ሐምሌ 21 ፣ 2012

ጠቅላይ ሚንስተር ዐቢይ አህመድ በአፍሪካ ምርጥ 100 ተቀባይነት ካላቸው ግለሰቦች አንዱ ሆኑ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አሊ ሬፒውቴሽን ፖል ግሎባል በተሰኘው የሰዎችን የተቀባይነት መጠን በመለካት በየአመቱ በተለያዩ ዘርፎች ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል ያላቸውን…

ጠቅላይ ሚንስተር ዐቢይ  አህመድ በአፍሪካ ምርጥ 100 ተቀባይነት ካላቸው ግለሰቦች አንዱ ሆኑ
ዶ/ር ዐቢይ  አህመድ አሊ ሬፒውቴሽን ፖል ግሎባል በተሰኘው የሰዎችን የተቀባይነት መጠን በመለካት በየአመቱ በተለያዩ ዘርፎች ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል ያላቸውን ሰዎች የስም ዝርዝር በማውጣት በሚታወቀው ድርጅት እውቅናን አገኙ። ከሰሞኑን በኖቤል የሰላም ሽልማታቸው ዙርያ ክርክርን በማስተናገድ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያው መሪ በዝርዝሩ ላይ ከመካተት ያላገታቸው ሲሆን፣ በዝርዝሩ ላይ ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ የሶል ሬብልስ ጫማና (soleRebels) የጋርደን ኦፍ ኮፊ (Garden of Coffee) ባለቤት ው/ሮ ቤተልሄም ጥላሁን አለሙና የሰስቴነብል ዴቨሎፕመንት ጎልስ ሴንተር ፎር አፍሪካ (The Sustainable Development Goals Center for Africa) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በላይ በጋሻው ከኢትዮጵያ በዝርዝሩ እውቅናን ያገኙ ግለሰቦች ሆነዋል።  ሬፕውቴሽን ግሎባል በዛሬው እለት የ2012 አመት በአፍሪካ አህጉር ተቀባይነት አላቸው ያላቸውን 100 ሰዎች የስም ዝርዝር ይዞ የወጣ ሲሆን በዝርዝሩ በአመራር፣ በትምህርት፣ በንግድና በመዝናኛ ዘርፎች ለተሰማሩ አርባ ሰባት ሴቶችና ሃምሳ ሶስት ወንዶች እውቅናን ሰጥቷል። የተዘረዘሩት ግለሰቦች የተመረጡበት ማምጣት የቻሉትን ለውጥ፣ ባሳዩት ርትዑነትና ክሱትነት (Integrity, Visibility and Impact) መሆኑንም መረጃው ጨምሮ ይስረዳል። ዝርዝሩም ፖለቲካዊም ሆነ ከላይ ከተጠቀሱት መስፈርቶች ውጪ የተጠቀማቸው መመዘኛዎች እንደሌለ አክሎ በመግለፅ በተሰማሩበት ዘርፍ በአፍሪካም ሆነ በአለም ዙርያ በስራቸው መልካም ተፅዕኖና እውቅናን መስጠት እንደሚገባ የሽልማቱ አዘጋጆች ዝርዝሩ ይፋ በሆነበት ዝግጅት ላይ ተናግረዋል። በተጨማሪም በመካነድሩ በተቀመጠው መረጃ መሰረት ዝርዝሩ በደረጃ ሳይሆን በፊደል ተራ ቅደም ተከተል መሆኑን ተናግረዋል። በውስጣዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና በውጫዊ የፖለቲካ ድርድሮች ተጠምደው የሚገኙት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በወቅቱ በተለያዩ የአለም መድረኮች ወቀሳን እያስተናገዱ እንደሚገኝ ይታወቃል። አዲስ ዘይቤ ባለፈው ሳምንት የዘገበው የኦሮሞ አለማቀፍ ፎረም ለኖቤል ኮሚቴ በሰኔ 5፣ 2012 ቀን የላከው የሰላም ሽልማቱ ለጠቅላዩ አይገባም የሚል ጭብጥን የያዘው ደብዳቤ እንደአንድ ማሳያ መውሰድ ይቻላል። ታዳያ ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰው እውቅና በኖቤል ሽልማት ደረጃ ያለ ተቀባይነት አለው ለማለት ባያስችልም፣ የኢትዮጵያው መሪ በዝርዝሩ መካተት በጠቅላዩ ተቺዎችና ተቃዋሚ ወገኖች ዘንድ የሚፈጥረው ቅራኔ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል። በዝርዝሩ የተካተቱት ወ/ሮ ቤቴልሄም በንግድና ስራ ፈጠራ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን አለምአቀፍ ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለውን ሶል ሬብልስ ጫማን ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማሩ እንስት ኢትዮጵያዊ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። የ40 አመቷ ሴት የንግድ ባለሙያ በዘርፉ ካሳኩት ስኬት በተጨማሪ ለሴት ሰራተኞች በፈጠሩት የስራ እድል ትልቅ እውቅናን ማግኘታቸው ምስጢር አይደለም። በተመሳሳይ አህጉራዊ ዝርዝሮች ላይም ሲካተቱ የመጀመርያቸው አይደለም። ሌላኛው በዝርዝሩ የተካተቱት ኢትዮጵያዊ ዶ/ር በላይ በጋሻው ሲሆኑ ግለሰቡ በሰስቴነብል ዴቨሎፕመንት ጎልስ ሴንተር ፎር አፍሪካ በዋና ዳይሬክተርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ዶ/ሩ ከኢትዮጵያ የግብርና ሚንስቴር አንስቶ በተለያዩ አህጉራዊና አለምአቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በግብርናና የገጠር ልማት ዘርፎች  ከ20 አመት በላይ የስራ ልምድ እንዳላቸው የሚታወስ ነው። ዝርዝሩ ካካተታቸው ሊሎች አፍሪካውያን መካከል የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ፣ የሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ከንቲባ ዩቫን አኪ-ሳውየርና የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንቱ ፌሊክስ ሼስኬዲ ከአመራር ዘርፍ እንዲሁም በአድቮኬሲ ዘርፍ የቱኒዚያ የሰብአዊ መብት ሊግ ፕሬዝዳንት ቱኒዝያዊው አብድሰታር ቤን ሁሴንና ደቡብ አፍሪካዊው የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ሴክረተሪ ጀነራል ኩሚ ይገኙበታል።  በቢዝነስ ዘርፍ ደግሞ የዲሎይት አፍሪካ ዋና ስራ አስካያጅ የሆኑት ደቡብ አፍርካዊው ልዋዚ ባምና በነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማራው ናይጄርያዊው ፌሚ ኦቴዶላ ይገኙበታል። ሬፕውቴሽን ግሎባል ከላይ ከተጠቀሰው ዝርዝር በተጨማሪ በአለም ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦችን ዝርዝርና፣ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ተቀባይነት ያላቸው ስራ አስኪያጆች ዝርዝር በማውጣት የሚታወቅ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ የአለም ምርጥ 100 የእርዳታ ድርጅቶች በሚል ርዕስ የተሰጠው አዲስ ዝርዝር ለማውጣት በዝግጅት ላይ መሆኑን በመረጃው አስቀምጧል።

አስተያየት