባይተዋርነት እና በአስመሳይነቱ በጸጸት የሚቃጠልና በቁጭት የሚንገበገብ ኑሮ የተቃናለት ኢትዮጵያዊ ልሂቅም እንዳለ መዘንጋት የለበትም፡፡ በዚህ ረገድ በጸጋዬ ገብረ መድህን እሳት ወይ አበባ የግጥም መድብል ውስጥ የምናገኘው “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡የዚህ መጣጥፍ ዋና ዓላማ የናቲ ማንን “እመነኝ” የዘፈን ግጥም እያብራሩ ያለምንም ሀበሻዊ ንፍገት ማወደስ ነው፡፡ ለዚህ ማዳነቅና ማጨብጨብ እንዲረዳኝም ለናቲ ማን የዘፈን መልእክት በርዕሰ ጉዳይ እጅግ የቀረበውን የጸጋዬን “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” በንጽጽር  አነሳለሁ፡፡ መምህራኖቼ በትዝብት የሚያስታውሱት አለማወቄ ሳይዘነጋ፤ ሁለቱ ጥበባት መልክና ገበር ሆነው ተገልጠውልኛል፡፡ “የቱ ነው መልክ? የቱስ ነው ገበር?” ብሎ የሚጠይቅ ነገረኛ አንባቢ ቢኖር አለማወቄን የሚያውቀው እሱ ፈጣሪዬ ይያዝልኝ!የ“እመነኝ”  ድምፀቶችሙዚቃ ብዙ አላባውያን አሉት፡፡ ለምሳሌ በጥራዝ ነጠቅነት (እኔ እንኳን) ከማውቃቸው መካከል ዜማ፣ ቅኝት፣ ምት፣ ቅንብርና ግጥም ይገኙበታል፡፡ “እመነኝ” በሚለው የናቲ ዘፈን የተማረኩት በግጥሙ መልእክት ስለሆነና እኔም በጉዳዩ ላይ ለመጻፍ ምጡቅ እውቀት ሳይሆን ትንሽ የመግደርደሪያ ትውውቅ ያለኝ እሱ ላይ በመሆኑ በዚሁ ላይ እወሰናለሁ፡፡ ከ“እመነኝ” የዘፈን ግጥም ውስጥ ከአሰነኛኘቱ፣ ከምቱና ከቃላት ምጣኔው ይልቅ ሰፊውን የሙዚቃ አድማጭ(እኔንም ጨምሮ) ሊስብ የቻለው ድምፀቱ ይመስለኛል፡፡ “ድምፀት የግጥሙን ተናጋሪ ስሜትና አመለካከት ይገልጻል” ሲል ያስረዳል ብርሃኑ ገበየሁ የአማርኛ ሥነ ግጥም በተባለው ሥራው፡፡ በሌላ በኩልም ሲታይ ድምፀት “ግጥሙ [በሰሚው] ላይ የሚያሰርጸው መንፈስ ነውም ማለት ይቻላል”(1999፡ 313)፡፡ በአጭሩ ድምፀት በግጥም ውስጥ የሚገለጸውን በዘፋኙ እና አድማጩ መካከል የሚፈጠረውን የስሜት አይነት የምንረዳበት ጽንሰ ሀሳብ ነው፡፡ከ“እመነኝ” ዘፈን አራት ዋና ዋና  ድምፀቶች አግኝቻለሁ፡፡ ከኔ የተሻለ ባለሙያ ቢኖር ተጨማሪ ሊያሳየን ይችላል፡፡ እኔ ግን በተረዳኹት መጠን ስሜቴን የኮረኮረውን አቀርባለኹ፡፡ የመጀመሪያው ድምፀት ተማጽኖ(ልመና) ነው፣ ሁለተኛው ትዝብት(ቁጣ ያዘለ)፣ ሶስተኛ ቅሬታ እና አራተኛ ግራ መጋባት ነው፡፡ሀ. ተማጽኖ በ”እመነኝ”ልመና የሚያቀርበው ባለታሪክ ገበሬ መሆኑን የምንገምተው “ጥማድ ለኔ አይገዛ”፣ “ሞፈር”፣ “እፍኝ ሳይዘራ”፣ “ያጨደ”፣ “ጎተራ” የሚሉት የሙያ ቃላት ስላሉ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ደሀ ገበሬ አዱኛ ከሞላችለት ልሂቅ ወንድሙ ጋር ከአንድ እናት የተፈጠረ ነው፡፡ ይህ ወንድሙ ኑሮውንና ሕይወቱን እንዲያይለት እንዲህ ሲል ልመናና ግብዣ ያቀርባል፡፡“እስኪ ና ቁጭ በል እህ በል አድምጠኝየሆዴን አረፍ በል ከጥላው ከዋርካውላንተ የኔ ኑሮ መጠኑ ሚዛኑ ምን ይሆን መለኪያውእስኪ ና ዝቅ በል ውረድ ወደ መሬት እ መሬት አይተህ ብትረዳው ዓይንህ ቢመለከት የኛን ኑሮ የኛን ህይወት”እዚህ ላይ ተማጽኖው፣ ልመናው ስሜት ቆንጣጭ የሆነው ድምፀቱ ከናቲ ሊወጣ ይችላል ብዬ ፈጽሞ ባልጠበቅኩት ቅላጼ ተለውሶ በመቅረቡ ይመስለኛል፡፡ ስለ ናቲ ማን የተሳሳትኩት ምናልባትም  ምስክር በማያስፈልገው ያላዋቂ ግምቴ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የድምጹ ቅላጼ ፍጹም ረዳት ያጣ ደሀ ሰው ስሜትን በሚገባ የገለጸ ይመስለኛል፡፡ ተስፋ ቢሱ ደሀ ኑሮውን እንዲያዩለት ከመማጸን በቀር(ድሀ ለማኝ ነውና) አማራጭ እንዳጣ እንረዳለን፡፡ለነገሩ ባለቅኔው ጸጋዬ “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” የግጥም ርዕስ ሥር ደሃው ለልሂቁ ኑሮውን ያለመንገሩን ጉዳይ እንዲህ ሲል አንስቶት ነበር፡፡“ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፤ ሕመምክን ለማታዋየኝበጸጥታህ ለምትወቅሰኝጎፈሬህን እንዳባትህ፤ እንደሞያህ አጎፍረህበወለባ አንቆጥቁጠህሎቲ አጥልቀህ ጦር አንግበህበመኪና እግር እማልፍህየማትጠራኝ የማላውቅህ”ባለቅኔ ነብይ ነው ብዬ እስክገረም ድረስ ባለጎፈሪያሙ ናቲ ማን ደሀው ልሂቁ ላይ የነበረውን የጸጥታ ወቀሳ ወደ ገነፈለ ዜማ ቀይሮ አምጥቶልናል፡፡ ይህ ምላሽ እንግዲህ ከ45 ዓመታት በኋላ የመጣ የጥበባት ወግ ሆኖ ተሰምቶኛል።በዚህ የናቲ ዘፈን መሰረት ልሂቁ  የገበሬ ወንድሙን ሕይወት አያውቅም፣ አይረዳም፡፡ እዚህ ላይ ከቦታቸው መራራቅ ይልቅ አሳሳቢው የልሂቁ ችላ ባይነት፣ ባይተዋርነትና የወንድሙን ኑሮ አለመረዳቱ ይመስለኛል፡፡ ወንድም ለወንድሙ፣ ወገን ለወገኑ የሚያሳየውን ችላ ባይነት በተመለከተ ግን የናቲ እመነኝ ዘፈን አዲስ ባይሆንም ከደሀው አንጻር  የባላገሩን  ወዮታ ከነቢዩ ኤርሚያስ ባልተናነሰ የሰቀቀን ድምፀት ያስደምጣል፡፡ “የማለቅሰው ስለነዚህ ነገሮች ነው፤ ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል፤ ሊያጽናናኝ የቀረበ፤ መንፈሴንም ሊያረጋጋ የሞከረ ማንም የለም…፡፡”(ሰቆቃው ኤርሚያስ 1፡16)ወንድም ለወንድሙ ባሳየው የምናገባኝነት ጉዳይ ናቲ ማን ከደሀው ወገን የመንገሩን ያህል ከልሂቁ ወገን ደግሞ በጥልቅ ስሜት የምናገኘው “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” የሚለው የጸጋዬ ገብረ መድህን ግጥም ነው፡፡ ልሂቁ ለባላገሩ እንዲህ ሲል ስሜቱን ይገልጻል፡፡“ይድረስ ላንተ ለማላውቅህ ለወንድሜ ሩቅ ለማልፍህለምታውቀኝ ለማላውቅህለምታየኝ-ለማላይህማነህ ባክህ?ሳትወደኝም ሳታምነኝም፤ አጢነህ ለምትፈራኝስናገርህ አጠንክረህ፤ አተኩረህ ለምትሰማኝ…ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፤ ለአረህ ዟሪው ለገታሩለሩቅ ገጠሬ ነባሩለማላውቅህ ለዳር ዳሩማነህከሩቅ የምታስተውለኝየማልለይህ-የምትለየኝተግተህ የምትገምተኝ፤ ያላየህኝ አስመስለህአቀርቅረህ ተግ ብለህ፤ ባንደበትህ የእርግማን መርዝ፤ በልብህ ትዝብት ቋጥረህ…”በቃ ይኸው ነው! “ከዚህ በላይ እንደምትመለከቱት” ብዬ ለማብራራት አልሞክርም፡፡ “ያላዋቂ ሳሚ…” እንደሚባለው  ቅኔውን ባልተገራ  ቋንቋ መለቅለቅ ስለሚሆንብኝ ከታላቅ ትህትና ጋር ወደ ቀጣዩ የ”እመነኝ” ድጸምት ልሻገር፡፡ ለ. የትዝብት ድምፀትበናቲ “እመነኝ” ተማጽኖው ስሜታችንን ቀስቅሶ መልእክቱን ነግሮን ሲያበቃ እንዲሁ ያንኑ ልመናና ልቅሶ እየደጋገመ አይቆምም፡፡ አንዱ ድምፀት ወደሌላው እየተቀባበለ፣ እንደሰንሰለት እየተቀጣጠለ የጭብጥ ውህደታቸውን እንደጠበቁ ይፈሳሉ፡፡ ደሃው በ“እመነኝ” ጥያቄውን ተማጽኖውና ግብዣውን ካቀረበ በኋላ ተግ በሚለው አስገምጋሚ ድምጽ ናቲ ማን የስሜት ጡዘቱን (crescendo) ይጀምራል፡፡ ጡዘቱ ሲጀምር የትዝብት ድምፀትን እናገኛለን፡፡“እህ!የናንተ ቁምነገር የናንተ ክርክርጥማድ ለኔ አይገዛ አያግዝም ሞፈርሚታይ ሚናፈሰው በየሞገዱ ላይ ቅንጣት ደስታን እንጂ የኛን ችግር አያይ”እዚህ ላይ (ዘፈኑን በጥሞና ካዳመጥነው) ደሀው ተማጽኖውን ጨርሶ ቁጣ ያዘለ ትችት ውስጥ ሲገባ የትችቱ ምንጭ ወቅታዊ ሁነቶች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ እገምታለሁ፡፡ የልሂቃኑ ክርክርና መረጃ መቀባበል (በየሞገዱ ላይ) በማህበራዊ ድህረ ገጽ የሚካሄድና ለደሃው ኑሮ ፋይዳ የሌላቸው ርዕሰ ጉዳዮች እንደሆኑ  እጠረጥራለሁ፡፡ የትዝብት ድምፀቱ ጠንከር የሚለው ግን ደሀው በአርቲስቱ ላይ የሰላ ትችቱን ሲሰነዝር ነው፡፡“አንተም ጥበበኛው አንተ ባለዝናውበባህሌ ደምቀህ በባህሌ ኮርተህ አጊጠህ በዜማው የውስጤን ትኩሳት ምነው ማታወራው?”በዘልማድ “አርቲስቱ ከሕዝብ ነው የወጣው” ይባላል፡፡ አብዛኛው አርቲስትም (ሁሉም አላልኩም) ለቧልትና ለፈንጠዝያ ሆን ተብለው በተከፈቱና በተጠናከሩ የቴሌቪዥን ትእይነቶች(TV Shows) ላይ ቀርበው ሲናገሩ “ሀብቴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ አገሬን እወዳለሁ” ይላሉ፡፡ ታዲያ በሚያነሱዋቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከመዘናቸው ቀላል የማይባሉ የሀገራችን ድምጻውያን ጥበበኞች ሳይሆኑ የቢራ አሻሻጮች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ግባቸው አንድና አንድ ነው፡፡ መሸታ ቤት አስጨፍሮ መክበር! ናቲ ግን ይቀጥላል ለዚያ ድሃ ድምጽ ሆኖ፡-“እስኪ ና ዝቅ በል፤ ግልጽ እንነጋገር፤ የእውነት፤ በል እንወቃቀስ ስለ ፍቅርስንት አለ በሆዴ፤ እህ ብዬ ፍርዱን ለሱ ትቼ፤ ያለፍኩት ሳልናገር” ብዙ ኢትዮጵያውያን ፍርዱን ለአምላክ የምንተወው ምናልባት በምድር ያሉ ተቋሞቻችን ለግፍ ቅርብ፣ ለፍትህ ሩቅ ስለሆኑ ይሆን? ከዓመታት በፊት ባህር ዳር ላይ አንዱ ተስፋ የቆረጠ ባለጉዳይ ለክልሉ ባለሥልጣን በጻፈው የአቤቱታ ደብዳቤ “ግልባጭ ለእግዚአብሔር” ያለው ወዶ ነው?ጥበበኛው የባላገሩ ልጅ ነኝ አንዳንዴም እኔ ራሴ ባለገር ነኝ እያለ ነገር ግን መልሶ እሱኑ በሚጎዳ ተግባር ውስጥ እየተዘፈቀ መኖሩ በፊትም የነበረ፣ ናቲ በሰላ ትችት አጅቦ እንዳዜመለን አሁንም ያለ፣ ምናልባትም ነገም የሚኖር ይመስለኛል፡፡ የአሁኑን ዘመን የጥበበኞች እፍረተ-ቢስ መመጻደቅ  በ”እመነኝ” የጠቀስኩት በቂ ስለሆነ፤ የወደፊቱንም ለማወቅ እንደነ ኤርሚያስ የትንቢት ነጋሪነት ጸጋ አልተሰጠኝምና (ጽድቁ በቀረና.. አላችሁ?) ማስረጃ ላቀርብበት የምችለው በቀዳሚው ዘመን የተንጸባረቀውን ስሜት ነው፡፡ የልሂቁን አስመሳይነት በተመለከተ የናቲ እመነኝ ከደሃው እይታ አንጻር ፍንትው አድርጎ ያሳየንን የጸጋዬ “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” የሚለው ግጥም ደግሞ ከልሂቁ ምልከታ አንጻር በውብ ቋንቋ ያቀርበዋል፡፡ ጥቂት ስንኞች ለንጽጽር እንመልከት፡፡“ባክህ ማነህ ወንድምዬ፤ አንድም ቀን የማንወያይበውል በጣይ፤ ባደባባይበፎቶግራፍ ዓይን እንጂ ዓይን ለዓይን የማንተያይእኔ ለወሬ አንተን መሳይ፤ አንተ ለጭንቅ እኔን መሳይማነህ እኮ የማላውቅህማዶ ለማዶ ሩቅ ለሩቅ፤በመኪና ዓይን የማይህየማትቀርበኝ የማልቀርብጠረንክን የምጠየፍህበጋዜጣ በመጽሔት ወሬህን የምተርክህሥዕልክን ፎቶግራፍክን ላገር ጎብኚ የምሸጥህ”የጸጋዬ ግጥም የጥበበኛውን፤ የልሂቁን  አስመሳይነት ነገር በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ይቀጥላል፡፡“አንተ ማነህ? እኮ ማነህ ወንድምዬ፤ ደራሲ የሚቀኝብህሠዓሊ የሚነድፍብህቀሲስ የሚቀስስብህየቱሪስት የጋዜጠኛ፤ ካሜራ እሚጋበዝህየሚተች የሚተረጉም፤ የሚነድፍህ የማንም እጅየማነህ ደም የማነህ ቅጅ?አንተ የማማ ኢትዮጵያ ልጅእኔማ ሆኜብህ ፈረንጅአሳብ ለአሳብ ለተጣጣንምን አጣልን፤ ማን አጣላንማን እንዳንወያይ ገራን…”ሐ. የቅሬታ ድምፀትእመነኝ ከተማጽኖና ከልመና ባሻገር ቁጣ የሞላው ትዝብት እንዳዘለ፤ ከትዝብትም አልፎ ቅሬታ የሚያቀርብ ዜማ ነው፡፡ ቅሬታውም የቀረበው በትዝብት የጀመረውን የስሜት ጡዘት (crescendo) በማስቀጠል ነው፡፡ ናቲ ማን እንዲህ ሲል “አቤት አቤት” ይላል፡፡“እፍኝ ሳይዘራ ግፍ ሳይፈራስንት አለ ያጨደ፤ የሞላ ጎተራ”   የስሜት ጡዘቱ ጫፍ የደረሰው ይሄኔ ይመስለኛል፡፡ ናቲ ማን ራሱ የቅሬታ ድምፀቱን (ለነገሩ ለቅላጼውም ጭምር) አጽንኦት የሚሰጠው በነዚህ ስንኞች ላይ ነው፡፡ ቅሬታ የ“እመነኝ” ኃይለ ቃል እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ በማጠቃለያ ላይ ደግሞ ሆን ብሎ ይደግመዋል፡፡ በርግጥም ዝርፊያ ሕግ በሆነበት አገር፣ ሞላጫ ሌባም በአደባባይ በሚሞገስበት ዘመን ቅሬታ ኃይለ ቃል ያልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ነው? የ“እመነኝ” የቅሬታ ድምፀት በጸጋዬ ግጥም ውስጥ እንኳን አቻ አጥቼለታለሁ፡፡ ባለቅኔ ሎሬት ያላነሳው የሀብት ክፍፍል ነገር “እመነኝ” አንስቶታል፡፡ ይህም ሥራውን  ኦሪጂናሌ አድርጎታል፡፡መ. የግራ መጋባት ድምፀት“እመነኝ” የሕይወትን፤ በተለይም የኑሮን እንቆቅልሽ በግራ መጋባት ስሜት ያነሳዋል፡፡ ምን ቢሆን ነው የአንድ እናት ልጆች፤ ወንድማማቾች፤ እህትማማቾች አጥጋቢ ባልሆነ ምክንያት ኑሮአቸው የሚለያየው?“ካንድ እናት ተፈጥረን ሆነን በአንድ ላይኑሮአችን ለየቅል የምድርና ሰማይ”በተለይ የወቅታዊውን የኢትዮጵያ ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ለምናስተውል ይህ ደሀው በ “እመነኝ” ያነሳው የግራ መጋባት ሥሜት ብዙ ነገር ይነግረናል፡፡ በርግጥም ኑሮን በማሸነፍ በኩል ችሎታና የዜግነት መብት በሌላ መመዘኛ በልተተኩባት ኢትዮጵያ ግራ መጋባት የምንደብቀው ስሜት ሊሆን አይችልም፡፡እንደ መውጫበነገራችን ላይ ናቲ ማንን ሆነ ሎሬት ጸጋዬን በቅርበት አላውቃቸውም፡፡ ከያኒያኑ ከኔ ሩቅ ቢሆኑም ከሥራዎቻቸው መካከል “እመነኝ” እና “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” ግን ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ትይዩ ስሜት የሚሰጡ የጥበብ ስራዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡በመጨረሻ ተማጽኖ፣ ትዝብት፣ ቅሬታ እና የግራ መጋባት ሥሜቶች የገነኑበት የሙዚቃ ቪዲዮ ቢሰራ ይህን ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ሥራ ከድምጽ ባሻገር የዕይታ ጉልበት ይሰጠዋል እላለሁ፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ?

አስተያየት