ጥቅምት 19 ፣ 2012

የጥላቻ ንግግር መዋጋት፡ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን

ሕግ

መንደርደሪያ

መንደርደሪያ

የጥላቻ ንግግር የዛሬዋ ኢትዮጲያ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖአል፡፡ በሬዲዮ፣ ቴሌቭዥን፣ ጋዜጣም ሆነ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶች የተለየ የቡድን ማንነትን እያጠለሹ፣ ለግጭትም ምክንያት እየሆኑ ነው የሚል ግንዛቤ በብዛት ይታያል፡፡ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደርም የጥላቻ ንግግር ለሀገር ደኅንነት አደጋ ነው የሚል አቋሙን በተለያዩ አጋጣሚዎች አንጸባርቋል፤ በሕግ እስከመገደብ እና እስከመቅጣጥ የሚደርስ እርምጃ ለመወሰድም ተነስቷል፡፡ እንደመንግስት አዝማሚያ የጥላቻ ንግግር ዋነኛ ማሰራጫዎች የሚላቸው የኢንተርኔት/የማኅበራዊ ሚዲያውን መድረኮች ነው፡፡ የኢንተርኔን ተጠቃሚ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም በፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡ ባለው አነስተኛ ተጠቃሚም ቢሆን በሀገሪቷ ውስጥ የሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች እና የተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲጠሩ እና ሲደራጁ፣ የማህበረሰብ አመለካከትም ሲቀረጽ ታዝበናል፡፡ መንግስት ለዓመታት እራሱ ብቻ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት የግሉ ዘርፍ እንዲገባበት መወሰኑ ተጠቃሚዎቹ በፍጥነት ሊጨምሩ የሚችልበት አዝማሚያ እንደሚኖር ማየት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መልእክቶች የሚኖራቸው ሚና እየጨመረ ይሄዳል፡፡ 

መንግስት የኮምፒዩተር ወንጀልና የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕጎችን በማውጣጥ የማህበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ ሚዲያዎችን በብሮድካስት ባለስልጣናት ለመቆጣጠርም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከመንግስት ባሻገር የተለያዩ አካላትም የጥላቻ ንግግሮችን ለመዋጋት የተለያዩ አካሄዶችን ለመጠቀም ሲጥሩ ይታያል፡፡ የሚዲያ ስነምግባርን ለመከታተል የታለሙ የሚዲያ ማህበራትን መቋቋምም አለ፡፡ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተቋማት መመስረት፣ የኩነት ማጣራት ስራዎች ማከናወን፣ እና ማህበረሰቡ መረጃዎችን ስለሚያጣራበት አካሄድ ማሳወቅ መንግስታዊ ያልሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት እየሰሩባቸው ከሚገኙ አካሄዶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ይህ ጽሑፍ እነዚህ አካሄዶች እውነት ለጥላቻ ንግግር መድሃኒት ናቸው ወይስ ማስታገሻ የሚለውን ለመርመር ይሞክራል፡፡

የጥላቻ ንግግር ብያኔ

የጥላቻ ንግግርን ብያኔ ከሕግ ማእቀፎች በተሻለ የሚገልጽ አይኖርም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ በአይሁዶች ላይ የደረሰው የዘር ማጥፋት እልቂት ዓለም ለጥላቻ ንግግሮች የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ያስተጋባ ደውል ነበር፡፡ በኮሶቮ እና ሩዋንዳ የደረሰው የዘር እልቂትም የጥላቻ ወንጀሎችን የሚያነሳሱ መልእክቶች በበለጠ የሕግ ትኩረት እንዲያገኝ አጋጣሚውን የፈጠሩ ክስተቶች ነበሩ፡፡ ሀገሮች የጥላቻ ንግግሮችን እንዲቆጣጠሩና እንዲቀጡ በአለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ቃልኪዳን እና ማንነትን መሰረት ያደረጉ አድሎዎችን ለማጥፋት በተቋቋመ ስምምነት ላይ በግልጽ ተደንግገዋል፡፡ ሀገራት የዘር ማጥፋት የሚያነሳሱ ወንጀሎችን የሚቀጡ የወንጀል ድንጋጌዎችን እንዲያካትቱ የሚያስገድድ ስምምነትም ተደርጓል፡፡

የጥላቻ ንግግር እንደ አንድ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ገደብ ነው፡፡ የጥላች ንግግር ሃሳብን በመግለጽ እና በእኩልነት የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶች መካከል ሲዋትት እናገኘዋለን፡፡ አንድ ሰው የተለየ ቡድን አባል በመሆኑ ምክንያት ከተለያዩ ሀገራዊ ጥቅሞች፣ በሕግና ተቋሞች ፊት አድሎ ሊደረግበት እንደማይገባ የሚያትተውን የእኩልነት መብት ለመገደብ፣ ጫን ሲልም ጥቃት እንዲደርስ የሚተላለፍ መልእክት ነው - የጥላቻ ንግግር፡፡ በተለዩ የሚዲያ አማራጮች ወይም በአደባባይ በሚደረግ ጥሪ አንድ ማህበረሰብ በሌላው ላይ የጥላቻ አመለካካት እንዲይዝ ይህንንም ተከትሎ አድሎ ወይም ጥቃት እንዲያደርስ የሚተላለፍ መልእክት የጥላቻ ንግግር ብያኔ ውስጥ ይወድቃል፡፡

የጥላች ንግግር ... በዛሬይቱ ኢትዮጲያ

በዛሬይቱ ኢትዮጲያ የጥላቻ ንግግር የብሔር ማንነትን በዋነኛነት መሠረት አድርጓል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሀይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ንግግሮች ደግሞ የብሔር ማንነት ተቀጽላ መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል፡፡ በ60ዎቹ የተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደተጸነሰ የሚነገረው "የብሔር ጥያቄ" ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ ዛሬ ላይ አጠቃላይ የሀገሪቷ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማዕከል ሆኗል፡፡ የአንድ ብሔር እሴቶች የሀገሪቷ ዋና መገለጫ እንደሆኑ እና ሌሎች እንደተዋጡ፤ ይሄም ሊታከም የሚገባው የተዛባ የሕዝብ ግንኙነት መፍጠሩ የ“ያ ትውልድ” የፖለቲካ አፍ መፍቻ ነበር፡፡ የወታደራዊ መንግሰቱን መውደቅ ተከትሎ የመጡት የዚሁ ትውልድ አካል የሆኑና በብሔር የተደራጁ የሽምቅ ተዋጊዎችም ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ብሔርን ማእከል ያደረገ አስተዳደር አቁመዋል፡፡ ይሄ የብሄር ስርዓትም በይስሙላ የክልል ስልጣን  ከመሃል በሚዘወር ወጥ የፖለቲካ አመራር ለአመታት ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ ስርዓቱ ወጥ ይሁን እንጂ ክልሎች የአንድ ብሔር ግዛት የመሆናቸውና የራስ ገዝ እምነታቸው እየጠነከረ እንዲመጣ ሲደርግ፣ አዲሱ ትውልድን በጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት እንዲያጠምቅ አስችሎታል፡፡ 

ከስርአቱ ዋነኛ ቀማሪዎች ውስጥ አንዱ የሆኑት የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞት ተከትሎ የፓርቲያቸውና የሀገሪቷ ወጥ አስተዳደር እየተዳከመ እንዲመጣ፣ መንግስት በሚዲያ፣ ሲቪክ ማህበራት እና የፓርቲ ፖለቲካ የነበረው ቁጥጥር አንዲላላ ሆኗል፡፡ ከአመታት የአደባባይ ላይ ተቃውሞና በመሳሪያ የታጀበ ተቃውሞ ተከትሎ ወደ መንበሩ ብቅ ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ደግሞ በቡድን የታጠረውን ፖለቲካ አንጠልጥለው የሊብራል ዲሞክራሲን አካሄድ ለሀገሪቷ እንደ አማራጭ ወሰዱ፡፡ ይሄንንም ተከትሎ የበሰለው የክልሎች የራስ ገዝ ጥያቄ ወደ ፊት እንዲመጣ፣ የብሔሮች ውድድርም ወደ ውይይት መድረኩ እና አደባባይ ጎልቶ እንዲመጣ ሆኗል፡፡ ዛሬ ላይ ክልሎች እርስ በራሳቸው ሲናቆሩ እና በማዕከል ላይ ያላቸው ብሔር ተኮር ዉክልና በሌላው እንደተቀሙ ሲያስተጋቡ ማዳመጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ የመንግስት አካላትም ሆኑ ግለሶቦች በብሔር ተደራጅተው የጨቋኝ-ተጨቋኝ፣ የባለቤት-መጤ ትርክቶችን በየተገኘው መድረክ ሲስተጋቡ ይሰማል፡፡ ልዩነቶች ሰፍተው በየጎራው መነቋቆር የእለት ተእለት ህይወት ክፍል መሆኔ አሌ አይባልም፡፡ ብሔርን መሠረት ያደረጉ የጥላች ንግግሮች በየመድረኩ ሲስተጋቡ መስማትም ተለምዷል፡፡ 

የብሔር ጠበቃ ሚዲያዎቻችን...

የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ከመጣ በኃላ የሚዲያ ነጻነት በሰፊው ተከፍቷል ማለት ይቻላል፡፡ ሚዲያዎች ከብሮድካስት ባለስልጣን ምዝገባ እና ፈቃድ ሲያገኙ ይስተዋላል፡፡ ጋዜጠኞችና የተለያዩ ዜጎች በሚያስላልፉት ሃሳብ የሚከሰሱበት አጋጣሚ ከናካቴው ባይጠፋም ቀንሷል፡፡ የሚዲያና የሲቪክ ማህበራት አፋኝ ሕጎችን የማሻሻል እርምጃዎችም እየተካሄዱ ነው፡፡ ነጻነቱ ግን ጽድቅን ብቻ ሳይሆን እርግማንም ይዞ መጥቷል፡፡ የጋዜጠኝነት ገለልተኛነት እና እውነተኛነት መሠረታዊ የሙያ ስነምግባር አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ 

የብሔር ተኮር ሚዲያዎች ሁሉን በኩል መነጽር ማየት አቅቷቸዋል፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጲያ ሚዲያዎች፣ በተለይም በከፍተኛ ወጪ የሚተዳደሩ የመንግስት ሚዲያዎች አደረጃጀት ብሔር ተኮር ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልል የራሱን ብሔር ድምጽ የሚያስጋባ ቴሌቭዥን አለው፡፡ ይሄም ሚዲያዎቹን ያሉባቸውን የገለልተኛ እና እውነተኛነት የሙያ ስነምግባር እንዲወጡ እድሉን ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ የሚወክሉት ብሔር ከሌላው ጋር ያለበትን የኢኮኖሚና የግዛት ጥያቄ፣ የማኀበራዊ እሴትና የታሪክ ትርክት እሽቅድድሞሽ እንዲያሸንፉ ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ አንዱ ሌላው ብሔር የሀገሪቷን ሀብት፣ የፖለቲካ ስልጣን እና የእሴት የበላይነት ለአመታት ተቆጣጥሮ እንደከረመ፣ የራሱ ብሔር የዓመታት ተጨቋኝ እንደነበር ይተርካል፡፡ 

በተለይ በግጭት ጊዜ የሚኖርባቸውን ለሁለቱም ጎራ እኩል ድምጽ የመስጠት፣ ኩነቶች አንደ አቀማመጣቸው የመዘገብ እና ተገቢውን የግጭት አፈታት አካሄድ ላይ ትኩረት የመስጠት ኃላፊነት ለመወጣት አልቻሉም፡፡  የብሔር ተኮር ኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ይህንን አይፈቅድም፡፡ ለተቋቋሙለት የብሔር ቡድን የተሻለ ድምጽ የመስጠት እና ጥፋቶቹን የመደበቅ አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ የቆሙለት ብሔር ከግጭቶች መንስኤነት ያስጥሉታል፣ ሁሌም እራሳቸውን በመከላከል ላይ እንደሆኑ ይተርካሉ፡፡ እውነትንም በተደጋጋሚ አንገቷን ያስደፏታል፡፡ 

ተገቢው ትኩረት የተነፈገው የክልል መንግስት ኃላፊዎች መልዕክቶች

የጥላቻ ንግግር በማኅበራዊ እና መደበኛ ሚዲያዎች ላይ ብቻ ይተላለፉሉ የሚሉ ምልከታዎች አሉ፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ እና ሙሉዕ ምስል የማይከስት ነው፡፡ የጥላቻ ንግግሮች ከሚያስተላለፉ ግለሰቦች ውስጥ ዋነኞቹ የክልል ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ክልሎቹ የተዋቀሩት በብሔር ማንነት፤ በተለይም በቋንቋ ነው፡፡ ዘጠኙም ክልሎች ለተለዩ ማንነቶች ብቸኛ ግዛት ተደርገው ይቆጠራሉ - በሀገሪቷም ሆነ የክልል ሕገ መንግስቶች መሠረት፡፡ በዚህም ምክንያት የክልል ኃላፊዎች የሚወክሉት በክልላቸው ውስጥ የሚኖሩትን የተለየ የብሔር አባላትን ብቻ ይሆናል፡፡ በክልሎች ውስጥ የተለያዩ የብሔር ማንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች የመኖራቸው እውነታ ተክዷል፡፡ በሀገር ግንባታ ሂደት በነበረው የህዝቦች መስተጋበር ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ተቀየጠው መኖራቸው ተዘንግቷል፡፡ በዝምድና እና ለስራ ዜጎች በሀገሪቷ ጫፍ ጫፍ ተዳርሰዋል፡፡ የቅርቡ በደርግ ዘመነ መንግስት፣ በ1977 ዓ.ም የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ እንኳን በሰፈራ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የሰፈሩ ሕዝቦች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ 

ነገር ግን እነዚህ በክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ሌላ የብሔር አባላት የፓለቲካ ውክልና ያጣሉ፡፡ የክልሎቹ ባለስልጣናት ኃላፊነታቸው ለሚያስተዳደሩት የተለየ ብሔር ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህም የክልል ባለስልጣናት በክልሎች ውስጥ የሚኖሩ የተለዩ ብሔሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሌላውን የመጉዳት አዝማሚያ ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካችን መሠረት የሆነውን ባለቤት-መጤ ትርክት እንዲያራምዱ ምክንያት ይሆናል፡፡ ሌላ ብሔሮች በወረራ እንደመጡ፣ ያፈሩት ንብረት፣ መሬታቸውም የራሳቸው እንዳልሆነ ሊያስተጋቡ ይችላሉ፡፡ ጥላቻቸውን ይዘራሉ፣ በክልላቸው ውስጥ ባለው ኅዳጣን ላይ አድሎ፣ ጥቃትም እንዲደርስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሔደ የኦሮሞ የምስጋና በአል፣ እሬቻ ላይ የኦሮሚያ ክልልን በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚያስዳደሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተናገሩት "ነፍጠኛውን ሰበረነዋል" ንግግር ሊጠቀስ እንደምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ "ነፍጠኛ" በምክትል ፕሬዝዳንቱ አነጋገር አዲስ አበባን የወረረውን፣ አሁንም ይዞ የሚገኘውን ማህበረሰብ ሊያመላክት ይችላል፡፡ በተመሳሳይ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጀዋር "ጥቃት ሊደርስብኝ ነው" የሚል መልእክት ተከትሎ በክልሉ ውስጥ በደረሱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች "ነፍጠኛ ይውጣልን" የሚለው አመለካከት አካል ነው፡፡ 

የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ኃላፊዎች የሚወክሏቸው ብሔሮች፣ ተከታዮቻቸው ለመዋለ ነዋያት በሚያደርጉት ውድድር ከሌላ ቡድኖች ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ያበረታታሉ፡፡ በክልላቸው ውስጥ ግጭቶች በሚኖሩበት ጊዜ የአንዱን፣ የሚወክሉትን ብሔር የመወገን አካሄድ ይኖራል፡፡ የሚወክሉት ማህበረሰብ "እራስህን ተከላለከል፣ ሀብትህን ጠብቅ" በሚል ሊያነሳሱት ይችላሉ፡፡ የጸጥታ ሀይላቸውንም "በመጤው" ላይ ሊዘምቱ ይችላሉ፡፡ የክልል የጸጥታ ሀይሎች አንዱን ብሔር ሲወግኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ታዝበናል፡፡ የሚወክሉት ተጠቂ ሌላው አጥቂ አድረገው የመሳል አዝማሚያ ይኖራል፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን ሌላው ብሔር ካለቦታው የመጣ፣ ሰፋሪ የሚል የሀገሪቷን ማእከላዊ የፖለቲካ ትርክት እንዲያራምዱ ምክንያት ይሆናል - በብሔር የተወሰነ የፓለቲካ ውክልና፡፡ 

ይሄ ስርዓት ከፍ ሲልም የክልሉ አስተዳዳሪዎች ከክልላቸው ውስጥ ያልፈለጉትን የማስወጣት፣ የራሴ የሚሉትን ብሔር ደግሞ በፈለጉት ቦታ የማስፈር መብትን ያጎናጽፋቸዋል፡፡ ሰፈራ በጥንቃቄ ካልተካሄደ በቦታው ያለውን የማህበረሰብ ጥቅም እና ማህበራዊ ስብጥር ሊያዛባ፣ ግጭት አንዲነሳሳም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የጥቅም አድሎዎች ሊፈጠርም ይችላል፡፡ በቅርቡ ከሌላ ክልል የተፈናቀሉ ማህበረሰቦችን ለማስፈር በተደረገው ጥረት፣ የሀገሪቷን ማእከል ማኀበራዊ ስብጥር ወደ አንድ ብሔር የማዘንበል ዓለማ መኖሩ መታየቱ ውጥረት መፍጠሩ ይታወሳል፡፡

በክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ኅዳጣንን ውክልና ለማስጠበቅ እንደአማራጭነት የተያዘው ልዩ ዞን እና ወረዳ የሚባሉ አስተዳደራዊ አነስተኛ መዋቅሮችን በክልሎች ውስጥ መመስረት ነው፡፡ ይሄ አካሄድም ለአንዱ የመብት ጥያቄ ሲሆን ለሌላው የተስፋፊነት አደጋ ነው፡፡ ይሄን "ተስፋፊነትን" ለመመከት የክልል ኃላፊዎች የሌሎች ብሔሮችን ራስ የማስተዳደር መብት ከመከልከል በዘለለ፤ የነበራቸውንም እስከማሳጣት የሚዘልቅ መልዕክትንም ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ "ተስፋፊነትን መክቱ" በሚል ትርክት፣ የጥላቻ ወንጀሎችን ሊያበረታቱ ይችላሉ፡፡

በብሔር የታጠረ የፓለቲካ ውይይት

የድህረ 1983 ዓ.ም ኢትዮጲያ የፓለቲካ ውይይት፣ የፓርቲዎችና የተለያዩ የሲቪክ ማህበራት አደራጃጀት በብሔር ሆኗል፡፡ ይሄም የቋንቋን ወሳኝነት በሰፊው በመለጠጥ እና የባህል ልዩነቶችን በመጠቀም የብሔር ተሟጋችነት ማዕረግን ለብዙዎች አጎናጽፈዋል፡፡ ይህንን ማዕረግም በሀገር አቀፍና በክልል ያላቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የማኅበራዊ ቦታ እና የፖለቲካ ፍላጎት መጠቀሚያነት ያውሉታል፡፡ ይሄ ፍላጎታቸው እንዳይቋረጥም "ለሚዋጉለት" ብሔር አደጋ የሚሆን ሌላ ብሔር ይፈጥራሉ፡፡ ቁርሾ ይዘራሉ፣ የጥላቻ ንግግርም በየሚዲያውና በሚያገኙት መድረክ ላይ ያስተጋባሉ፡፡ 

የፖለቲካ ውይይቶችን በብሔር ላይ የታጠሩ መሆናቸው በግዛት፣ በግጦሽ መሬት፣ በውሃ እና በመሳሰሉት የሚነሱ የግለሰብ እና የአነስተኛ ጎሳ ግጭቶች ወደ ጋራ ጠቦች/ጥያቄዎች ተቀይረው የማንነት፣ የብሔር ጠብ መልክ እንዲይዙ ምክንያት ይፈጥራል፡፡ በጊዶ-ጉጂ፣ በትግራይ-አማራ፣ ሶማሌ-ኦሮሞ፣ እና የመሳሰሉት ግጭቶች ለዘመናት የነበሩ፣ መነሻቸው በትናንሽ ግዛቶች እና መዋለ ንዋዮች የነበሩ፤ በትናንሽ ቅርበት ባላቸው ቡድኖች መካከል ብቻ የታጠሩ ነበር፡፡ የብሔር ትኩረት ሲሰጠው ግን በሁለት ብሔሮች መካከል እንደሆኑ ተደርገው ይሳላሉ፡፡ የብሔር ወኪል ነኝ ባዩች በሌላ ብሔር ወገንህ ተጠቃ ብለው በሰፊው ያስተጋባሉ፡፡ ለቦታው ቅርበት የሌላቸውን እና ለጥቃቱ ተጋላጭ ያልሆኑ የብሔሩ አባላት፤ አጥቂውን እንዲጠሉ፣ ባገኙበት አጋጣሚ አድሎ እንዲፈጽሙ፣ ጥቃትም እንዲያደርሱ ያነሳሳሉ፡፡ ሕዝቡም በመቶዎች ኪሎሜትር ርቀት ላይ ለተፈጠሩ ግጭቶች፣ ጎረቤቱ ያለውን የብሔር አባል ለማጥቃት ይነሳል፡፡ ግጭቶቹም እየተስፋፉ ወደ ማይታረቁ ፍላጎቶች፣ የብሔር ልዮነቶች ያድጋሉ፡፡ ሞት እና መፈናቀል አንደዋዛ ይከሰታል፡፡

ችግሩን ከመሰረቱ

የጥላቻ ንግግሮችን ለመዋጋት ከሚደረጉ አካሄዶች ውስጥ የሕግ ክልከላ፣ የሚዲያ ቁጥጥር አካሄድ ማቋቋም፣ ማንነታቸው ለሚጠለሽና ለአድሎና ጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰብ ድምጽ የሚሆን አራማጅነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ስልቶች ጊዜያዊ መፍትሔ ከመስጠት የዘለለ አቅም የላቸውም፡፡ በጊዚያዊነት የሚሰጡትም መፍትሔ ርዕትነት የሚጎድለው ይሆናል፡፡ የሕግ አስፈጻሚዎች የአንዱ ብሔር ወኪል በሆኑበት ሁሉንም ጎራ እኩል መጥቀም እና መቆጣጠር አይቻላቸውም፡፡ አንዱ ብሔር የወከላቸው ዐቃቤ-ሕግ የወከላቸውን ብሔር ትርክት የጠብ መንስኤ ነው ብለው እንዲነሱ እንዴት ይጠበቃል? በብሔር ኮታ ከሚቋቋም፣ ሹመት በተራ በሚደረግበት የብሮድካስት ባለስልጣን ሁሉም የብሔር ሚዲያዎች የሚያስላለፉትን መልእክት እኩል ማየት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ የሚዲያ ቁጥጥር በብሔር ከተደራጀ፤ የአንዱን ማጋነን፣ የሌላው ማኮሰስ መኖሩ አይቀርም፡፡ እውነትን እያነፈነፉ ከማጋለጥ ይልቅ አጀንዳ ለመቅረጽ፣ ትርክቶችን አቅጣጫ ለማስያዝ ጥረት ቢያደጉ አይገርምም፡ አራማጆች በብሔር ተደራጅተው እንዴት የጥላቻ ንግግር ተጠቂዎችን በኩል ዓይን ያያሉ? ጭራሽ የራሳቸውን ብሄር ጥቃት እያገነኑ የጥላቻ ወንጀሎችን ያነሳሳሉ እንጂ፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል?

ብሔር እና ማንነት ከስልጣን መቆናጠጫነት፣ ከመንግስታዊ መዋቅር ብቻ ሳይሆን ከሚዲያ አደረጃጀት መውጣት አለባቸው፡፡ ማንነት የስነ ልቦና እና ማህበረሰብያዊ ወሳኝ እሴት ነው፡፡ ቋንቋ መጎልበት ፣ ባህል መዳበር፣ ታሪክ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ማንነት የውድድር ማእከል በሆነበት፣ "የአንዱ የኢኮኖሚ እና ፓለቲካ ተጠቃሚነት፣ የማህበራዊ እሴቱም መጎልበት፣ በሌላው መውደቅ ላይ ይመሰረታል" አይነት ትርክት እና መዋቅር ተይዞ ከጥላቻ ንግግር፣ አድሎ እና ጥቃት እናመልጣለን ማለት ከንቱ ልፋት ይሆናል፡፡ 

ይሄ ፅሁፍ የጥላቻ ንግግርን እና ሐሰተኛ መረጃ በኢትዮጲያ ያለበትን ሁኔታ ቅርጽ ለመስጠት በሰባ ደረጃ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኃላ.የተ.የግል ማኅበር፣ የአዲስ ዘይቤ እና ጎበና መንገድ አታሚ እና በኢንተርኒውስ፣ የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ዜናዎችን እና መረጃዎችን እንዲያዘጋጁ ማገዝን አላማው ያደረገ ለትርፍ ያልተቋቋመ አለም አቀፍ ድርጅት ትብብር የሚዘጋጁ ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ የሚዲያ ውጤቶች አካል ነው፡፡©በሰባ ደረጃ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኃላ.የተ.የግል ማኅበር2012 ዓ.ም.

አስተያየት