ሐምሌ 11 ፣ 2011

“የማይሰበረው” ኤርሚያስን እንዳነበብኩት!!

መጽሓፍትኑሮታሪክ

.

“የማይሰበረው” ኤርሚያስን እንዳነበብኩት!!

በጊዜያችን የ“ሰይጣን አምላኪዎች” ወደሚባሉት የምዕራብ ሀገራት ብዙ ህዝብ በስደት ይነጉዳል:: በርካታው የዓለማችን ክፍል ነዋሪ እነኚህን አገራት የሙጥኝ ብሏል:: ይህ ደግሞ ዛሬ ብቻም ሳይሆን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያሳለፈ ገሐድ እውነታ ሆኗል:: በተለይ በኢትዮጵያ ከአብዮቱ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ለመጀመርያ ጊዜ በስደተኝነት መዝገብ ስማቸውን ያሰፈሩበት የታሪክ ዘመን ነው፡፡

ፅሑፌን የምጀምረው "የእግዚአብሔር አገር" የምትባለው ኢትዮጵያ ልጇቿን ገፍታ የባቢሎን ምድር ወደምትባል አገር ጥገኝነትን ጠይቆ፣ የተደላደለ እና ደፋ ቀና በሚል እሳቤ ግለሰቦች የግል አቅማቸውን ለዓለም የሚያስተዋውቁበት የመኖር እድል ፈንታን ሊሻሙ ከቅድስት አገር ወደ ባቢሎናዊት ምድር መሰደዳቸው ለምንድን ነው በሚል ተላላ በሚመስል ሃሳብ ነው:: እጅግ ግራ ያጋባል::

ይህንን ያልኩት የኤርሚያስ ጠቅል አመልጋን የህይወት ታሪክ ገፅ 63 ላይ ስደርስ ነው:: "ወይ ኢትዮጵያ ቅድስት አይደለችም" አልያም "አማሪካ የባቢሎን ምድር" መባሏ የቅናት ይሆን?  ወይስ ሌላ ምን!?

ከሞቀ ከጣፈጠ የቤተሰብ ታሪክ ህይወት ወጥቶ በልጅነቱ የንጉስነትን ማእረግ ሽረው ትምህርትን የመረጡት አያቱ፤ ከጉራጌ ቤተሰብ የተቃረነ ልማድ ተላቀው "ንግስና ይቅርበት ትምህርት ይማር" ብለው ያስተማሩት አባት፤ አዲስ አበባመጥተው በግል ትምህርት ብቃታቸው ስራ ይዘው እስከ ውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ድረስ ተቀጥረው፣ ዲፕሎማት ሆነው...በግብፅ፣ በኬንያና በአዲስ አበባ ዊንጌትን ጨምሮ የውጭ ማኀበረሰብ ትምህርት ቤት ትምህርቱን የተከታተለው ኤርሚያስ፤ በአባቱ እና እናቱ ብርቱ የህይወት ትግል እውቀትን መሰረት ያደረገ የህይወት ዘይቤን መውረሱን እንመለከታለን:: የውርሶች ሁሉ የማይነቅዘውን ውርስ ከጠቅል አመልጋ እና አባታቸው መተላለፉንም እንመሰክራለን! ትጋት - ልፋት - እውቀት -ችግር --መፍትኄ - ጥናት - ምርምር- ተስፋና ትዝታ- ወድቆ መነሳት የሕይወት ጉዞ መርህ...!!

የግለ ታሪኩ አሰናኝ አንተነህ ይግዛው በአጫጭር መጣጥፎቹ የምናውቀው ሲሆን ከማህበራዊ <<ሚድያ>> ራቅ ብሎ ይዞልን የመጣው የአነጋጋሪውን ግለሰብ የህይወት ታሪክ ነው::

መፅሐፉ ጥብቅ ክትትልን እና በአፅንኦት እንደተሰናዳ ከፊደል ግድፈት አናሳነት እና ዝርዝር ሀተታዎች ላይ መመልከት ይቻላል::

ፀሐፊው በተርታ ሊመሰገን የሚገባው ነው:: መሰል ስራዎችም እንዲበዙልን ከማሳስሰብ ወዲህ - በተቻለ መጠን ያለ ተፅእኖና ያለ ዳረጎት - መዘጋጀት የሚኖርባቸው፣ የታሪክ ምስክርነትን ሆነው ህያው የሚሆኑ ውድ ቅርሶች መሆናቸውንም በቀይ መስመር በማስመር ጭምር ነው::

የግለሰቦችን ታሪክ ማንበብ እጅግ እወዳለሁ:: የማንኛውም ውጣ ውረድ ያሳለፈን ግለሰብ ልጅነት እድገት እውቀት የህይወት ፍልስፍና አረዳድ የስኬት ጉዞ የውድቀት ምክንያት እና ምላሽ ማንበብ ሌላ የህይወት እድልን እንደመጎናፀፍ እመለከተዋለሁ::

መፅሐፉ እጅግ ቀለል ባለ የፅሁፍ አጣጣል በማይጎረብጥ አማርኛ በሚጣፍጥ አተራረክ ዘይቤ ተከሽኖ ስለቀረበ ከአንድ አጭር አለም አቀፍ በረራ ውስጥ ተሳፍሬ እስክወርድ ድረስ ያለማቋረጥ ያነበብኩት ነው:: ይመስጣል:: አንብቡኝ እንጂ ዝጉኝ ዝጉኝ አይልም:: ይህን በረከት በዚህ ዘመን ማግኜት በራሱ አንድ መታደል ነው:: 390 ጣፋጭ ገፆች:: ከአንዱ ገፅ ወደ አንዱ ገፅ ሂደት የሚደረገውን የገፅ ገለጣ ሳናስታውሰው በምናብ እዛው ባለታሪኩ ልብ ውስጥ ተቀምጠን እንደምንጓዝ የሚያስችለንን መሳጭ የስበት ኃይል ይቸረናል- ወይ የፀሐፊው ስል ብእር ነው አልያም የባለታሪኩ የታሪክ ገጠመኝ!!

መጽኸፉበጣት የሚለቀሙ ትየባ ግድፈት በቀር ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኑሮ መርህ ሊሆን የሚገባን ቁምነገር የምናገኝበት ነው ብዬ አምናለሁ:: ቢቻል ቢቻል የምጣኔኃብት ባለሙያዎች ጭምር ቢገመገም መልካም ነው ባይ ነኝ:: የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ አስተያየት የሚሆነው በስነፅሁፉም በምጣኔ ሃብቱም ኂስ ለመስጠት ብቃቱ እንደሌለው ማሳወቁ ትችት ነቀፋን ለባለሙያው እንዲሆን በማስገንዘብ ጭምር ነው::

መፅሐፉን ከሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል:: ከአክሰስ ሪል ስቴት በፊት እና በኋላ:: ከአክሰስ ሪል ስቴት ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ የምናነበው ታሪክ ብዙዎች በአፅንኦት የሚጠብቁት እንደሆነ አልጠራጠርም:: ይህንን በመጽሐፉ የመጀመሪያዎቹክፍሎች እናገኘዋለን፡፡ ምዕራፍሁለት ላይ ደግሞ አክሰስ ካፒታል ሰርቪስ የተባለ ኩባንያ ሲቋቋም ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ውጣ ውረድ የምናይበት ነው::  አድካሚ ቢሆንምየጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ብቻ የሌሊቱ መንጋት ግድ ሳይሰጥ መፅሐፉን ጨርሰን ማደር እንዳለብን አሁንም ወይ ፀሐፊው አንተነህ አልያም ተተራኪው ኤርሚያስ ፈርደውብናል፡፡

በንግድ ዓለም ሶስት አይነት ሰዎች አሉ ተብሎ ይነገራል:: የሰጎን ባህርይ፣የግንደ ቆርቁር ወፍ እና የተለዋዋጭ ባህርይን የሚያሳዩ ግለሰቦች:: የሰጎን ባህርይን የያዙ ግለሰቦች በስራ ዘርፋቸው የሚያጋጥማቸውን የችግር አይነት ልክ ሰጎን እንደምትደርገው አንገታቸውን ወደ መሬት ቀብረው የመጣውን የችግር አውሎ ነፋስ ያልፉታል:: የግንድ ቆርቁር አይነት ባህርይ ያላቸው ደግሞ ልክ ግንደቆርቁር ቁኑን ሙሉ የግንዱን ወገን ስትቆሩቁር እንደምትውለው ሁሉ ችግሮቻቸውን ብቻ ሲፈተፍቱት ችንካር ተክለው ሲደበድቡት በሚውሉ አይነት ሰዎች ተመስለዋል:: ሁለቱም አይነት ሰዎች በስራቸው አጥጋቢ ውጤትን ማምጣት እንደማይችሉ ጥናቱ ያረጋግጣል::

ሶስተኛው ባህርይ ችግሮችን እንዳመጣጣቸው መፍትኄን አዘጋጅቶ በሌላ አማራጭ መንገድ ፈትቶ ወደሌላኛው የስራ እርከን ደረጃ ከፍ እያለ የመጓዝ ጸባይን የሚያሳይ ነው:: ለችግሮች ሁሉ መፍትኄ አለው!! መፍትኄ የሌለው ችግር የለም!!

ምናልባት ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ለዚህኛው ባህርይ የታጨ ግለሰብ አርአያ ሊሆን የሚችል ነው:: ይህም እ.ኤ.አከ1995 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የተሸጋገረባቸውን አስራ ዘጠኝ ያህል ድርጅቶችን መመልከት እና ታሪካቸውን ማጥናት ከበቂ በላይ ነው::

የእነዚህ አስራ ዘጠኝድርጅቶች ታሪክ ውስጣዊ ውስብስብ ሸክሞቻቸው ውድቀትና ስኬት የመላ አገሪቷን የስራና የልማት እንቅስቃሴ በጉልህ የሚያሳዩ ናቸው::

እንደ አገር ዘቅጠን የኃሊት ሽምጥ የምንጋልብበትን ቁልፍ ችግር ከዚህ መፅሐፍ ውጭ የሚያሳየን ይኖራል ተብሎ አይታሰብም:: አሜሪካን አገር ከሞቀ  ትዳሩ እና ቤት ቤተሰቡ፣ ከደራው የስራ ህይወቱ የስኬት እርከኑ ማማ ላይ አስኮብልሎ ወደዚህች “ቅድስት ምድር” ያስመጣው የሒሳብ ስሌት ምንድን ነው ብለን የራሳችንን የኅሊና ጓዳ ሳንጠይቅ አናልፍም:: ማን ነው የአማሪካን "ግሪን ካርድ" ለሰጭው ባለቤት የሚመልስ? መልሱን የአሜሪካን ኢምባሲ በኢትዮጵያ የገጠመውን ክስተት በመፅሐፉ በማንበብ እናገኘዋለን:: (የአሜሪካን ግሪን ካርድ ለሚመልሱ አመልካቾች የሚሞላው ቅፅ በአሜሪካን ኢምባሲ ለጊዜው መታጣቱ ምላሽ ነው::)

ሰውዬው የውጭ ድርጅቶችን በይሁንታ እያንጠለጠለ የሚያጎርፍበት ምክንያት የሁልጊዜ ጥያቄዬ ነው:: ለፕሮጀክቶቹ የሚያቀርባቸውን የትንተናዎች ጥራዞችን በማየት ብቻ በሚልዮን የሚቆጠሩ ረብጣ ዶላሮችን ለማፍሰስ ቆርጠው የሚመጡ ድርጅቶችን እሺታ ከማግኘት በላይ ሌላ ከባድ ነገር ምን ሊኖር ይችላል!?

እውነትም ይህች አገር እርግማን አለባት ያስብላል::

እውነትም እያስጀመረየሚያከሽፍባትን"የእድገት ሾተላይ" ምስጢር ቅኔውን ለመግለጥ ላይ ብንታትር  መልካም ነው::ይህንን ቅኔ ምስጢር ለመግለጥ ከኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ የሚሻል ሰው አለ ብሎ ማሰብ ይከብዳል::

የሰቆጣው ብረት:: በአማራ ክልል ባላስልጣናት የቀረበውን የገበሬዎች ጥያቄ እና ተጀምሮ በእንጥልጥል የቀረው ጉዳይ በእርግጥም ኢትዮጵያን ለአለም በገሃድ የሚያስቃኝ የክሽፈታችን ጥግ ነው:: ለአማራ ገበሬዎች መልሶ ማቋቋም ስራ ሂደት ገበሬዎች ጋር ባደረገው ንግግር ኤርሚያስ የገለፀውን ምልከታ እዚሁ ማስቀመጥ ሳይጠበቅብን አይቀርም!!

"አልተማሩም ከሚባሉት የኮምቦልቻ ገበሬዎች የሚቀርቡልኝ ጥያቄዎች: ዘመን ባንክንና አክሰስ ሪልስቴትን በማቋቁምበት ወቅት ከባለሃብቶችና ከኢንቬስተሮች ይቀርቡልኝ ከነበሩት ጥያቄዎች በእጅጉ የላቁና ትርጉም ያላቸው ነበሩ::" <<የማይሰበረው >>-ገፅ 204

በመፅሐፉ መግቢያ ታሪክ ውልደት እና እድገት ጀምሮ የ20ኛዋን ክፍለዘመን ኢትዮጵያ በግልፅ ያስቃኘናል:: የንጉሱ ስርዓት ግለሰቦችን ያለ "ብሔራቸው" በሙያና ብቃታቸው ብቻ ዋቢ ሆኖ ከተርጓሚነት እስከ ዲፕሎማት ድረስ መድረስ እንደሚቻል የኤርሚያስ አባት አሳይተውናል::

እውቀት ምን ያክል ክብር እንዳላትና የግል ትጋት ምን ያክል ከወርቅ የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር መሆኑን ያሳያል!! በእርግጥ ምን ያክል የዝቅጠት ጉዟችንን እርከን የምናየው - በዘመነ ፌዴራሊዊት ኢትዮጵያ እውቀት እና ቀጣይነት ያለው የስራ አፈፃፀም ኪሳራችን ጣራ የነካበት ዘመን መሆኑን በአደባባይ እንመለከታለን::

የግል እውቀት ብርቱ ሰዎች የማይከበሩባት ቅድስት አገር እያለችን ስለምን አልተጠቀምንባቸውም? ስለምን እርኩሳን አደረግናቸው? ስለምን ቤተክስያን እንደገባች ውሻ ማዋከብ ምላሻችን ሆነ? ስለምን አጎሳቆልናቸው? ስለምን..!? እያልን የጥያቄ ሰበዝ ብንጀምር ማለቂያ ወደሌለው ራስ ምታት መዛለቃችን ነውና ከዚህ ከማይሰበረው ግለሰብ ምን ተበደልን ብቻ ሳይሆን ምን እናግኝ ብንል የምናጣው አይኖርም:: ሰሎሞን ደሬሳ ለዚህ ሃሳብ ሽብልቅ የሚሆኑ ግለሰብ ሳይሆኑ አይቀርም::

ኢትዮጵያ በግለሰቦች እዳ ሸክም በእነሱ ኪሳራ እንባ ታጥባ እድገቴን እቀጣለኹ ካለች ቅድስትነቷ ከሲኦል የተላከ ምስክርነት እንዳይሆን አጥብቀን እንማፀናለን:: ኢትዮጵያ የኤርሚያስ እና የመሰሎቹ ባለ ዕዳ ናት!!

የማይሰበረውን ለመስበር ሁነኛ ሆነናል:: ምን ነክቶን ይሆን!? የሆነው ይሁንና የማይሰበር ስብእናን ይዘን ፀንቶ መቆም መታደል ነውና ከኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ህይወት ታሪክ ውስጥ በገንዘብ የማይሸመት ልምድን አካብተናል:: 390 ገፅ መፅሐፉን በትጋት ማንበብን ግን ይጠይቃል! ያለ ትጋት የሚገኝ ሁሉ እርግማን ነው:: የኢትዮጵያ ችግር ይህ ሳይሆን ይቀራል!?

አስተያየት