ሰኔ 4 ፣ 2010

ጉራማይሌ ቋንቋ ፣ ጉራማይሌ ማንነት

ባሕልትምህርት

አንዳንድ የአገራችን ባለስልጣናት ለውጭ አገር ጋዜጠኞች ቃለ-መጠይቅ ሲሰጡ ባሳዩት ደካማ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ በማህበራዊ ሚዲያ አካባቢ ሲተቹ እንደነበር…

አንዳንድ የአገራችን ባለስልጣናት ለውጭ አገር ጋዜጠኞች ቃለ-መጠይቅ ሲሰጡ ባሳዩት ደካማ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ በማህበራዊ ሚዲያ አካባቢ ሲተቹ እንደነበር አስታውሳለሁ። ባለንበት የሉላዊነት (globalization) ዘመን ጥሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ከሚያስገኝልን ጠቀሜታዎች አንፃር ይኼ በተወሰነ መልኩ እውነትነት አለው። እንግሊዝኛን አቀላጥፈው የማይነገሩ ባለስልጣናት ደግሞ በአስተርጓሚ ታግዘው ሃሳባቸውን በሙላት እንዲያስተላልፉ ቢደረግ የሚሻል ይመስለኛል። አላለልንም እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአገር መሪዎች ብሔራዊ ኩራታቸው ከሚገልፁበት መንገድ አንዱ(እንግሊዝኛም እየቻሉ)ለውጭ ጋዜጠኞች በራሳቸው ቋንቋ ቃለመጠይቅ በመስጠት ነው። የግብፅና የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ባለስልጣናት በአገራችን ጉብኝት ሲያካሂዱ እነሱ በቋንቋቸው ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ የእኛ አገር መሪዎች አጥርተው በማይችሉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሀሳባቸውን ለማስተላለፍ ግዴታ ያለባቸው ይመስል ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ነው። መሪ ሁሉን አዋቂ ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ደግሞ የእውቀት መለኪያ ተደርጐ በሚወሰድበት እንደኛ ባለ ማህበረሰብ ግን አንድ መሪ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተርጓሚ እንዲመደብለት መጠየቅ የሚታሰብ አይደለም።ፖለቲከኞቻችን በውጭ ግንኙነቱ መስክ ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ዜጋ ጋር ሲነጋገሩም ጥርት ባለ የአገር ውስጥ ቋንቋ መጠቀም አይፈልጉም ወይም አይችሉም። ከቀበሌ አስተዳዳሪ እስከ አገር መሪ በየስብሰባውና በየቃለ መጠይቁ አድማጩን (audience) ባላገናዘበ መልኩ በንግግሩ መሀል የእንግሊዝኛ ቃላት በመደንጎር የሃሳብ ድህነቱን ለመሸፈን ይሞክራል። የ2007 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ ቀን የምርጫ ቦርድ ሃላፊው በምሽት ሁለት ሰዓት ዜና ላይ ቀርበው “የመራጩ turnout ዲሞክራሲያችን solid ground ላይ እየተገነባ እንደሆነ የሚያሳይ አንዱ indicator ነው” ብለው ሲናገሩ ስንቱ ገበሬ ተረድቶት ይሆን ብዬ አሰብኩ (መቼም አሁን አሁን ቴሌቭዥኑ ገጠር ከተሞችም እየገባ ነውና)።ጉራማይሌ ቋንቋ የመጠቀም አባዜያችን ትንሽ ቆየት ያለ ይመስላል። እውቁ የታሪክ ፀሓፊና ፖለቲከኛ ተክለፃዲቅ መኩሪያ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ የታዘቡትን ‘የሕይወቴ ታሪክ’ በተሰኘው ግለ-ታሪካቸው እንዲህ አስፍረውታል:“ያንድ መሥሪያ ቤት በጀት ጉዳይ ክርክር ተይዟል። ለአስረጅነት የቀረበው የገንዘብ ምክትል ሚኒስትር በግምት በንግግሩ ውስጥ ሃምሳ በመቶ እንግሊዝኛ ነው። የሌሎቹም ሚኒስትሮች ይነስ ይብዛ ሃያ አምስት በመቶ እንግሊዝኛ ነው። እኔም ብጣሽ ወረቀት ላይ ‘ክቡር ሰብሳቢ ፡ ምክር ቤታችን የእንግሊዝ ምክርቤት ሊመስል ምንም አልቀረው። ምናለበት አባሉ ሁሉ በመንግሥቱ ቋንቋ አሳቡን እንዲገልፅ ቢደረግ’ የሚል መልእክት ፃፍኩና ለሰብሳቢው ሰጠሁት::”ይኼ በመሪዎቻችን ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቀመስ በሚባል የማህበረሰብ ክፍልም በሰፊው የሚታይ ችግር ነው (መሪዎቻችንስ ከኛው አይደል የወጡት)። እንግሊዝኛ ቀላቅሎ በማውራት ብቻ አዋቂ መምሰል የሚፈልግ ወጣት ቁጥሩ ቀላል አይደለም። እንግሊዝኛ ቋንቋ እንደ ሌሎች ቋንቋዎች ዕውቀትን የምንገበይበትና የምናስተላልፍበት መሳሪያ ከመሆን አልፎ ራሱን የቻለ እውቀትና የእውቀት መለኪያ ተደርጐ እየተወሰደ ነው። በአንድ ወቅት በአንድ የቋንቋ ትምህርት ቤት “እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚችል ሰነፍ ተማሪ የለም” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎ አነበብኩ። ትምህርት ቤት ደጃፍ ረግጦ የማያውቅ ኬንያዊ ገበሬ እንግሊዝኛን ከናንተ በበለጠ አቀላጥፎ እንደሚናገር ማን በነገራችሁ አልኩኝ። እንግሊዝኛ ቋንቋን አቀላጥፈው እንዲናገሩ ማስቻል የመጨረሻ ግባቸው የሚመስል አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶችም ከዓመት ዓመት ከልክ በላይ በሚንረው ክፍያቸው የብዙ ወላጆችን ኪስ እያራቆቱ ይገኛሉ። ቤታቸው እንግዳ በመጣ ቁጥር ልጃቸውን ከጓዳ ጠርተው “እስቲ በእንግሊዝኛ አስደምማቸው” እያሉ የሚንቀባረሩ ወላጆችም አጋጥመውኛል።በቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ ለሚታየው ችግር አንዱ መንስኤ ቋንቋችንን ትተን የባእድ ቋንቋን ለትምህርት መስጫነት ማዋላችን ይመስለኛል። ፕሮፌሰር ፓይ ኦባንያ የሚባሉ ናይጀሪያዊ የስነ-ትምህርት ተመራማሪ ያለንበትን አሳዛኝ ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል:“አፍሪካ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ምሁራንን ከበቀሉበት ማህበረሰብ የሚነጥል ዘላቂ ልማት ለማስመዝገብ የሚጠበቅባቸውን ወሳኝ አስተዋፅኦ የማድረግ አቅማቸውን የሚያዳክም ነው። አንድን ሰው ገና ከመጀመሪያው ከአፍ መፍቻ ውጭ በሆነ ቋንቋ ማስተማር አዋቂ እንዲሆን ቢረዳው እንጂ በባህል ተኮትኩቶ እንዲያድግ አያግዘውም። ይኼ ደግሞ ለማህበረሰቡ የኔነት ስሜት እንዳይኖረው ያደርገዋል። አፍሪካውያን ምሁራን ልጆቻቸው በአገር በቀል ቋንቋ ትምህርት ወደማይሰጥባቸው የግል ትምህርት ቤቶች በመላክ ለችግሩ መባባስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ። አብዛኞቹ ወላጆች ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሊግባቡ አለመቻላቸው የክብር ኒሻን የተሸለሙ ያህል ይኮሩበታል (Many see the inability of their children to communicate in their mother tongue as a badge of honor).”  ይህንን ሀሳብ በሚያጠናክር መልኩ ዶ/ር ታጁዲን አብዱልረሒም የተባለው ናይጄሪያዊ ምሁር ዩኒቨርሲቲዎቻችን እንደ ደሴት ከማህበረሰቡ ተነጥለው ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልፁታል: “የጥናት ማእከሎቻችን ጥናት ሲያካሂዱ ህብረተሰቡ የሌለ እስኪመስል ረስተዉት ነው፡፡ መንግስታትም ፓሊሲ ሲያወጡ አገር በቀል ምሁራን የሌሉ እስኪመስል ድረስ ተረስተው ነው፡፡ በመሠረቱ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከማህበረሰቡ ጋር የተገናኙ አይደሉም።”ወደ አገራችን ስንመጣ ዩኒቨርሲቲዎች ከማህበረሰብ እንዲነጠሉ ካደረጋቸው ምክንያት አንዱ ትምህርት የሚሰጠውና ጥናትና ምርምር የሚካሄደው በባእድ ቋንቋ መሆኑ ይመስለኛል። በአገራችን ውስጥ ብዙ ቋንቋዎች ከመኖራቸውና ከቋንቋዎቹም ዝቅተኛ የስነፅሑፍ እድገት ደረጃ ጋር ተያይዞ እንግሊዝኛ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአገር በቀል ቋንቋ መተካት አይቻል ይሆናል። ቢሆንም ግን የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠቃቀማችን በአገር በቀል ቋንቋዎች እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳያሳድር ማድረግ እንደምንችል እገምታለኹ። በቅኝ ገዥዎች ተገዝታ አታውቅም ብለን የምንኮራባት አገራችን የገዛ ታሪኳን ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንድታስተምር የምትገደድበት አሳማኝ ምክንያት ይገኝ ይሆን? ምሁራን የሚያካሂዷቸው ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች በአገርኛ ቋንቋ ተተርጉመው መቅረብ ካልቻሉ የጥናቱ ጭብጥ በትምህርት ወዳልገፋው የማህበረሰቡ ክፍል ሊሰርፅ የሚችለውስ እንዴት ነው? ምን ያህሉስ የተማረ ሰው ነው? እውቀቱን አርሶ አደሩ በሚገባው ቋንቋ ማስረዳት የሚችለው?የትምህርት እድል አግኝቼ በጐበኘኋትና የፍየል ግንባር በምታህለው ዴንማርክ በምትባል አገር (ስፋቷ የኢትዮጵያን 4% ያክላል) የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት የሚሰጠው ሙሉ በሙሉ በዴኒሽኛ ቋንቋ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪና ከዛ በላይ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። ሆኖም ተማሪዎች ከፈለጉ ፈተና ላይ በቋንቋቸው እንዲመልሱና ጥናታዊ ፅሑፍ እንዲያቀርቡ ይበረታታሉ። ክፍል ውስጥ የውጭ አገር ዜጋ ከሌለ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያካሂዱት በዴኒሽኛ ቋንቋ ነው። በዓለም ዙሪያ አዲስ የወጡና ተነባቢ የሆኑ (Best seller) መፃህፍት ወዲያው በዴኒሽ ቋንቋ ተተርጉመው ገበያ ላይ ለሽያጭ እንዲቀርቡ ይደረጋል። እንደዚህ የሚያደርጉት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ አይደለም። ዴንማርካውያን እንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ ጠንክረው በመስራታቸው ብሔራዊ ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ሳይሆን ጥሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆኑት አገሮች ከስዊድን ቀጥለው ሁለተኛ ደረጃ ይዘዋል። በዚህ በሉላዊነት ዘመን የአለምን ገበያ የሚፈጥረውን እድል አሟጠው ለመጠቀም እንዲያስችላቸው ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ከጀርመንኛና ከፈረንሳይኛ አንዱን መርጠው እንዲማሩ ይደረጋል። ጥሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ እያላቸው ታዲያ ለምንድነው ነው ልጆቻቸውን በዴንሽኛ ቋንቋ የሚያስተምሩት? በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲማሩ የሚማሩትን ነገር በጥልቀት እንዲያውቁት ፣ ከቀን ተቀን ኑሮአቸውም ጋር አዛምደው ችግራቸውን ለመቅረፍ እንዲጠቀሙበት እንደሚያግዛቸው ስለተረዱ ይመስለኛል። እስኪ ጉዳዩን ወደ አገራችን እናምጣውና አንድ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የኢትዮጵያ ታሪክ ፈተና ላይ መልስ እየፃፈ በእንግሊዝኛ መግለጽ ያቃተውን በአማርኛ አሟልቶ ቢፅፍ ስንቱ አስተማሪ ይሆን ቋንቋውን ግምት ውስጥ ሳያስገባ የፃፈውን ፍሬ ነገር አንብቦ የሚገባውን ውጤት (ማርክ) የሚሰጠው?ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአንድ አገር የስራ ቋንቋና የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ቋንቋ ከተለያየ የሚሰጠው ትምህርት ችግር ፈቺ ሆኖ የማገልገል እድሉ አናሳ ነው። ከዚህም ባለፈ ትውልዱን ለውጭ የባህል ወረራ ሰለባ እንዲሆን በር ይከፍታል። አቶ ፍሥሃ አስፋው የተባሉ ፀሓፊ ስጋታቸውን እንዲህ በማለት ይገልፃሉ: “የአማርኛ ቋንቋችን የምርምርና የጥበበ ዕድ ማስተማሪያ እንዲሆን ባለመደረጉ ፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ሆነ በቤተምርምር ማዕከላት እንዲሰራበት ዕድል ባለመሰጠቱ ዛሬም ቢሆን በባህሎቻችን ፣ በሥነምግባራችንና በውስጥ ስሜታችን ለውጭ ባህልና የርዕዮተዓለም ወረራ ቅኝተገዥነት እየተጋለጥንና እየተንበረከክን መቀጠላችን አይካድም፡፡” ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ እኛ ኢትዮጵያውያን ጃፓን ከተከተለችው መንገድ መውሰድ የሚገባንን ትምህርት እንዲህ በማለት ያስረዱናል: “ጃፓን የተከተለችው ብሔራዊ ቋንቋ አጠቃቀም ኢትዮጵያ ከተከተለችው ይለያል። የጃፓን መሪዎች ዜጎች የውጭ ቋንቋን እንዲያውቁ የሚያበረታቱት ከውጭ የሚጠቅማቸውን ለማወቅና ተርጉመው ለህዝባቸው ለማቅረብ እንዲመቻቸው ነው። የውጭ ቋንቋ የአገሪቱን ብሔራዊ ቋንቋ ተራ ተክቶ እንዲጫወት አልፈቀዱለትም። የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ የማስተማሪያ ቋንቋ ሆኖ መቀጠሉ እውቀት በቀላሉ ለአብዛሃኛው ህዝብ እንዲዳረስ ከማስቻሉም በላይ ብሔራዊ ቋንቋቸው ከዘመናዊ ጥናትና ምርምር መንደር ሳይወገድ ባህላቸውን አስጠብቀው እንዲቀጠሉ እድሉን አመቻችቶላቸዋል።”በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግስት የጣልያን መውጣትና የእንግሊዞች መግባት ተከትሎ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የበላይነት እያገኘ መምጣቱ ቢያሳስባቸው አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያን ታሪክ በአማርኛ ቋንቋ ለመፃፍ ያነሳሳቸው ምክንያት እንዲህ በማለት ያስረዳሉ:በአማርኛ ቋንቋ የታተመ የኢትዮጵያ ታሪክ ስለሌለ ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትና በሌሎቹም የሚገኙት እንግሊዞችና አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ ወጣቶች የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያስተምሯቸው በእንግሊዝኛ በተጻፈ መጽሐፍና ቋንቋ ነው። መድኃኒዓለም ትምህርት ቤትም ፈረንሳዮቹ የሚያስተምሩት በፈረንሳይኛ ነው። …‘ፊደል እያለን ጸሐፊም ሳይጠፋ የገዛ ታሪካችንን ለገዛ ወጣቶቻችን የውጭ አገር ሰዎች በየቋንቋቸው እንደምን ማስተማር ቻሉ።እያልሁ ማሰላሰል ጀመርኩ።   የአገሬው ታሪክ ፣ በአገሬው ቋንቋ ፣ ለአገሬው ዜጋ እንዲደርስ ላደረጉት አስተዋፅኦ አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ሊመሰገኑ ይገባል። በዚህ ዘመንስ በተሰማራንበት የትምህርት ዘርፍ የሌሎችን ይቅርና የራሳችን የጥናት ውጤቶች በአገርኛ ቋንቋ ተርጉመን ለህዝቡ እንዲደርስ ያደረግን ስንቶቻችን ነን?መፍትሄው ምን ይሁን ለሚለው ጥልቅ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም የሚከተሉት የመፍትሔ ሃሳቦች ተግባራዊ ቢደረጉ ይጠቅማሉ ብዬ አስባለሁ።በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወሰኑ የትምህርት አይነቶች (ኮርሶች) ተመርጠው በአገሪቱ የስራ ቋንቋ ተቀርፀው መስጠት ቢጀመር ጠቀሜታው የጐላ ይመስለኛል። በአገር ውስጥና ውጭ አገር የታተሙ ተነባቢ መፃሕፍትና ጥናታዊ ስራዎችም በአገሪቱ የስራ ቋንቋ እየተተረጐሙ ለገበያ ቢቀርቡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማንበብ የማይችለው የህብረተሰብ ክፍል የእውቀቱ ተቋዳሽ እንዲሆን ያስችለዋል። በመተርጐሙ ሂደት ላይ ደግሞ ፍቺ ያልተገኘላቸው ቃላቶች የቋንቋ ሰዎች እየተገናኙ ፍቺ ለማፈላለግ በሚያደርጉት ጥረት ቋንቋችን ዘመኑ ለደረሰበት ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሚመጥን መልኩ እንዲያድግ ያግዘዋል።በቅርቡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመፃፍ የሚታወቁት እውቁ የታሪክ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ከአሁን በፊት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያዘጋጁት የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ በአማርኛ ተርጉመው አቅርበውልናል። ይህንን አስመልክቶ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዲህ ሲል በብሎጉ ከትቧል፡ በእንግሊዝኛ ከታተመው መጽሐፍ ይልቅ በአማርኛ ተተርጉሞ የቀረበው መጽሐፍ ለተከታታይ ጊዜ በብዙ ሺህ ቅጂዎች የመታተም ዕድል አግኝቷል። በአማርኛ የተጻፈው መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ከተጻፈው ቅጅ ይልቅ በብዙ ዓይነት አንባቢዎች ዘንድ የመግባት ፣ በየጽሑፎችም የመጠቀስ ዕድል አግኝቷል፡፡ ‘ለምን?’ የሚል ጥያቄ እዚህ ላይ ማንሣት ይገባናል። መልሱ ቀላል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ዘርፍ የላቀ ማዕረግ ላይ በደረሰው በፕሮፌሰር ባሕሩ የተዘጋጀው መጽሐፍ ፣ በሀገሩ ቋንቋ ለታሪኩ ባለቤት ሊቀርብለት በመቻሉ ነው። … ከኩሬ ይልቅ ወንዝ ብዙ ቦታዎችን የማርካትና በመስኖ በየእርሻው የመድረስ ዕድል ስላለው ነው፡፡ ኩሬ ምሁርነት የምንለው: በመነጨበት ቦታ በዚያው ታቁሮ ቀርቶ ራሱን ብቻ የሚለውጥ ነው፡፡ ምሁራን ወንዝ የሚሆኑት አካዳሚያዊ ባሕሉን፣ መንገዱን፣ ዘዴውንና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለሌላውም ማኅበረሰብ ሲተርፉ ነው።”እንዲህ አይነት አካሄድ በምሁራን ዘንድ ቢለመድ ለአገሪቱ የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ ነው። ቋንቋችን ከእንግሊዝኛ ልክ እያደገ ሲሄድ ብቻ ነው በእንግሊዝኛ ‘ምናውቀው’ በደንብ (በጥልቀት) ምናውቀው ፣ ከቀን ተቀን ኑሮአችን ጋር የምናዛምደው/የምናዋህደው ፣ ሳይማር ባስተማረን ማህበረሰብ ውስጥ የምናሰርፀው። ባህላችንና ቋንቋችን ጠብቀን ማደግ ስንችል ብቻ ነው በሀገራችን በማንነታችን መኩራት የምንችለው። 

አስተያየት