ኅዳር 3 ፣ 2014

ጦርነት እንቅፋት ሆኖባቸው 12ኛ ክፍል ያልተፈተኑ ተማሪዎች ጉዳይ

City: Addis Ababaትምህርትማህበራዊ ጉዳዮች

በዓለም አቀፍ ሁኔታ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅቱ የተዛባው እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ በተከሰተው የጸጥታ ግጭት ምክንያት የተስተጓጎለው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የመልቀቂያ ፈተና ምን አይነት የስነልቦና ተጽዕኖ አምጥቷል?

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

ጦርነት እንቅፋት ሆኖባቸው 12ኛ ክፍል ያልተፈተኑ ተማሪዎች ጉዳይ

ራሄል መሰለ የ20 ዓመት ወጣት ናት። የወልዲያ ነዋሪ ስትሆን የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት። በአሁን ሰዓት በሰሜኑ ክልል የተፈጠረውን ግጭት በመሸሽ አዲስ አበባ ዘመዶቿ ጋር ተጠግታ በመኖር ላይ ትገኛለች።

በ2012 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ሁኔታ ተከስቶ የነበረው ኮቪድ-19 በፈጠረው የትምህርት ቀናት መዛባት ምክንያት የ2013 ዓ.ም የ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ከጥቅምት 29- ህዳር 02 2014 ዓ.ም. እንዲሰጥ የተደረገ ቢሆንም ራሄል እንደ እኩዮቿ ለፈተና መቀመጥ አልቻለችም።

“በእርግጥ አሁን ላይ ተወልደን ያደግንበት ቦታ ካለበት አስከፊ ሁኔታ አንጻር የትምህርት ጊዜያችን መስተጓጎሉን እንደ ትልቅ ችግር ማየቱ ቅንጦት ሊመስል ይችላል” የምትለዉ ራሄል ያለችበት ሁኔታ ስለ ደህንነቷ እንድታስብ እንጂ ትምህርቱን እንድትናፍቅ እንዳላደረጋትም ትናገራለች።

“ይህ ሁኔታ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? ነገስ እንዴት ነው የምንሆነው የሚል ስጋት ውስጥ ከቶናል፣ አእምሮኣችን ያለበት ሁኔታም በምን አይነት ፍጥነት ወደ ትምህርት እንደሚመለስ አናውቅም” ስትል ለአዲስ ዘይቤ ገልጻለች።

ይህ ታሪክ የራሄል ብቻ አይደለም። በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ ዋግህምራ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ ሰሜን ሸዋ፣ እና ሰሜን ጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እየተባባሰ በሄደው ግጭት ሳቢያ የዩኒቨርሲቲ ፈተና መውሰድ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ2012 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ሁኔታ ተከስቶ የነበረው ኮቪድ በፈጠረው የትምህርት ቀናት መዛባት ምክንያት የ2013ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከጥቅምት 29- ህዳር 02 2014 ዓ.ም. እንዲሰጥ የተደረገ ቢሆንም፣ ትምህርት ሚኒስቴር በጸጥታ ችግር ምክንያት በብሔራዊ ፈተናው 36ሺህ ተማሪዎች መቀመጥ አለመቻላቸውን በመጥቀስ ሁለተኛ ዙር ፈተና ከአንድ ወር በኋላ እንደሚሰጣቸው እና አሁን እየተፈተኑ ከሚገኙት ተማሪዎች ጋር ምደባ እንደሚደረግላቸውም ገልጿል።

በአንድ ሀገር ውስጥ በተመሳሳይ የትምህርት እርከን ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተለያየ መንገድ እንዲከተሉ ሲደረጉ የሚያጋጥማችው የስነልቦና ጫና ከሌሎች የጦርነቱ ጫናዎች ጋር ሲደመር ከባድ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።

ይህን አስመልክቶ በአሁን ሰዓት በዚህ ጦርነት ሳቢያ ፈተናቸው የተስተጓጎለ ተማሪዎች ብዛት እና እነሱን አስመልክቶ ሊደረግ የታሰበው እቅድ ምንድነው ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ሲመልሱ በአማራ ክልል 357 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ በመጥቀስ ከነዚህም መካከል በጦርነቱ ምክንያት በ112 ትምህርት ቤቶች ብሄራዊ ፈተናው አይሰጥም ብለዋል። በተማሪዎች ብዛት ሲገልጹም ከ164 ሺህ ተማሪዎች መካከል 36,000 ተማሪዎች መፈተን እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ስለመፍትሄው እና ስለቀጣይ አቅጣጫዎች ጥቆማ ሲሰጡንም “የትምህርት ሚኒስቴር እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በሚያስቀምጡልን አቅጣጫ መሰረት እንዴት እንደሚደረግ ይወሰናል” ያሉ ሲሆን አያይዘውም በአሁን ሰዓት አስቀድመው ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ የሄዱ እና ለመፈተን ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡ ከ100 በላይ ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በተደረገ ትብብር በተለያዩ የመፈተኛ ጣቢያዎች እየተፈተኑ እንደሚገኙ በመግለጽ “በቀጣይም ሁሉም ፈተናውን የሚያገኙበት መንገድ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

አዲስ ዘይቤ ከትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዘሪሁን ዱሬሳ (ዶክተር) ባገኘችው መረጃ መሰረት የ2013 ዓ.ም. የአጠቃላይ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና በሁለት ዙር እንዲሰጥ የተወሰነው ኤጀንሲው የንቅናቄ ሰነድ በማዘጋጀት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ሲሆን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለፈተና መስተጓጎል የተጋለጡትን በግጭት አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎችን የስነ-ልቦና ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ነው ሁለተኛው ዙር ፈተና የተዘጋጀው። በመሆኑም በፌደራል መንግስት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት በተመረጡት የአማራ ክልል ቦታዎች ለሚገኙት 36,340 ተማሪዎች ሁለተኛው ዙር ፈተና ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሲገልጹ “የጸጥታ ሁኔታው ውሉ ያልለየለት ጉዳይ በመሆኑ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአሰራር ለውጦች ለማድረግ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችም ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ ጠቁመዋል።

በኮቪድ-19 ተጀምሮ በጦርነቱ ሳቢያ የቀጠለው የፈተና እና የትምህርት መስተጓጎል በተማሪዎች ላይ ስለሚያሳድረው ጫና ምሁራን በተለያየ መድረክ ላይ አስተያየታቸውን ሲያስቀምጡ ቆይተዋል። አብዛኛዎቹ እንደምክንያት የሚያነሱት በትምህርት ላይ የነበሩ ተማሪዎች አንድ ዓመት ቢያልፋቸው ከእድሜያቸው አንድ ዓመት እንደመቀነስ ነው ይላሉ።

ማዕረጉ ቢያበይን (ዶ/ር) በኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ በትምህርት አመራርና አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው።

ተማሪዎች አንድን የትምህርት ክፍል ለሁለት ዓመት እንዲማሩ ማድረጉ በስነልቦና ላይም ሆነ በትምህርቱ ላይ በራሱ የረጅም ጊዜ ቀውስ እንዲኖር ያደርጋል ይላሉ።

ባለሙያው አለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቀውስ እንደፈጠረ በማንሳት “ቢያንስ ኮቪድ በዓለም የመጣ መሆኑ ሁሉም ቦታ የሚኖረውን ሁኔታ ተመሳሳይ ማድረጉ የጋርዮሽ ስሜትን ስለሚፈጥር የስነ ልቦና ጫናውን ይቀንሰዋል። በግጭቱ ሳቢያ ሲሆን ግን በአንድ ሀገር ተመሳሳይ እርከን ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን በቦታ ልዩነት ብቻ ለተለያየ እጣ መዳረጉ ብቻውን የስነ ልቦና ጫናውን የከፋ ያደርገዋል” ይላሉ።

ከዚህ በኋላ የሚፈጠረው ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል ግምታቸውን ሲያስረዱም ከዚህ በኋላ የሚኖረው የትምህርት አሰጣጥ ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ተማሪዎች ትምህርት ትተው በቤታቸው መቀመጣቸው የፈጠረባቸው የስነ ልቦናና የመዘናጋት ተጽኖ ሊኖር እንደሚችል በማመላከት ነው። የማካካሻ ትምህርትና ትኩረት ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ያለ ፈተና ወደ ቀጣዩ ክፍል የሚሸጋገሩትም ሆነ ለፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች በቅድሚያ ማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ሲያስቀምጥ ጊዜው የተፈጠረባቸዉን የስነ ልቦና ህመምንም ያማከለ መሆን እንደሚኖርበት ይመክራሉ።

በትምህርት ተኮር ስነ ልቦናና በሌሎች ተመሳሳይ ዘርፎች ምርምሮችን ያደረጉት ዶክተር ማዕረጉ አክለውም “በመንግሥትም ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ በተማሪዎች የትምህርት ጫና ላይና የሥነ-ልቦና ግንባታ ላይ የሚሠራው ሥራ በእጅጉ አናሳ ነው” በማለት ጦርነት እና ተያያዥ ግጭቶችን ገፈት እንዲቀምሱ የሚገደዱ ተማሪዎች የተሻለ ዕሳቤና ግልጽ የሆነ የሕይወት ዓላማ እንዳይኖራቸው እንደሚያደርግ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

አስተያየት