ግንቦት 26 ፣ 2013

“ኢትዮ-ሳት”ን ያልተቀላቀሉት ሦስቱ ጣቢያዎች

ሚዲያ ወቅታዊ ጉዳዮች

“ኢትዮ-ሳት” የተሰኘው ሳተላይት ይፋ ከሆነ 1 ዓመት ከ5 ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ 97 የሚሆኑ የሐገር ውስጥ ጣቢያዎችን ማካተት እንደቻለም ተነግሮለታል፡፡

“ኢትዮ-ሳት”ን ያልተቀላቀሉት ሦስቱ ጣቢያዎች

በሐገር ውስጥ ቋንቋዎች ለኢትዮጵያውያን የሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንደሚተላለፉበት የተነገረው “ኢትዮ-ሳት” የተሰኘው ሳተላይት ይፋ ከሆነ 1 ዓመት ከ5 ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አገልግሎቱን መጠቀም ከጀመሩ ደግሞ ከሁለት ወራት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ 97 የሚደርሱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንደተቀላቀሉት የተነገረለት የሳተላይት ጣቢያው የዲሽ ሰሀንን ወደ “ኢትዮ-ሳት” አቅጣጫ ማዞርን መጠየቁ የበርካቶች ቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሰራሩ በፈጠረው ቅሬታ ምክንያት የሳተላይት መቀበያ (ዲሽ) ሰሀናቸውን ወደ “ኢትዮ-ሳት” ላለማዞር የወሰኑ ተጠቃሚዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ የባለሙያ እጥረቱን ለመቅረፍ ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደ ስራ የገባው “ኢትዮ-ሳት” ለቴሌቪዥን ባለ ንብረቶች ለሳተላይት ኪራይ የሚያከፍሉት ዓመታዊ ኪራይ ላይ በሚያስገኘው ቅናሽ ምክንያት በባለንብረቶቹ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በጊዜ ሂደትም አብዛኛዎቹን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ማቀፍ ችሏል፡፡ 97 የሚሆኑ የሐገር ውስጥ ጣቢያዎችን ማካተት እንደቻለም ተነግሮለታል፡፡ 

የኢትዮ-ሳት እና ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ስትገለገልበት የቆየችው የ“አረብ-ሳት” እና የ“ናይል-ሳት” ሳተላይቶች መገኛ በተቃራኒ አቅጣጫ መሆኑ በ“ኢትዩ-ሳት” የሚተላለፉ የቴሌቪዥን መሰናዶዎችን መመልከት የፈለገ ሰው የመቀበያ ሰሐኑን የማዞር ግዴታ ይጣልበታል፡፡ ይህ መሆኑ በቀደሙት ሳተላይት ጣቢያዎች የሚተላለፉትን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያሳጣዋል፡፡ ሁለቱንም የማየት ፍላጎት አለኝ የሚል ተጠቃሚ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ሰሀን መግጠምን ግድ ብሎታል፡፡

የ“ኢትዮ-ሳት” እና ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ስትገለገልበት የቆየችው የ“አረብ-ሳት” እና የ“ናይል-ሳት” ሳተላይቶች መገኛ በተቃራኒ አቅጣጫ መሆኑ በ“ኢትዩ-ሳት” የሚተላለፉ የቴሌቪዥን መሰናዶዎችን መመልከት የፈለገ ታዳሚ የመቀበያ ሰሐኑን የማዞር ግዴታ ይጣልበታል፡፡ ይህ መሆኑ በቀደውት ሳተላይቶች በመጠቀም ፕሮግራሞቻቸውን የሚያሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ያሳጣዋል፡፡ ሁለቱንም የማየት ፍላጎት አለኝ የሚል ተጠቃሚ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ሰሀን መግጠምን ግድ ብሎታል፡፡

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው ጌታሁን አየለ የተባለ ወጣት “ሁለት የዲሽ ሰሀኖችን ለመግዛት ተገድጃለሁ” ይላል። ነፃነት ግርማ ደግሞ ያላትን እንድ የዲሽ ሰሀን ወደ ‘ኢትዮ-ሳት’ ከለወጠች ሠነባብታለች። አብዛኛዎቹን ጣቢያዎች በጥራት ማግኘቷ ቢያስደስታትም “እንደ በፊቱ ያሻኝን የማየት ምርጫዬን ገድቦታል” ትላለች።

ይሕ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ በኢትዮ-ሳት በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ካሉ ጣቢያዎች የተካተቱት ከ90 በላይ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የኤስ.ኢ.ኤስ ድርጅት ዳይሬክተር መነን አገኘው ነግረውናል። ጣቢያዎች ለሳተላይት የሚከፍሉት ገንዘብም ከነበረው በግማሽ ቀንሷል። ይህም የበፊቱ ሳተላይት ሰሜንን እና መካከለኛው ምስራቅ አፍሪካን ኢላማ አድርጎ የተዘረጋ ስለነበረ ነው። ሳተላይት ሰፊ ቦታ ስለሚያካልል እና ኢላማው ከሆነው አካባቢ በተጨማሪ በዙሪያው ላሉትም አገልግሎት ስለሚሰጥ ኢትዮጵያም የተከራይ ተከራታይ በመሆን ስትጠቀም ቆይታለች። አሁን ለራሷ የተዘጋጀውን ‘ኢትዮ-ሳት’ ተቀብላለች ይላሉ ዳይሬክተሯ። እንደ እርሳቸው አባባል እንደዚህ ዓይነት ሳተላይት እንዲመጣ ቀደም ብለው ጣቢያዎች ፍላጎት ሲያሳዩ እና ሲጠይቁ ነበር።

ይሁን እንጂ ውሱን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሁንም ቀድሞ በነበሩበት ሞገድ ላይ መቆየትን መርጠዋል፡፡ ኢትዮ-ሳትን ካልተቀላቀሉት ጣቢያዎች ውስጥ መረጃ ቲቪ፣ ትግራይ ሚድያ ሐውስ እና ኦሮምያ ሚስያ ኔትወርክ ይጠቀሳሉ፡፡ 

ኢትዮ-ሳትን በዋነኝነት ለሚያስተዳድረው ኤስኢኤስ (SES) የተሰኘው ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሚስስ ሳሚያ ሳቤር “ጣቢያዎችን የምትቀበሉት በምን መስፈርት ነው?” የሚለውን ጥያቄአችንን ሲመልሱ "እኛ ደንበኞቻችንን ሁልጊዜም የምንጠይቀው በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ በሀገሪቱ አገልግሎቱን ለማድረስ የተመዘገበበትን ወረቀት እና የንግድ ፍቃድ እንዲሰጠን ነው" ያሉ ሲሆን "ትግራይ ሚዲያ ሀውስ፣ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ እና መረጃ ቴሌቪዥን ስርጭታቸውን በኢትዮ-ሳት ለማድረግ ጥያቄ አቅርበው ከሆነ እና  ከጠየቁ የእናንተ ምላሽ ምን ነበር?" ስንል ላስከተልነው ጥያቄ

"ትግራይ ሚድያ ሀውስ ከቀደሙት ደንበኛቻችን ውስጥ አንዱ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ራሡ ትቶታል። ማንኛውም የመገናኛ ብዙኃን ወደ ኢትዮ-ሳት ለመግባት ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ፍቃድ ይዞ መምጣት አለበት። ኦሮሚያ ሚድያ ኔትዎርክ እና መረጃ ቲቪ ይህን ወረቀት ይዘው እንዲመጡ አሁንም እየጠበቅናቸው ነው።" ይላሉ ኃላፊዋ።

ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የመገናኛ ብዙኃን ምዝገባ፣ ፍቃድ እና እውቅና ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን አስረስ እንዳረጋገጥነው ኦሮሚያ ሚድያ ኔትዎርክ ፍቃዱ ተሠርዟል፣ መረጃ ቲቪ ፍቃድ እስኪያወጣ በኢትዮጵያ ያለው ቢሮው ተዘግቷል፣ ትግራይ ሚዲያ ሀውስ በባለሥልጣኑ አይታወቅም እንዲሁም እንደ ኦኤምኤን  ፍቃዱ ተነስቶ የነበረው ትግራይ ቴሌቪዥን አሁን ተመልሶ በኢትዮ-ሳት ውስጥ ተካቷል። "ያለ ፍቃድ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ የሚሠራ ጣቢያ ይቀጣል" በማለት ዳይሬክተሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።

እነዚህ ጣቢያዎች ሳተላይቱን እንዲቀላቀሉ አይፍቀድላቸው እንጂ መቀመጫቸውን በሌሎች ሀገራት አድርገው በሌሎች ሳተላይቶች ስርጭታቸውን ቀጥለዋል። "ሌሎች ሳተላይቶች በቀላሉ ይቀበላሉ የሚባል ነገር ሰምቻለው። እኛ ደግሞ በሕጉ መሠረት አስፈላጊ እና መሠረታዊ የተባሉ ቻናሎች አካተናል" የሚሉት  የኤስ.ኢ.ኤስ (SES) በኢትዮጵያ ዳይሬክተር መነን አገኘው ናቸው። የሀገር ውስጥ እና የውጪ ጣቢያዎች ድምፁ በማይረብሽ እና የምስል ጥራቱ ከፍተኛ በሆነ ቴክኖሎጂ ተካተዋል ያሉት ኃላፊዋ የዲሽ ሰህን የመቀየሩም ጉዳይ የሳተላይቱ አቀማመጥ እንጂ የተለየ ምክንያት የለውም ይላሉ። “አስፈላጊና መሰረታዊ” ያሏቸውን ጣቢያዎች ምንነት እና እንዴትነት ሲያብራሩ ለሀገር ውስጥ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ የተሰጣቸው መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበር ኃላፊ አቶ እንዳሻው ወልደሚካኤል በበኩላቸው የዚህ ድርጅት ሣተላይት እና ኢትዮጵያ ያስመነጠቀችው ሳተላይት አቀማመጣቸው ተቀራራቢ እንደመሆኑ ከ2 ዓመት በኃላ ኢትዮጵያ የራሷን የኮሚኒኬሽን ሳተላይት ስታመጥቅ የዲሽ ሰሀኑ አሁን በተቀየረበት አቀማመጥ ለመቀጠል ያመቻታል።

ኢትዮ-ሳትን ካቀረቡት ባለሙያዎች በተጨማሪ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጋዜጠኝነት እና ኮሚንኬሽን መምህር "የአሠራሩ ጉዳይ፣ የጥራቱ፣ እና ለጣቢያዎቹ ያለው የዋጋ መሻሻል እንዳለ ሆኖ ሁሉንም በአንድ ቋት ሰብስቦ ማቅረቡ ሰው የፈለገውን ለመናገር እና ለመግለፅ ያለውን ሰብአዊ  መብት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት ይጋፋል ብዬ እሰጋለው" ብለውናል። 

አስተያየት