ሐምሌ 17 ፣ 2012

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ሽልማት ተቃውሞ እና ድጋፍ እያስተናገደ ነው

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎችፊቸር

ወደ መንበረ ስልጣን ከመጣ ሁለት አመታትን ያሳለፈው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ አሊ መንግስት በስልጣን ቆይታው የተለየዩ አወንታዊና አሉታዊ ጊዜያትን…

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ሽልማት ተቃውሞ እና ድጋፍ እያስተናገደ ነው
ወደ መንበረ ስልጣን ከመጣ ሁለት አመታትን ያሳለፈው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ አሊ መንግስት በስልጣን ቆይታው የተለየዩ አወንታዊና አሉታዊ ጊዜያትን ማሳለፉ ይታወቃል። የስልጣን ዘመን የስኬት ጊዜያት መካከል ጠቅላዩ በ2011 የኖቤል ሽልማትን የተጎናጸፉበት አጋጣሚ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው። ዐቢይ ሽልማቱን ለማግኘታቸው በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት መካከል የነበረውን ዘመናትን ያስቆጠረ ቁርሾ መፍትሄ መስጠታቸው እንደዋነኛ ምክንያት መጠቀሱም ይታወሳል። ከቅርቡ ወዲህ ግን (በተለይም ከዝነኛው ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ሰሞኑን ከተፈጠረው አለመረጋጋት በኋላ) ለጠ/ሚንስቴሩ የተሰጠውን ሽልማት ትክክለኝነት የሚጠራጠሩና ብሎም የኖቤል ኮሚቴ ሽልማቱን መልሶ እንዲወስድ የሚደረጉ ጥሪዎች ተበራክተዋል። ከላይ የተጠቀሰውን ጥሪ ካቀረቡት ድርጅቶች መካከል በሜሪላንድ የሚገኘው የኦሮሞ አለም አቀፍ ፎረም ለኖቤል ኮሚቴ በሰኔ 5፣ 2012 ዓ.ም ያስገባው ደብዳቤ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው። ሃያ ስምንት በአውሮፓ፣ አሜሪካና በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ የኦሮሞ የፖለቲካና የሀይማኖት ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈው ድርጅቱ ሽልማቱ ለዐቢይ መሰጠት የለበትም በማለት የተለያዩ ምክንያቶችን በደብዳቤው አስቀምጧል። ድርጅቱ በደብዳቤው እንደገለጸው ከሆነ የዶ/ሩ መሸለም የኖቤል የሰላም ሽልማት ለአንድ ሰው እንዲሰጥ በመስራቹ አልፍሬድ ኖቤል የተቀመጠውን መስፈርት አያሟላም በማለት ያስቀመጠ ሲሆን የኖቤል ሽልማትን የሚሰጠው ኮሚቴ በዐቢይ የመጀመreያ ወራት ስራ ያልተገባ ድምዳሜ ላይ በመድረሱ የተሰማውንም ቅራኔ በግልጽ አስቀምጧል። የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ሁኔታ በዋነኝነት ሕወሃትን ለማዳከምና በአለም አቀፍ መድረክ ተቀባይነትን ለማግኘት የተደረገ የፖለቲካ ቀመር እንጂ ሰላምን ለማስፈን የተወሰደ ውሳኔ አለመሆኑን ጨምሮ የዶ/ሩን ያለፈ የስራ ታሪክና አሁንም በምዕራብና በደቡብ የኦሮሚያ ክፍሎች እየቀጠለ ነው ያሉትን የፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች እስራትና ጭቆና በደብዳቤው ላይ እንደምክያትነት ድርጅቱ አቅርቧል። የአምኒስቲ ኢንተርናሽናልን የመጋቢት ወር ዘገባ ዋቢ ያደረገው ደብዳቤው በኦሮሚያ በተለያዩ ክፍሎች መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ የዘር ማጥፋት ምልክት ያለው ሲል የገለጸ ሲሆን የኖቤል የሰላም ሽልማቱ ዐቢይን የማይገባ ተቀባይነት እንደሰጠው ድብዳቤው ያስረዳል። ባሳለፍነው ማክሰኞ ሐምሌ 12፣ 2012 ዓ.ም ደግሞ በአለም አቀፋዊ የኢትዮጵያውያን ማሕበረሰባዊ ድርጅቶች ኔትወርክ የተባለ ደርጅት ለኖቤል ኮሚቴ በላከው ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሰውን ጥያቄ እንደማይቀበለውና ለዐቢይ የተሰጠው ሽልማት ተገቢ እንደሆነ አስረድቷል። በስሩ ሃምሳ ሰባት ማኅበራዊ ድርጅቶችን ያቀፈው ኔትወርኩ በደብዳቤው ላይ የተለያዩ ምክንያቶችን በመዘርዘር ኮሚቴው የዶ/ሩን ሽልማት መልሶ እንዳይወስድም ደብዳቤው ይጠይቃል። የተለያዩ የፖለቲከኛ እስረኞች ካልተገባ እስር መለቀቅና ከስደት እንዲመለሱ መፍቀድ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በጠቅላዩ መሪነት ስለተፈጠረው የሰላም ግንኙነትና በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የአለምን የዛፍ መትከል ክብረወሰን 353 ሚሊዮን ዛፎችን በአንድ ዓመት አገሪቷ ለመትከሏ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ከተቀመጡት ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። ከላይ የሰፈረው ጥያቄም ሆነ ክርክር የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ገጽታ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑ የማይካድ ቢሆንም በሽልማቱ ላይ ይህ ነው የሚባል አንድምታ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም። ይህንን ለመረዳት ወደኖቤል ሽልማት መካነድር በማቅናት ድርጅቱ በተደጋጋሚ ለሚጠየቁ ጥያቄዎች ያስቀመጠውን መልስ መቃኘትና የድርጅቱን የቀድሞ ታሪክ ማጤን በቂ ነው። በመካነድሩ በግልጽ እንደተቀመጠው በድርጅቱ ታሪክም ሆነ የመተዳደርያ ድንብ ላይ ሽልማትን የመመለስ አሰራር እንደሌለው የሚያስረዳ ሲሆን ከዚህ ቀደምም ከተሰጠ በኋላ የተቀማ ሽልማት አለመኖሩንም ጨምሮ ይገልጻል። ይህ ማለት ግን ከላይ የተጠቀሱት ደብዳቤዎች ፋይዳቢስ ናቸው ማለት አይደለም። በአንፃሩ ድብዳቤዎቹ የአገሪቱን ዘር ተኮር የፖለቲካ ምህዳር ከማስረዳታቸው በተጨማሪ በጠቅላይ ሚንስቴሩ አለማቀፍዊ ተቀባይነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው። ከዚህ ቀደም የኖቤል ኮሚቴ ለበርማዋ አንግ ሳንሱ ኪ በ1983 ዓ.ም በሰጠው የኖቤል ሰላም ሽልማት ተመሳሳይ ተቃርኖንና ትችትን ማስተናገዱ የሚታወስ ሲሆን ሽልማቱ ከተመሰረተበት ከ1893 ጀምሮ ለ100 ያህል ግዜያት መሰጠቱን የኖቤል ሽልማት መካነድር ያስረዳል። ሽልማቱ ለ134 የተለያዩ ተሸላሚዎች የተሰጠ ሲሆን ከነዚህም መካከል መቶ ሰባት የሚሆኑት ግለሰቦች ሲሆኑ ቅሪዎቹ ደግሞ የተለያዩ ድርጅቶች መሆናቸው የሚታወቅ ነው። 

አስተያየት