ግንቦት 24 ፣ 2013

በጅግጅጋ በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ሹፌሮች መቸገራቸውን ገለፁ

City: Jigjigaዜናዎች

በማደያ 22.50 ብር የሚሸጠው አንድ ሊትር ቤንዚን ለቸርቻሪዎች በ25.50 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ ታዝባለች፡፡

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በጅግጅጋ በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ሹፌሮች መቸገራቸውን ገለፁ

(አዲስ ዘይቤ-ጅግጅጋ) በጅግጅጋ ከተማ ከሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባጋጠመው የቤንዚን እጥረት ምክንያት በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ 12 የነዳጅ ማደያዎች መካከል አንዱ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ አረጋግጣለች።

የቤንዚን እጥረት ካገጠመ ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ካሉት ማደያዎች ውስጥ ጎመጁ የሚባፃለው የነዳጅ ማደያ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በማደያው ረጅም ሰልፍ ተስተውሏል፡፡ በዚህም የተነሳ በከተማው የሚገኙ የባጃጅ ሾፌሮች በነዳጅ እጦት መቸገራቸውን ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል። አገልግሎት እየሰጠ በሚገኝው ብቸኛ ማደያ ተገኝቶ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ያነጋገረው የባጃጅ አሽከርካሪ ቤንዚን ለመቅዳት ወረፋው ረጅም በመሆኑ፤ የስራ ጊዜውን እያባከነበት እንደሆነ አስረድቷል፡፡

"ቤንዚን ለመቅዳት ከሶስት ሰዓት በላይ ተሰልፌ መጠበቅ አለብኝ" ሲል ምሬቱን ገልጿል።

በዚህም የተነሳ አሽከርካሪዎች ከህገወጥ ቸርቻሪዎች በጥቁር ገበያ በከፍተኛ ዋጋ ነዳጅ ለመግዛት እንደተገደዱ ያስረዳል።

በማደያ 22.50 ብር የሚሸጠው አንድ ሊትር ቤንዚን ለቸርቻሪዎች በ25.50 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ ታዝባለች፡፡

"የልጆች አባት ስለሆንኩኝና መስራት ስላለብኝ ሰዓቴን ላለማባከን በችርቻሮ የሚሸጠውን በሌትር በ35ብር ለመግዛት ተገድጃለሁ፡፡» ይላል ሌላኛው የባጃጅ አሽከርካሪ ሁሴን ሙሳ።

“በጅግጅጋ ከተማ የቤንዚን እጥረት ተከሰተ የሚባለው በጣም በተደጋጋሚ ነው፡፡ አንዳንዴ ነዳጅ ማደያዎች ሆነ ብለው የለም በማለት በድብቅ ዋጋውን ጨምሮ ለሚቸረችሩ ግለሰቦች ይሸጣሉ፡፡ የከተማው ንግድ ቢሮም ጠንካራ የሆነ ክትትልና እርምጃ ሲወስድ አይታይም፡፡ እጥረት ከመፈጠሩ በፊት ራሱ ከቶታልና ጎመጁ የነዳጅ ማደያዎች ውጪ ያሉት ሌሎቹ በአግባቡ አያስተናግዱንም፡፡” በማለት በከተማዋ በተደጋጋሚ በሚፈጠረው የቤንዚን እጥረት ግዜያቸውንና ገንዘባቸውን እያባከነባቸው እንደሆነ የተናገሩት ደግም ሌላኛው አሽከርካሪ ዋለልኝ መብራቱ ናቸዉ፡፡

"አንድ የነዳጅ ቦቴ ከጅቡቲ ተነስቶ አዳይቱ የሚባል ቦታ ስለተበላሸቶብን ተጠግኖ ጅግጅጋ ለመድረስ ዘጠኝ ቀን ወስዶበታል፡፡ ነዳጁ ከደረሰ በኋላ ከሌሊቱ 12 ሰዓት ጀምረን አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን፡፡" ሲሉ የጎመጁ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ሞላ  ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በከተማው ያሉት አብዛኞቹ  ማደያዎች አንዳንዴ ነዳጅ እያላቸውም ለመሸጥ ፍቃደኛ አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም ለቸርቻሪዎቹ እትርፎ መሸጥ ስለሚያዋጣቸው ይላሉ አቶ አብርሃም፡፡

"ለማሳያነት አሁን ተከሰተ የሚባለውን የቤንዚን እጥረት እንኳን ብንወስድ ከጀቡቲ ምንም አይነት እጥረት በሌለበት ሁኔታ ነው፡፡” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ጉዳዩን አስመልክታ አዲስ ዘይቤ ጥያቄ ያቀረበችለት በጅግጅጋ ከተማ ንግድና እንዱሰትሪ ቢሮ መርማሪና ተቆጣጣሪ የሆኑት የአቶ  መሃመድ አብዱላሂ ሀሳብ ከዚህ የተለለየ ነው፡፡

«የቤንዚን እጥረቱ የተፈጠረው በጅግጅጋ ከተማ ብቻ ሳይሆን፡ በጅግጅጋ ዙሪያ ባሉ  ወረዳዎችም ጭምር ነው፡፡ የእጥረቱ ምክንያት ደግሞ በጅቡቲ ካለው የነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ ነው፡፡» ብለዋል። አክለውም« ችግሩ ከተከሰተ ግዜ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ በመደወል ነዳጅ ማደያዎቹ በቶሎ ቤንዚን እንዲያስገቡ እያደረገን ነው፡፡ ስለዚህ እስከ ነገ ድረስ ችግሩ ይፍታል ብለን እናምናለን፡፡ በከተማው ያሉ የነዳጅ ማደያዎች በህግወጥ ንግድ እንዳይሰማሩ ከፖሊስ ጋር ሆነን ቁጥጥር እያደረገን እንገኛለን፡፡ ነዳጅ ማደያዎቹን ቀን ቀን በፖሊስ እንጠብቃለን፣ ማታ ድግሞ ዘግተን እንሄዳለን፡፡ በዚ ዙሪያ ጥቆማም ሲመጣ እያጣራን ነው፡፡” በማለት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አስረድተዋል፡፡

አስተያየት