ግንቦት 24 ፣ 2013

ሕጎች ከሰብአዊ መብት አኳያ ሊፈተሹ ይገባል ተባለ

City: Addis Ababaሕግወቅታዊ ጉዳዮች

በመረቀቅ ሂደት ላይ የሚገኙ ክልሎች የሴቶችን እና የህጻናትን መብቶች ያገናዘቡ መሆን እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።

ሕጎች ከሰብአዊ መብት አኳያ ሊፈተሹ ይገባል ተባለ

(አዲስ ዘይቤ፡ አዲስ አበባ) የቤተሰብ ሕግ ያጸደቁ ክልሎች አተገባበሩ ላይ ያለውን የአረዳድ ልዩነት እንዲያጠሩና፤ የቤተሰብ ሕግ ያልተደነገገባቸው ወይም በመረቀቅ ሂደት ላይ የሚገኙ ክልሎች የሴቶችን እና የህጻናትን መብቶች ያገናዘቡ መሆን እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።

ኢሰመኮ ከቀጣዩ ዓመት ግንቦት 2004 ዓ.ም ቀን ጀምሮ የሚታሰበውን ዓለም አቀፍ የወላጆች እና የአሳዳጊዎች ቀን አስመልክቶ ነው በዛሬው እለት ጥሪውን ያስተላለፈው፡፡ ‹‹በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም. የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የወላጆችን እና የአሳዳጊዎችን ሚና ጎልቶ እንዲታይ ማድረጉ ቀኑን ለማሰብ በተዘጋጁ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለምአቀፍ መድረኮች እየተገለጸ ነው።›› ያለው መግለጫው “ምስጋና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወላጆች እና አሳዳጊዎች” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወላጆች እና አሳዳጊዎችን ቀን አስቦ መዋሉን አሳውቋል፡፡

ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ያለውን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በግጭቶች እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ሳቢያ ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ፣ የተሰደዱ፣ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ያጡ፣ በጎዳና ለመኖር፣ ለጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲሁም ለተለያዩ አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳቶች የተዳረጉ ሕጻናት እና አሳዳጊዎች መኖራቸው፣ በእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሕጎች እና ፖሊሲዎችን ወቅታዊነትና አግባብነትን መፈተሽን የሚያስገድድ ስለመሆኑም አንስቷል፡፡

የፌዴራል እና የተለያዩ ክልሎች የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ ኮሚሽኑ የሚያተኩርባቸውን የሕግ እና የፖሊሲ ማእቀፍ ቀረጻና ማሻሻያ የማድረግና የመተግበር ግፊት ሥራዎች ተለይተዋል ብሏል፡፡

አስተያየት