ሐምሌ 13 ፣ 2012

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፎቶግራፈር በክራይስለር የአርት ሙዝየም ስራውን ማሳየት ጀመረ

ኑሮፎቶፊቸርኹነቶች

ዘ ዋሺንግተን ፓይልት የተሰኘው መካነ ድር ባሳለፍነው አርብ እለት ይዞት በወጣው ዘገባ እንደዘገበው ከሆነ ትውልደ ኢትጵያዊው አሜሪካዊ ፎቶግራፈርና…

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፎቶግራፈር በክራይስለር የአርት ሙዝየም ስራውን ማሳየት ጀመረ
ዘ ዋሺንግተን ፓይልት የተሰኘው መካነ ድር ባሳለፍነው አርብ እለት ይዞት በወጣው ዘገባ እንደዘገበው ከሆነ ትውልደ ኢትጵያዊው አሜሪካዊ ፎቶግራፈርና ዳይሬክተር ዳዊት ኤን ኤም (Dawit N.M) በዝነኛው ክራይስለር የአርት ሙዝየም የመጀመርያ ኤግዚቢሽኑን ዘ ዓይ ዛት ፎሎውስ ፎቶግራፍስ ባይ ዳዊት ኤን ኤም (The Eye That Follows: Photographs by Dawit N.M) በተሰኘ ርዕስ ማሳየት ጀምሯል። በወቅቱ ኑሮውን በኒው ዮርክ ሲቲ ያደረገው የ24 አመት ትውልደ ኢትዮጵያዊው፣ በዝግጅቱ ላይ ያቀረባቸው ስራዎች በኖርፎክ ቨርጂንያ የሚገኙትን የመካነ ሂወት አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ቤተክርስትያንና የቅድስት አርሴማ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ጨምሮ በሎስ አንጀለስ፣ ኒው ዮርክና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተነሱ ፎቶዎችን ያካትታሉ። በፎቶግራፊ ጋዜጠኝነትና በአብስትራክት ፎቶግራፊ ዘርፍ የሚመደቡ ከ50 በላይ ፎቶግራፎችን የያዘው የዳዊት ዝግጅት፣ ሓምሌ ወርን ጨምሮ እስከ ነሓሴ አጋማሽ እንደሚታይ መረጃው ያሳያል። በታዋቂዎቹ የኒው ዮርከርና ቮግ መጽሔቶች ፎቶዎቹን በተለያዩ ወቅቶች ማሳየት የቻለው ወጣት ከፎቶግራፍ ስራዎቹ በተጨማሪ በዳይሬክተርነትም የተለያዩ ስራዎችን  መስራቱ ይታወቃል። በዚሁም ዘርፍ በ2011 የአሜሪካ ብላክ ፊልም ፌስቲቫል የምርጥ አዲስ ዳይሬክተር ሽልማትን ለዳዊት ማበርከቱም ይታወቃል። በወቅቱ ሽልማቱን የተበረከተለት ዘ ጃንግል ኢዝ ዘ ዌይ አውት (The Jungle Is The Only Way Out) በተሰኘው የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሙዚቀኛ መረባ የሙዚቃ ስራ ላይ በሰራው የዳይሬክቲንግ ስራ መሆኑ ይታወቃል።ዳዊት ለዋሺንግተን ፓይልት በሰጠው መረጃ መሰረት በክራይስለር አርት ሙዝየም ስራውን ማቅረቡ ለሱ ለየት ያለ ስሜትን እንደሚሰጠው ተናግሯል። ይህም ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ ባመራበት ወቅት የጎበኘው የመጀመርያ ሙዝየም በመሆኑ እንደሆነ ዳዊት ጨምሮ ተናግሯል። የዳዊት ስራዎች እንደአንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአሜሪካ ባደገበት ወቅት ያለፋባቸውን የተለያዩ የህይወት መንገዶችን ጨምሮ የግልና የቤተሰቡን ታሪክ ያካተቱ መሆናቸውን መረጃው ያስረዳል። 

አስተያየት