መጋቢት 19 ፣ 2010

ሀገር በቀል ቅኝ ግዛት

መጽሓፍትኑሮ

ርዕሰ፡ Native Colonialism: Education and the Economy of Violence Against Traditions in Ethiopiaጸሐፊ፡…

ርዕሰ፡ Native Colonialism: Education and the Economy of Violence Against Traditions in Ethiopiaጸሐፊ፡ ይርጋ ገላው ወልደየስገጽ ብዛት፡ 236አሳታሚ፡ The Red Sea Press  ከርዕሱ በመነሳት መረዳት እንደሚቻለው የጥናት ባለሙያው የይርጋ ገላው መጽሐፍ ዋና ሃሳብ ኢትዮጵያውያን በቀጥታ ቅኝ ባይገዙም እንኳን ሀገር በቀል ቅኝ ግዛት ስር መውደቃችቸውን ማሳየት ነው። ጸሐፊው ከሁለት መቶ በላይ ገጾችን በያዘው መጽሐፉ ኢትዮጵያውያን ለቅኝ አገዛዝ የተዳረጉት በዘመናዊ ትምህርት አማካኝነት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ይርጋ ለአውሮፓ ዕውቀት በፈጠርነው አመለካከት የራሳችንን በንቀት በማጥፋት እና በማስወገድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የዕውቀት መሰረቶችን ዋጋ ቢስ አድርገናቸዋል በሚል ማዕከላዊ ሀሳብ ይከራከራል።በስድስት ምዕራፎች የተዋቀረው በታሪካዊ አተራረክ ስልት የተዋቀረው መጽሐፍ በሴማዊ ጥናት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ መቅድም ይጀምራል። ፕሮፈሰሩ በመቅድሙ ‘በዘመናዊት ኢትዮጵያ ውሱን የትምህርት ፍልስፍና የፈጠረውን ችግር በስርዓት የተነተነ የማውቀው የመጀመሪያው ሰው ይርጋ ነው’ ይላሉ፡፡እውቀትን በመረዳት ዙሪያ በማተኮር ጥናቶችን የሚያደርገው ይርጋ ገላው ወልደየስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ሀገራዊ አብርክቶነት ለዘመናት ተዘርግቶ የነበረው ትውፊታዊው ትምህርት ዘዴዎችን በማስተዋወቅ ዘመናዊ የት/ት ዘዴያችንን አመጣጡን፣ ስርዓቱን እና ከባህላዊ የትምህርት ዘዴያችን ጋር ያለው ግንኙነት እና ልዩነት ያቀርባል።“ማዕከልነት” (Centerdness) እና “ጥልቅ መሰረትነት” (rootedness) በሚል የሚያነሳቸው ሁለት ሀሳቦች ምን ያህል ለአንድ ግለሰብ አስፈላጊ እንደሆኑ በማስረገጥ ዘመናዊ የትምህርት ዘዴያችን የገባበትን ችግር ያመላክታል። መጽሐፉ የcolonial and post-colonial [የቅኝ አገዛዝ እና ድህረ- ቅኝ ግዛት ጥናቶች] ስር የሚገኙ አፍሪካዊም ሆኑ ሌሎች አለም አቀፍ ምሁራንን ሀሳቦች ከኢትዮጵያ ጋር በማገናኘት ያቀርባል። እነዚህ ጥናቶች ኢትዮጵያ ቅኝ ስላልተገዛች ከስራዎቻቸው ሀገራችንን ሲያካቱ እምብዛም አይታዩም። እነሙዲምቤ፣ ምቤምቤ፣ ንጉጊ ወዘተን ከኢትዮጵያ የነጻነት ታሪክ ጋር አዛምዶ አቅርቧል። ለይርጋ የኢትዮጵያውያን ቅኝ ባለመገዛታቸው ያላቸው ኩራት በሀገር በቀል ቅኝ አገዛዝ ተፈትኗል። የተማረውንም የማኀበረሰብ ክፍል የቅኝ ተገዢነት መንገድ ጠራጊ ‘agents of colonization’ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ለማሳየትም ይሞክራል።የኢትዮጵያ ስርዓተ ትምህርት ችግሮችን በሚነቅሱ የምርምር ጽሑፎቻችው ከሚታወቁት ተከስተ ነጋሽ እና ሙሉጌታ ወዳጆ ጋር የሚስማማው ይርጋ ትምህርት እና ዕውቀት በመሰረታዊ ደረጃ ከሕዝቡ ባሕላዊ አኗኗር ጋር የተቆራኘ ሲሆን ጠቃሚ ይሆናል ባይ ነው። በተጨማሪም መጽሐፉ እንደመንደርደሪያ የሚያነሳቸው ‘ዕውቀትን ለትህትና’ እና ‘ዕውቀትን ለስልጣን/ሀብት ማካበቻ’ ብሎ የሚጠራቸው ሁለት ሀሳቦች ከትረካው በተጨማሪ ጽሑፉን ተጨማሪ መዋቅር (frame-work) ይሰጡታል።በታሪክ ደረጃ ይርጋ የአጼ ቴዎድሮስን፣ የምንይልክን እናም የኃይለሥላሴን ዘመን መንግስታት የትምህርት ዘዴዎችን እናም የስልጣኔን መለኪያዎች በመዳሰስ ከቴዎድሮስ በኋላ ኢትዮጵያውያን የመፍጠር ሳይሆን የመኮረጅ፣ የማሰብ ሳይሆን የመቅዳት ዘይቤዎችን እንዳዳበሩ ያመላክታል።በምንይልክ ዘመነ መንግስት በት/ት ዘርፍ የመጀመሪያው ዘመናዊ ት/ቤት ተከፈተ። ዳግማዊ ምንይልክ ትምህርት ቤትም ባህል እና ፈጠራን ጎን ለጎን ለማስኬድ ታስቦ የተከፈተ ተቋም ነበረ። የውጭ ቋንቋዎችንም ለተማሪዎች በማስተማር የመንግስት ሰራተኞች እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሀገሪቷን ሊረዱ የሚችሉ መጣቶችን ማፍራት ነበረ አላማው። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት እንዲልኩ የተደረገው ትውፊታዊውን ባሕል ለማስወገድ ሳይሆን የማራመድ ዓላማ ተይዞ ነበር። በምንይልክ ዘመነ መንግስትም የተፈጠረው የተማረ ትውልድ በጥቅሉ ለሁለት ተከፍሎ (አውሮፓ ቀመስ እና የቤተክህነት ቀመስ ተማሪዎች) ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት የትምህርት ዘዴ ለመቀየስ ይንቀሳቀስ ጀመር። ነገር ግን የውጭ ትምህርት ብቸኛ የዕውቀት ሚዛን ሆኖ አይታሰብም ነበረ በማለት ይተርካል።ተፈሪ መኮንን በኋላ ላይ ከሚሺነሪዎች ጋር ከነበራቸው ቅርበት ሳቢያ የተለያዩ የፈረንጅ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ አድርገዋል። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ምንም አይነት አስተዋፅዖ እንድታደርግ አልተጠየቀችም ነበር። ቀስ በቀስም ት/ት ላይ የነበራት የበላይነት እየተሸረሸረ ሄዶ ከጣልያን ወረራ በኋላም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ እንደተቋቋመ ኃይለሥላሴ የትምህርቱ ዋና አላማ የሕዝቡን ጥንታዊ ማንነት ከዘመኑ ጋር ማካሄድ ነው ብለው ቢናገሩም ይርጋ ከዩኒቨርሲቲው መቋቋም እስከአወቃቀሩ ድረስ ኢትዮጵያውያን ኢምንት ሚና እንደነበራቸው ያሳየናል ብሎ ይሟገታል። መምህራኑ በብዛት ከውጪ የመጡ ሲሆኑ ትምህርቱ ከውጭ የተቀዳና በእንግሊዘኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የሚስጥ ነበር። ሌላው በመጽሐፉ የተገለጸው በትውፊታዊው ስርዓተ ትምህርት የአውራነት ድርሻ ያላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊው ትምህርት የተነፈጋት ተሳታፊነት ነው፡፡ ጉልህ ድርሻ ሊኖራት ሲገባ የራሷ ቤተክርስትያኗ ትምህርት በኮሌጅ ተዋቅሮ ፈረንጅ መምህራን ተቀጥረው በእንግሊዘኛ እንዲያስተምሩ መደረጉን መጽሐፉ ይነቅፋል።እንዲህ እያለ በታሪካዊ ስልት የኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቅኝ ግዛት ውስጥ መነከር ከተረከ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት በተማሪዎች ላይ የሚያመጣውን የተለያየ ተጽዕኖ ይገልጻል። አንዱ መገለል ሲሆን፥ ይርጋ ፊደላዊነት/ልሂቃዊነት ‘eliticism’ ብሎታል፡፡ ዕውቀትን ለትሕትና በሚጠቀም ማህበረሰብ ውስጥ እውቀትን ለስልጣን እና ለሀብት ማካበቻ መጠቀሚያ ሲደረግ ይህ መገለል ይፈጠራል ። ትንሽ ተማርኩ የሚለው ሁሌ ተጠቃሚ እና የሀገሪቷን ጥያቄዎች ብቸኛ ፈቺ እና ተረጂ ነኝ ማለቱም የዚህ ሌላ መገለጫው ሊሆን ይችላል። ሰፊው ማህበረሰብ የሚኖርበትን ዘይቤ፣ አስተሳሰብ ወዘተ የማያውቀው ቢሆንም እንኳ ይህ ልሂቅ ለህዝቡ የሚጠቅመውን አውቃለሁ ባይ ነው። የትምህርት ዘዴው ከማህበረሰቡ አዋዋል እና አኗኗር የተነጠለ፣ ለማህበረሰቡ አስፈላጊ የሆነውን ያልተረዳ፣ ህዝቡ የቸገረውን እና የጎደለውን የማያውቅ ነገር ግን አለም አቀፋዊ ዕውቅና የያዘ/የተቀበለ ስለሆነ ብቻ ‘ህዝቡ ኋላቀር ተማሪው ፈርቀዳጅ’ የሚሆንበት ዘዴ ተፈጥሯል። ፊደላዊው ልሂቅ በጥቂቱ የአውሮፓ ትምህርት የተማረ የተከበረ ከመጣበት ማህበረሰብ የተነጠለ በብዛትም የተገለለ ነው።የቅኝ ግዛት ዋነኛ ስራ ቅኝ ተገዢው ስለራሱ ያለው ግምት እንዲወርድ፣ ከአውሮፓ የመጣ ነገር ሁሉ የሚበልጥ እንደሆነ ማሳመን እና የተለየ ርዕዮተዓለም ሊኖር እንደሚችል እንኳን እንዳያስብ ማድረግ ነው። በሀሳብ ቅኝ መገዛት እንደማለት። ይህ የሚታይበት ዋነኛው መንገድም ከዚህ በታች ሰፍሯል። የተከታይነት አባዜ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ከአውሮፓዊ ምሁራን በታች አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የቤተክህነት ምሁራን ሳይንሳዊ እንዳልሆኑ እና ለሀገሪቷ ከሀይማኖት ውጪ ምንም ፋይዳ እንደሌላቸው አድርገን መሳል ስልጣኔን የሚታሰብበት መልክ እራሱ እንዲንሻፈፍ አድርጓል። በዕውቀት እና ስልጣኔ መሀል ያለውንም ግንኙነት አዛብቷል። ለምሳሌ፤ ማይምሬ መና ሰማይ የተባሉ ምሁር ‘በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ (ቴዎድሮስን ሳያካትት) ስልጣኔን ጎትቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስገባት የተመኘ እንጂ ኢትዮጵያን ለማሰልጠን የፈለገ የለም’ ይላሉ።‘ኢትዮጵያን ማሰልጠን’ ሲሉ ኢትዮጵያውያን በሚያምኑባቸው እሴቶች፣ ፍላጎቾች እና አቅም ረገድ የታነጸ እና በምን ያህል ት/ቤቶች ወይንም ሆስፒታሎች ተቋቋሙ የሚሉ ጥያቄዎች ሳይሆን ት/ቤቶች ውስጥ ተማሪው ምን ዕውቀት ገበየ ወይንም ሰው በአስተሳሰብ ምን ያህል ተራመደ (ከብዙ በጥቂቱ) የሚሉትን ጥያቄዎች ይዞ የሚመጣ ነው።‘ስልጣኔን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት’ ግን ከዚህ ይለያል። እንደሳቸው ገለጻም ከሆነ ከይርጋ መጽሓፍ የሚታየው ባህላዊ እሴቶችን እና ተቋሞችን የሚደመስስ፣ ህዝቡን ማዕከላዊ ያላደረጉ ተቋማትን ለመተካት የሚሞክር፣ ሞክሮም ብዙ የማይሳካለት ሂደት ነው። ከውጭ በቁሳዊ ስልጣኔ ሄደዋል የሚባሉ ማህበረሰቦች እንደ ብቸኛ አዋቂዎች በመጠቀም ሃሳቦችን በመበደር እና በመዋስ መንቀሳቀስን ያበረታታል። የማኀበረሰቡ ጥያቄ የተረዳው ሳይኖር መልሱን መዋስን ያለማምዳል። የይርጋ መጽሃፍም ሆነ ጋሽ ማይምሬ በዕውቀት ዘዴ እንደ አዲስ መዋቀር እና መሻሻል ይህን ሊያስተካክል እንደሚችል ይጠቁማሉ። ስልጣኔ እና ባህል እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ ሳይሆኑ ሊደጋገፉ የሚችሉ ሀሳቦች ናቸው:: ይህንንም በማለት ይርጋ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ መምህራንን እና ምሁራንን እንዲሁም ሰፊውን ማህበረሰብ ስለእውቀት ማግኛ ዘዴዎች እና መንገዶች እንድናስብ እየሞገተ መጽሐፉን ይዞ ብቅ ብሏል።መልካም ንባብ።

አስተያየት