ሐምሌ 21 ፣ 2012

ራንደም ዴይሊ አርት፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ወቅት የስዕል አውደ ርእይ ማሳያ ቦታዎችን መዘጋትን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት የሚሸፍን አማራጭ መድረክ

የፈጠራ ዐውድኑሮዜናዎችፊቸር

አሁን ከምንኖርበት ዘመን ዋነኛ መገለጫዎች መካከል ሁሉም መረጃና የምንፈልገው ነገር ሁሉ በእጃችን መሆኑ በዋነኝነት ይጠቀሳል። የምንፈልገውን ነገር ሁሉ…

ራንደም ዴይሊ አርት፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ወቅት የስዕል አውደ ርእይ ማሳያ ቦታዎችን መዘጋትን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት የሚሸፍን አማራጭ መድረክ
አሁን ከምንኖርበት ዘመን ዋነኛ መገለጫዎች መካከል ሁሉም መረጃና የምንፈልገው ነገር ሁሉ በእጃችን መሆኑ በዋነኝነት ይጠቀሳል።  የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ከአንድ ቦታ ለማግኘት ያለንበት የተቀራረበ ዘመን ሁሉን አቅልሎልናል፡፡ በተለይም የተለያዩ መተግበሪያዎችና በበይነመረብ አማካኝነት የተለያዩ የስራ ፈጠራዎችን መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት አመቺ አማራጭ ሆነው ቀርበዋል። አለማችን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር መጋፈጧን ተከትሎ ሰዎች በቤት እንዲቆዩ በሚበረታታበት ወቅት እንኳን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመተግበሪያዎችና በኢንተርኔት በመታገዝ አገልግሎታቸውን ለተጠቃሚዎቻቸው እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ የሙዚቃ ድግሶችንም ከቤት መከታተል ተችሎዋል፡፡ የመዝናኛ ስፍራዎች ደንበኞች መቀበል ቢያቆሙም ተጠቃሚዎች በፍላጎታቸው የሚያሻቸውን የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ለተጠቃሚ ማድረስ የተለመደ ሆንዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያነት በአገራችን ኢትዮጵያ እንኳን የፈንድቃ ባህላዊ ማእከልን ተሞኩሮ መጥቀስ ይቻላል።  ከዚህም ጋር ተያይዞ ራንደም ዴይሊ አርት (Random Daily Art) በተባለው መካነ ድር አማካኝነት ሰዎች የስእል ጥማታቸውንም ሆነ ተሰጦኦዋቸውን ሚገልጹበት መድረክ መዘጋጀቱ ከሰሞኑን የተለያዩ የማህበራዊ ድህረ-ገጾች በመዘገብ ላይ ይገኛሉ። ይህ መካነ ድር በአፍሪካውያን ሰአሊያን የተሰሩ የስእል ጥበባት የሚታይበት መድረክ ሲሆን በኢትዮጵያም ያሉ ሰኣሊያን ስራዎቻቸውን ለአለም ህዝብ የሚያሳዩበትን መድረክ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ የማሳያ መድረክ ለአፍሪካውያን ሰአሊያን ልዩ ቦታ የሰጠ በመሆኑ የቀረው አለም ከአህጉሪቱ የሚወጡ ስእሎችን በመጎብኘት ጥሩ ጊዜን እንዲያሳልፉ ታስቦ የተቀመረ ነው፡፡መካነ ድሩ ከተፈጠረ ሁለት ወራትን ቢያስቆጥርም ከተለያዩ የአለም ክፍል አድናቆትን ከማካበቱ በላይ የተለያዩ ሰአልያንም የስእል ተሳጦዋቸውን በመላክ መድረኩን እያደመቁት ይገኛሉ፡፡ ታዋቂነትን ገና ላላተረፉ ሰአሊያን ከአድናቂዎቻቸው ጋር የሚገናኙብት መድረክም ሆኖላቸዋል፡፡ በተጨማሪም በአህጉሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ሰአልያን የሌሎች አርቲስቶችን ስእሎች የሚያደንቁበት ቦታ ሆኖላቸዋል፡፡ በዚህ ወቅት በአለም ላይ በተከሰተው የኮሮና በሽታ ወረርሽኝ አብዛኛው ሰው ቤቱ በተቀመጠበት ጊዜ ሊደርስበት ከሚችል የመንፈስ ውጥረት ሊያረጋጋና ሊያድስ የሚችል መድረክ እንደሚሆንም ይታሰባል፡፡አዲስ ዘይቤ የመካነ ድሩን ባለቤት ሰቴቨን ኤርሊ መድረኩን ለመፍጠር ምን እንዳነሳሳው በጠየቀበት ወቅትም “ኮሮና በህይወታችን ውስጥ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ሰው በቤት ውስጥ እንዲቆይ ሲገደድ እና የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች፤ የስዕል አውደ ርእይ ማሳያ ቦታዎችና የጥበብ ቤቶች ተዘግተው ሳይ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡  ለዚህም ምክኒያቱ ሁል ጊዜ ጠዋቴን ስጀምር የስእል ስራዎችን ማየት ስለምፈልግ ነው። ከዛም ለምን የስዕል ጥበብ ስራዎች ወደኔ አይመጡም የሚል ሃሳብ መጣልኝ። ሌሎች ሰዎችም በቫይረሱ የተነሳ በአስጨናቂው ዜና ከባድ ጊዜ እያሳለፉ እንደሚሆን መገመት አይከብድምና ምናልባት የሌሎችን ቀን ብሩህ ማድረግ ከቻልኩ በሚል ነው ራንደም ዴይሊ አርት መካነ ድርን የፈጠርኩት” ሲል መልሷል። መካነ ድሩ በተጠቃሚዎች እና በተመዝጋቢዎች የኢሜል መልእክት መቀበያ በየእለቱ የተለቀቁትን እና በድሩ ላይ የተለጠፉትን የስእል ጥበባት የሚያሳይ ሲሆን ለሰአሊያን ትልቅ ስፍራ መሰጠቱን ለመረዳት ችለናል፡፡ ማንኛውም የስእል ተሰጥኦ ያለው ወይም የስእል ስራዎችን ማየት የሚያስደስተው ሰው መካነ ድሩ ውስጥ በመመዝገብና የተለያዩ ስእል ስራዎችን በመለጠፍ በየእለቱ ጠዋት ላይ በግል የኢሜል አድራሻ አማካኝነት የስእል ስራዎችን መጎብኘት ያስችላል፡፡የመካነ ድሩ ባለቤት ሰቴቨን ኤርሊ በዜግነት ቱርካዊ ሲሆን የተለያዩ የአለም ክፍሎችን በመጓዝ የተለያዩ ሀገራትን ቋንቋ ባህል የምግብ ስርኣታቸውንና የስነጥበብ ስራዎችን በመጎብኘትና ያለውን የቴክኖሎጂ የስራ ፈጠራ ክህሎት ለሰዎች ሲያቀርብ ቆይቶዋል፡፡ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜም እጅግ በጣም የሚያሰደስቱ የስእል ጥበባትን የተመለከተ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ሰአሊያን ተሰጥኦዋቸውን ለአለም ህዝብ ቢያሳዩ መልካም እንደሆነ ይናገራል። ባስተላለፈው መልእክትም “ሰዎች ሁሉንም ነገር ለጥቂት ጊዜ ቆም አድርገው የሚያዝናና እና አእምሮን ፈታ የሚያደርግ ነገር እንዲፈልጉ እመክራለው::” ብሎዋል፡፡

አስተያየት