ግንቦት 17 ፣ 2010

ዐቢይና ዲርኣዝ

ፖለቲካ

ታላቁ ጩኸትየተማረ እንጂ የተባረከ መሪ ከለመንን ቆይተናል፡፡የተማረ ከተገኘማ በጣም ጥሩ ነው፤የተባረከ ይሁን እንጂ፡፡የተባረከ መሪ ከተገኘ ግን በጣም ጥሩ…

ዐቢይና ዲርኣዝ

 

  1. ታላቁ ጩኸት

የተማረ እንጂ የተባረከ መሪ ከለመንን ቆይተናል፡፡የተማረ ከተገኘማ በጣም ጥሩ ነው፤የተባረከ ይሁን እንጂ፡፡የተባረከ መሪ ከተገኘ ግን በጣም ጥሩ ነው፤ ባይማርም እንኳን፡፡ቴዲ አፍሮ የዛሬ 13 ዓመት ባሳተመው ጃ ያስተሰርያል የተባለው አልበም ሽፋን ላይ ታላቁ ጩኸት በሚል ከተቀመጠው የታናሽ ትልቅ መልዕክት ውሰጥ የተወሰደ ነው፡፡ዛሬ ኢትዮጵያ አዲስ ተብሎ የተነገረለትን መሪ ካገኘች ወደ ሁለት ወር እየተጠጋች ነው፡፡ ይህ ሰው አዲስ የሚያስብሉ ብዙ ነገሮች ሉት፡፡ እርግጥ ነው ሰብሮ የወጣው ከመነሻው አንስቶ ከተበላሸው እንቁላል ከኢህአዴግ ቅርፊት ነው፡፡ ይህ አዲስ ሰው ለመሆኑ ምንድነው? የተማረ? የተባረከ? የተማረም የተባረከም? የተረገመ?  የተረገመና የተማረ?ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አዲስ ከሚያስብሉት ጉዳዮች አንዱ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ከተካሄዱት ተቃውሞዎች ሁሉ ታላቁን ተቃውሞ ባስተናገደችና አገሪቱ በታላቅ የጥፋት ጩኸት በተናወጠችበት ጊዜ መጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘው ሰፊ የህዝብ ተቀባይነት ነው፡፡ በርካታው ለወትሮው ከየኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የመጣን ነገር ሁሉ እንደእርኩሰት ሲያይ የነበረው ተቃዋሚ ሳይቀር በዚህ ሰው ተማርኮ ታይቷል፡፡ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከረገጠ ጀምሮ ራሱን ህዝባዊ ነኝ ቢልም ክፉኛ የተራበው ነገር ቢኖር ደግሞ ህዝባዊ ተቀባይነትን ነው፡፡

 ታዲያ እንዴት ከዚህ ድርጅት መሃል የወጣ ሰው የዚህ ዓይነት ሰፊ ተቀባይነት አገኘ ብሎ ለጠየቀ መልሱ ብዙ የሚያነጋግር ሊሆን ይችላል፡፡ብዙዎች ዶ/ር ዐቢይን አገርን ሊያድን ከሰማይ የተላከ ሙሴ ሁሉ ነው ብለው ተቀብለው ይህንንም ሌሎች እንዲቀበሉላቸው ሲወተውቱ፤ ባንጸሩ ሌሎች ደግሞ ዐቢይ የእድሜውን ከፊል በላይ የኢህዴግን ጠጦ እየጠባ ያደገና  በመሆኑ ለውጥን ወደግንባሩ የሚያመጣ ሰው አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በሌላም በኩል ይህ ሰው ኢህአዴግ ውስጥም ቢያድግ ኢህአዴግነት እሱ ውስጥ አላደ­ገም እንዲያውም ኢህአዴግ በሱ ውስጥ ሞቷል፤ ጥቂት ጊዜ ካገኘም ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ ኢትዮጵያንም ይገድላል የሚል ጥቂት የማይባል ወገን አለ- እኔም ራሴን በዚህ ጎራ ነው የምድበው፡፡ ጥቂት ለማይባሉት ደግሞ ዐቢይ አገር የመለወጥ የሞራል ስብዕና ያልተላበሰ ስልጣንን በግርግር የመነተፈ አዋናባጅ ነው፡፡

  1. ከዐቢይ ምን አዲስ ነገር ተገኘ

ዐቢይን ኢህአዴግ አይደለም ብለው የሚያምኑ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ደፋር ድምዳሜ ላይ ምን አደረሳቸው ሲባሉ የራሱን የዐቢይን ንግግሮችና ጽሑፎች እንደአስረጅነት ይጠቅሳሉ፡፡ ከኢህአዴግ የመጣ ሰውን እንዴት በወሬ ይታመናል የሚል ጥያቄ ይከተላል፡፡ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች ትንሹ የረሱት ነገር ቢኖር ኢህአዴግ ሰውን በወሬ ሲወነጅል እንደነበረና፤ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ደግሞ እንዳይወሩ እቀባ የተደረገባቸው ወይ ደግሞ ከተወሩም ከዐቢይ ከምንሰማው በተቃራኒ እንዲሆኑ የተደረጉ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ነው፡፡

  1. የዲራአዝ ሁለት መጽሐፎች

ዶ/ር ዐቢይ ራሳቸው በአደባባይ ወጥተው እውነት ነው የለም ሃሰት ነው ብለው አይናገሩ እንጂ፤ እንኳን የመጨረሻዎቹ ሁለት ፊደሎች ዐቢይ የራሳቸው ስም እና ዝናሽ የባለቤታቸው ስም የመጀመሪያ ፊደሎች ፍንጭ ተገኝቶ ፤ዲርአዝ እንግዲህ የማን የብዕር ስም እንደሆነ የአዲስ አበባ ጎዳና ላይ የምታገኙትን ጫማ አሳማሪ ሁሉ ብትጠይቁት የሚነግራችሁ ጉዳይ ነው፡፡ዲርኣዝ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደ ድሃ ቀብር ተጣድፈው ከቤት የወጡ ሁለት መጽሐፍት ለአደባባይ አብቅቷል፡፡ ባለ 173 ገጹ እርካብና መንበር በታህሳስ 2009 የታተመ ሲሆን፤ ሌላኛው ባለ 122 ገፁ ሰተቴ ደግሞ በእ.ኤ.አ በ2016 እንደታተመ ይገልጻል፡፡ ሰውዬው በዚያ ቀውጢ ሰዐት ለምን ጊዜውን ሰውቶ እነዚህን የማይረቡ መጽሐፍት ወደገበያ እንዳመጣ የላይኛውና እሱ ራሱ ይወቀው፡፡ ሁለቱም መጽሐፍት የአማርኛ መጽሐፍት ቢሆኑም ምክንያቱ ባልታወቀ መልኩ የህትመት ጊዜያቸው የአንደኛው በኢትዮጵያ የሌላው ደግሞ በአውሮፓውያን አቆጣጠር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ 

በእውነቱ ለመናገር ሁለቱም መጽሐፍት ለንባብ እዚህ ግቡ ተብለው በቁምነገር የሚወሰዱ አደሉም፡፡ የመጽሐፍቱ ትልቁ ውበት ማነሳቸው ብቻ ነው! ይህ በእንዲህ እንዳለ ማሽቃበጥ የሚል ኮርስ የወሰዱ የሚመስሉ ጋዜጠኞቻችን ደግሞ ሰውዬው ለካ የስነ-ጽሁፍ ችሎታቸውም ለጉድ ነው እያሉ በየኤፍ ኤሞች ላይ ሲያወሩ መሰንበታቸው ያስገርማል፡፡በማነቃቂያ ንግግሮች (Motivational speech) የምናውቀው ዶ/ር ምህረት ደበበ እርካብና መንበር በተባለው መጽሐፍ ጀርባ ላይ የሚከተለውን አኑርዋል፡፡መንበር ከጠመንጃ አፈሙዝና አፈሙዝ ብቻ በሚፈልቅባት ሃገራችን፤ አመራር ጥበብ፤አመራር ዕውቀት ተደርጎ አይታሰብም፡፡ ደራሲ ዲራኣዝ ይህን ዘመን ያስቆጠረ ዕሳቤ በመለወጥ አመራር ሳይንስ፤መሪነት ጥበብ እንደሆነ በግል፤ በቡድን፤በማህበረሰብ ከዚያም ከፍ ብሎ እንደሃገር ራሳችንን ልናስተዳድርበት ስለሚገባው ጉዳይ ጠጣሩን የንድፈ-ሃሳብ ቋጥኝ አላልተው መሬት በማስነካት የመሪነትን ሚስጥር እንካችሁ ያሉናል፡፡መጽሐፉን ገልጸው ማንበብ ሲጀምሩ ዶር ምህረትን ምን ነካው ያስብላል፤በርግጥስ መጽሐፉን አንብቦታል ወይ የሚል ጥያቄንም ያጭራል፡፡ ከዚያ ይልቅ ምህረት መነሻው ላይ ጠመንጃን ማንሳቱ ጸሐፊው ወደጠመንጃ የቀረቡ ግን ለአመራር ምንም አያደርግልኝም ብለው የናቁ ሰው ናቸው የሚል ሹክሹክታ አለው፡፡  

ሁለተኛው አስተያየት ሰጪ ዶ/ር አብዱልረዛቅ ሙህየዲን ጭራሽ ይህን መጽሐፍ ከገ/ህይወት ባይከዳኝ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” እንዲሁም “ከከበደ ሚካኤል ጃፓን እንዴት ሰለጠነች” ጋር አወዳድሮ ይሄኛው የቀድሞዎቹ ያልነካኩትን ጉዳይ ሁሉ አዳርሶ መፍትሄ የሚያፈልቅ ትንግርት ነው ሲል ያሞካሸዋል፡፡እንደኔ ይህን መጽሐፍ ያነበበ ዲርኣዝን ብዙ አያከብረውም፡፡ ከሁለቱም መጸሐፍት ላይ አንባቢ የሚገነዘበው ጉዳይ ቢኖር ዲርኣዝ ለአቅመ መጻፍ ያልደረሰ፤ ጠግቦ ያላነበበ ወይ ደግሞ ያነበበው ነገር አጥግቦና አስገስቶ ያልተዋሃደው መሆኑን ይረዳል፡፡ ብዙ የሚያነሳቸው ነገሮች በሳይንሳዊ መጠይቆች የተሟሉና ለውይይት ወይም ለክርክር የሚጋብዙ፤ ከጥልቅ ንባብ የተቀዱ ትንታኔዎች ሳይሆኑ፤ እንዲህና እንዲያ ቢሆን ጥሩ ነው የሚሉ የእሳት ዳር የሞራል ወጎች ናቸው፡፡በሶስት ክፍሎችና በሰባት ምዕራፎች የተዋቀረ የሚመስለው እርካብና መንበር የአመራር ጥበብ ነው ተብሎ ይቅረብ እንጂ ውስጡ ሲገባ የሚገኘው ፖለቲካም፤ ታሪክም (የውጭ ታሪክን ጨምሮ)፤ ርዕዮተ ዓለም፤ የሃይልና የስልጣን አጠቃቀም በአምባገነኖችና በሰላማዊ ታገዮች ዘንድ፤ ሌሎችም ብዙ ነገሮች የታጨቁበት ሁሉን ካለስርዓት አደባልቆ  የኔ ቢጤ አቆፋዳ ነገር ነው፡፡ 

ለምሳሌ በክፍል አንድ የምዕራፍ ሁለት ርእስ ጀግንነት፤ ጀብዳዊ ጭካኔና ጀብዳዊ ቅንነት ይላል፡፡ ሲጀምር እነዚህን ስያሜዎች በአግባቡ ተገልጸው አይደለም ወደዝርዝር የሚዘልቁት፡፡ እንዲሁ ግን አንባቢ ጸሐፊው በቀጣይ ምዕራፍ እየደጋገሙ ያነሱትን የማኪያቬሌን ‘መስፍኑ’ የተባለ መጽሐፍ በማሰብ ጀብዳዊ ጭካኔን  (meanness) እና  ጅብዳዊ ቅንነት (generosity) ያሉት ተብሎ ሊተረጉመው ይችላል፡፡  ምእራፉን በሚከተለውያልዘሩት አይበቅልም ፈሪ ሰው አልወድም ያልገደለ አልወድም አብሬው ስተኛ ይመስለኛል ወንድም፡፡የመሳሰሉ በተለምዶ በሰሜን ኢትዮጵያ በአማርኛ ተናጋሪው አካባቢ የሚታወቁ የሂድ ተዋጋ ግጥሞች ይጀምራል፡፡ ይህንን ግጥም ደራሲው በአገራችን ህብረተሰብ ሲቀነቀን የኖረ ሲሉ እንዲሁ በደፈናው ያስቀምጡታል፡፡ ምእራፉ ምንም አያወራም ልንል እንችላለን በገሃድ የሚታወቁትን አነሂትለርን፣ ማሀተማ ጋንዲን፣ ማንዴላን እና ሙጋቤን በአንድ ሁለት መስመር እየደጋገም ከማንሳቱ ውጪ ፡፡ ምንም፡፡ከዚያ ይልቅ በምእራፍ ሶስት ከገጽ 35-38 ላይ ያነሳውን የማኪያቬሊን መስፍኑን ይሁን የራሱን የስልጣንና የሃይል አመለካከት ውይም ፍልስፍና እንደሚያወራ በማያሳውቅ ሁኔታ የሚያስፈሩ ዓረፍተ ነገሮችን አስቀምጧል፡፡«እንዳንድ ጊዜ በፍቅር ላይ የተመሰረተ ግዛት ልል ነው፡፡በውዴታ የተሳሰረን ሰንሰለት መበጣጠስ ቀላል የሚሆንበት ጊዜ ያለ ሲሆን ፍራቻ ከታከለበት ግን ሁኔታዎች ምንም ሆኑ ምን ቅጣቶችን በማሰብ በወላዋይነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ 

ይህ የሚሆንበት ምክንያት የሰው ልጅ በተፈጥሮው ምስጋናቢስ፤ ከዳተኛ፤ድብቅ እና ብዙ ለማግኘት የሚመኝ መሆኑ እንደሰበብ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡»ይህን በገጽ 35 ላይ ይልና ዝቅ ብሎ ደግሞ ስለዚህ ከፍቅር ይልቅ በትር ለመከበር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ይላል፡፡ገጽ 38 ላይ ደግሞ«እንደ ውሻ ጠላት ላይ በመጮህ ማምለጫን ማመቻቸት ዘላቂ መፍትሄ ባይሆንም ለጊዜው ይጠቅማል፡፡ምክንያቱም እንዳይመለስ ሆኖ ያልተሸኘ ጠላት ጊዜ ጠብቆ ዳግም ለማጥቃት እንደሚመጣ ጥርጥር የለውምና፡፡ታዲያ ጊዜው ሲደርስ ልክ እንደነበር ኮቴ ሳያሰሙ ከጀርባ ቀብ ማድረግና ህልሙን ባንድ ጀምበር ማምከን መረሳት የለበትም፡፡»እርካብና መንበር ነገርን እያወዙ ለማቅረብ በሚደረግ መውደቅ መነሳት በብዙ ተረቶችና ምሳሌዎች የተሞላ ነው፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ የተነሳውን ሃሳብ ርእስ ሊገልጹ አቅም የሌላቸውን ያለፉ የነገስታት ታሪኮች ካለዝግጅት እየቃረመ አምጥቶ በየገጹ ላይ በትኗል፡፡

  1. ኒዮ ሊበራሊዝምና ዶ/ር ዐቢይ

የመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ ኒዮ ሊበራሊዝም ይነሳል፡፡ የኒዮ ሊበራሊዝምን መጥፎነት ኢህአዴግ ለአንዲት ድሃ ባልቴት ለማስረዳት ብዙ ሲደክም እንዳልኖረ፤ ዐቢይ ግን በአግባቡ እንኳን ሳይረዳው በአያ ጅቦና ጦጢት ተረት ተረት ሊገልጽ ሲታገል ይታያል፡፡ምን ጥቁር ቢበሉ ነጭ ነው ኩስዎ  እያለ፡፡ ቢያንስ ብዙዎቹ የልማታዊ መንግስትነትን የሚያቀነቅኑ የኢህአዴግ ሰዎች ያነበቡትን የ Ha-Joon Changን Bad Samaritans ሳያነብ ሰው እንዴት ስለዚህ ጉዳይ ሊጽፍ የሚነሳ ከቶ ሊኖር ይችላል? ማንም አይችልም፡፡ አቶ ዐቢይ እንጂ!!

ከዲርዓዝ ቁምነገር ፍለጋእርካብና መንበር ድንገት ብልጭ እያለበት በየመንገዱ የሚያነሳቸው ከኢህአዴግ ትርክት የተለዩና ብዙውን ኢትዮጵዊ ልቡን ሊያሞቁ የሚችሉነጥቦችን እዚያም እዚህ ወርውሯል፡፡የመጽሐፉ መቅድም ላይበምንም ዓይን ቢታይና ቢፈተሸ ልብን በኩራት መሙላት የሚችል ጥንታዊ ስልጣኔና እልፍ ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ የተላበሰች ሀገር ባለቤቶች ስለመሆናችን ኢትዮጵያዊያን መስካሪ አያሻንም፡፡ እናወቃለን፤ ያውቃሉ፡፡ገጸ 59«በዘመነ መሳፍንት ብጥስጥሷ ወጥቶ ዜጎቿም በየጎጡ በሚበቅሉ ሽፍቶችና ነፍጥ አንጋች በነበሩበት መኳንንቱና መሣፍንቱ መከራና ፍዳቸውን ያዩ በነበረበት ጊዜ ነበር የቋራው ልጅ ካሳ ብቅ ያሉት፡፡»ገጽ 73አስተዋይነት አጥርና ድንበር አልፎ ሰውነትን ማክበር ወዲህ በቅርቡ ዘመን ታሪካችንም ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ከማን ጋር ከተባለ…ከአጼ ምኒልክና ከጅማው አባጅፋር ዝምድናና ወዳጅነት ውስጥ የሚል ይሆናል ምላሹ፡፡በምኒልክ ቤተመንግስት ለአባጅፋር ክብር ሲባል የእስላምና የክርስትያን ገበታ ጎን ለጎን በግራና በቀኝ ቀርቦ የነበር መሆኑን የምናውቅ ስንቶቻችን እንደሆን አላቅም፡፡እንዲህና እንዲህ የመሳሳሉ ኢህአዴግ ውስጥ ካለ ሰው ፈጽሞ የማይጠበቁ ነገሮችን መጽሐፉ ይዟል፡፡

  1. የዐቢይ ንግግሮች የኢህዴግ ትርክት መቀየር

ዐቢይ በንግግሮቹ ሰው ሆኖ ነው የመጣው፡፡ በመጀመሪያ ቀን ንግግሩ ስለእናቱ ሲያነሳ በፓርላማው ውስጥ ባልተለመድ መልኩ እናት የፓርላማ አባላት በነጠላቸው ጫፍ ዓይናቸውን ሲጠርጉ ይታዩ ነበር፡፡ ዐቢይ እርግጥ ነው ሰውኛ ከመሆን ውጪ ብዙ አማራጭ ያለውም አይመስልም፡፡ ወጣት ከመሆኑም በላይ በኢህአዴግ ከፍተኛ አመራርነት ብዙ አልቆየም፡፡ ከዚህ በላይ ግን የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ከሰውነት ብዙ ያራቃቸውን የማርክሲዝም ሌኒንዝምን ንባብ አያውቀውም፡፡ 

ከሞላ ጎደል በንግግሩ ሲያተኩርባቸው ከቆዩት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-ኢትዮጵያዊ አንድነትየኢትዮጵያ ህዝብ የቆየ አንድነት ታሪክ ለኢሀአዴግ ብዙ የማይዋጥለት ከመሆኑም በላይ፤ ይህን ታሪክ አጉልቶ መናገር፤ አዲሲቱ ብሎ የሚጣራትን በብሔሮች መልካም ፈቃድና ጋብቻ በ1983 ተጸንሳ በ1987 ላይ የተወለደችውን የወጣቷን ኢትዮጵያ ትርክት ማበላሸት ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊነትን በተቻለው መንገድ ሁሉ ተጣጥሎ ሲያበቃ፤ ብሔር ብሔረሰቦች የበቃ የምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ከፈለጉ ያንሱት፤ ከፈለጉም በየፊናቸውና በየመድረሻቸው ይሂዱ ነበር አዲሱ ትርክት ማብቂያው፡፡ 

ለዚህም ነበር ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን ጮክ ብሎ መጥራትም ሆን አድምቆ መጻፍ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚያስብልና የሚያስቀስፍ ወንጀል የመሰለበት ጊዜ የሆነው፡፡ መጀመሪያ አቶ ለማ መገርሳ፣ የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ቀጥሎ ዶ/ር ዐቢይ ነበር ይህን ትርክት የሰበሩት፡፡ የትርክቱ መሰበር አልነበረም ድንቁ ነገር፡፡ ይህን ነገር ትላንት ጠባብና አገር ከፈረሰ በነሱ ነው ተብሎ ሲነገርለት ከነበረው ከኦሮሞ አመራሮች መውጣቱ ነው ብዙውን ህዝብ በእንዴት ሊሆን ቻለ ብሎ እጁን በአፉ ያስጫነው፡፡የአቶ ዐቢይ የመጀመሪያ ቀን ንግግሮች በደምሳሳው ብዙ ሰውን ከተደፋበት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ አውጥቶታል ማለት ይቻላል፡፡ ይችን ለአምስት ደቂቃ በጥሞና ካሰብኳት የምታስለቅሰኝን ታላቅ አገሬን፤ ደጋግመው ሲያነሱ፤ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵዊው ልብ ውስጥ እንዴት መስወጣት ይቻል ይሆን ብለው ሲጠይቁ፤ አባት እናቶቻችን አንተ ይሄ ነህ አንተ ከዚህ ነህ ሳይሉ በየአቅጣጫው መውደቃቸውንና የኢትዮጵያን መሬት ብሄር ሳይሆን ኢትዮጵያ እንዳደረጉት ሲናገሩ እንባዬ መጥቷል፡፡ የጎሳ ብሔርተኝነት አሳንሶ መንደር ይከታል ሲሉ፤ ትልቋን ኢትዮጵያ እናወድስ ሲሉ የብዙውን ልብ አሙቀዋል፡፡የዜጎች ክብርሌላኛው የኢህአዴግ በደል የዜግነት ክብር ነበር፡፡ ብዙ ሰው ኢትዮጵዊ ሆኖ መፈጠር ያፈረበት ጊዜ ቢኖር ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ናቸው፡፡ ኢህአዴግ እዩልኝ ልማትና ዴሞክራሲዬን እያለ ሲጮህ ጆሮውን ይዞ ለስደት የሚሸሸው ዜጋ እጅግ ብዙ ነበር፡፡ ይህ ዜጋ በመንገዱ ላይ አፉን ከፍቶ ከሚጠብቀው አውሬና አሳነባሪ ተርፎ መድረሻው ሲደርስ ረክሶ የመጣ ፍጥረት ነውና ፤የታሰራል ፤ይገደላል፡፡ ዜጎች ታረዱ ብለው አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ልውጣ ያሉ ዜጎች እየተካለቡ መባረራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን የቆየ የልብ ቁስል የተረዳ ሰው ማነው ቢባል አቶ ዐቢይ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ይመስላል በተመረጠ በሁለት ወራት ውስጥ በጎረቤት አገሮችና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ዜጎችን ከእስር ሰንሰለት ማስለቀቅ የመረጠው፡፡

 ቅድሚያ ዜጎቻችንን አክብሩልን ስንል ነው ያከበሩን አለ፡፡ ለወትሮው ኢህአዴግ ይህ የሚያሰጨነቀው አልነበረም፡፡ ይልቁን ዜጎችን በባዕድ ሰዎች አሳፍኖ አምጥቶ መግረፍ ነበር የሱ ክብሩ!! ዐቢይ ግን ዜጎቻችንን ስናከብር እኛም ተከበርን አለ፡፡ትምህርትስለትምህርት የተናገረውም ቢሆን ከትምህርት ጠሉ ኢህአዴግ አቋም ጋር የሚሄድ አደለም፡፡ ኢህአዴግ እግሩ አዲስ አበባ እንደደረሰ ከተማሪ ጋር ብቻ ሳይሆን ከትምህርት ጋር ነው የተጣላው፡፡ የምሁር ትምክተኞች በሚል ምሁራንን በማሳደድ የተጀመረው ታሪካዊ ወንጀል ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ መማርን አማራጭ ሲጠፋ የሚፈልጉት አሳፋሪ ነገር አድርጎታል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ይህንን ማፈሪያ ነገር ነው የኩራት ምንጭ አደርጋለሁ ያሉት፡፡ ውድድር ነውር አደለም፡፡ በውድድሩ የላቀውንም እንሸልማለን፤እንደ ጥንቱ እናከብራለን ሲሉ ልቡን የማይሰጥ ኢትዮጵያዊ ጥቂት ነው፡፡

  1. ዐቢይና ንባብ

ኢህአዴግ አናት ላይ የተቀመጡት ግለሰቦች የኋላ ስብእናቸው ማርኪስሰት ሌኒንስት ላይ የበቀለ ነው፡፡ የችግር ሁሉ መፍቻና መተንተኛቸው ሁሉ የተነሱበት የማርከሲስም ሌኒንዝምና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነበር፡፡ ለነሱ ደግሞ ማርክሲስም ሌኒንዝምን አንብቦ ማነብነብ የእውቀት መለኪያ ብቻ ሳይሆን የመሪነት መመዘኛም ነበር፡፡ ህይወት ተፈራ Tower in the sky በተሰኘው እና ‘ማማ በሰማይ ላይ’ በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በተለመለሰው መጸሐፏ እንደምትነግረን የአመራር ቦታውን የሚወሰድ ሰው፤ ከሁሉ በላይ ማርክሲዝምን ያነበበው እሱ ነበር፡፡ 

የቅርቡ የ1993ቱ የህወሃት ‘እንፍሽፍሽ’ ወቅት መለስ ዜናዊ የተቃራኒውን አንጃ ቋንጃ ሊሰብር ከተጠቀመበት መላ መካከል አንጃውን በፖናታርቲዝም ማቆጥቆጥ ስም መክሰስ ነበር፡፡ መለስ የ1993ቷ ኢትዮጵያ የ19ኛው ክፍለዘመን አጋማሿ ፈረንሳይ መሰላ ታየችኝ ብሎ ድርቅ አለ፤ እሰኪ ልብ ብላችሁ ተመልከቷት እያለ አንጃው ላይ መቀለድም ጀመረ፡፡ የቀድሞ የትግል አጋሮቹንና የዚያን ጊዜ ባላንጣዎቹን የለብ ለብ ማርክሲስት ሌኒንስት ግርፍነት ስለሚያውቅና ፤ አንድን ማርክሲስታዊ ሃሳብ መለስ ቀድሟቸው የሸመደደ ከመሰላቸው  እየተራወጡ ወደ ግሩፕ ንባብ እንደሚገቡና ዋናውን ጉዳይ እንደሚረሱለት ስለገባው ይሆናል፡፡ አቶ ገብሩ በመጽሐፋቸው ‘ክርክሩ ሄዶ ሄዶ የቦናፓርቲስት ስርዓት አካል ተደርጎ የተወሰደውን የኢትዮጵያን ወዛደር የሚያቀረሽ ጨቅላ ነው የለም የለም ለሃጩን የሚያዝረበርብ ህጻን ነው’ ወደሚል የለየለት የምርቃና ወሬ ድረስ ወርዶ እንደነበር ገልጸውልናል፡፡ ከዚህም በላይ መለስ አረጋሽን ‘በደንብ አላነበብሽውም ምኑም አልገባሽ ገና’ እያለ እንደአንድ ፍሬ ልጅ በየስብሰባው መሐል ያስለቅሳት እንደነበር እዛው የገብሩ መጽሃፍ ላይ ስናነብ፤ መለስ ምንያህል ማርክሲስት ባልንጀሮቹን ቀድሞ ባነበበው ነገር ሊያበሽቃቸው እንደፈለገ እንገነዘባለን፡፡

ዛሬ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር እንኳን ማርኪስዝም ሌኒዝምን የችግር መተንተኛ ሊያደርጉ ይቅርና የስቴቨን ኮቬይን the 7 habits of highly effective peopleን ለካበኔ አባሎቻቸው በፓወር ፖይንት ሲያቀርቡ የማያፍሩ ናቸው፡፡አቶ ዐቢይ ብዙ ችግር የተበተባት የመቶ ሚሊዮን ህዝብ አገር ጠቅላይ ሚንስትር ሳይሆን የመቶ ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ማናጀር መስለው በዋሉበትና  የካቢኔ አባሎቻቸውን የስራ መመሪያና የፓወር ፖይንት ስልጠና በሰጡበት ውሏቸው፤ የጊዜን አጠቃቀም ከላይ ከተጠቀሰው መጽሐፍ ገጽ 151 ላይ ወስደው ለማስረዳት ሲሞክሩ ነበር፡፡ ሰው ያነበበውን ነው የሚመስለው መቼም፡፡ ደፍሮ የሚመረምርና የሚናገር ካለ ምንም እንኳን መሪነት ሙሉ ለሙሉ የንባብና የትምህርት ውጤት ባይሆንም አቶ ዐቢይ ብዙ አልተማረም ብሎ መደምደሙ አይቀርም፡፡ከዐቢይ ንግግርና ጽሑፍ የምንረዳው ቢኖር ንባቡ ብዙ ያልጠለቀና፤ በጥልቀት ሊያነበው የሞከረው ነገር ካለም የማነቃቂያ መጽሐፍት መሆናቸውን ነው፡፡በመግቢያዬ የጠቀስኩት የድምፃዊው ‘የተባረከ መሪ ከተገኘ ግን በጣም ጥሩ ነው፤ ባይማርም እንኳን’ የሚል ፀሎቱ ይሁንለት አይሁንለት ለማረጋገጥ ለጊዜው ማለት የሚቻለው የሰው ሆዱን የወፍ ወንዱን የት አውቀነው ብቻ ነው፡፡

አስተያየት