በ1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያሳተመው መዝገበ ቃላት “ሕገ-መንግስት ማለት አንድ አገር የሚተዳደርበትና ሕዝቦች ለሚያከናውኗቸው ተግባሮች ሁሉ መርህ የሚሆናቸው የሁሉም የበላይ የሆነ ሕግ ነው” በማለት ይተረጉመዋል።
በርግጥ ሕገ-መንግስት ከላይ በተቀመጠው ትርጓሜ መሰረት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን ከሕግ ሙያና ከፍትህ አካላት ተልዕኮ አንፃር ለመረዳት በሕግ መዝገበ ቃላት እና በሕግ መፅሃፍት ውስጥ የተሰጡትን ትርጓሜዎች መመርመር ጠቀሜታ ይኖረዋል።
በዚሁ መሰረት ሕገ-መንግስት አንድ አገር የሚመራበትና መንግስት የሚተዳደርበት መሰረታዊ ሕግ ሆኖ እንደየአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ በፅሁፉ ተጠቃልሎ በሕገ-መንግስትነት የታወጀ ወይም በረዥም ጊዜ ልምድና በሕግ የዳበሩ እሴቶችና መርሆዎች ሊሆን እንደሚችል፤ የተፃፈም ሆነ ያልተፃፈ ሕገ-መንግስት የመንግስትን አወቃቀር፣ የመንግስት አካላት አደረጃጀትና ስልጣን እንዲሁም ተግባር የሚወስኑ ገዢ መርሆችንና ድንጋጌዎችን የሚያካትት መሆኑን፤ ሕገ-መንግስት የመንግስት ሉዓላዊ የሥልጣን ምንጭና መሰረት እንደዚሁም የመንግስት ወሰንና ገደብ የሚወስኑ መርሆችና ድንጋጌዎችን የሚይዝና መንግስት ሉዓላዊ ስልጣኑን ስለሚጠቀምበት አግባብ የሚደነግግ የሕግ ክፍል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሕገ-መንግስት በመንግስትና በዜጎች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት በተለይም መንግስት ለዜጎቹ ማክበርና ማስከበር ስላለበት ሰብዓዊ መብቶች ይዘት የአፈፃፀም ስርዓት መሰረታዊ መርሆችን የሚይዝ በፅሁፍ የታወጀ ወይም በልምድ የዳበረ የሕግ ማዕቀፍ እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል።
በኢትዮጵያ በነሐሴ ወር 1984 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 24/1984 ዓ.ም የሕገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በማወጅ የተቋቋመው የሕገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አረቀቀው የተባለውና እስካሁን ድረስ በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግስት በሕገ-መንግስት ጉባዔ አማካኝነት ሕዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ስራ ላይ ውሏል።
የኢትዮጵያን ሕገ-መንግስት በተመለከተ ከሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው ሕገ-መንግስቱን ማን ይተርጉመው የሚለው ይገኝበታል። አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 62 ላይ እንደሰፈረው ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። ዓለም ላይ የሚሰራበትን ሁኔታ ያላገናዘበ አካሄድ ነው የሚሉ የተለያዩ ምህራን ግን ሕገ-መንግስቱ መተርጎም ያለበት በፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን ከተለያዩ ተፅዕኖዎች ነፃ በሆነ ፍርድ ቤት አማካኝነት ነው ሲሉ ይሞግታሉ። በሌላ በኩል ግን ሕገ-መንግስቱ መተርጎም ያለበት በፍርድ ቤት ሳይሆን በፌደሬሽን ምክር ቤት ነው የሚሉ ምሁራን ሃሳባቸውን ያቀርባሉ።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሀበጋር በተሰኘ የክርክር እና የውይይት መድረክ ላይ ሕገ-መንግስቱን መተርጎም ያለበት የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው ባሉና ሕገ-መንግስቱ መተርጎም ያለበት በፍርድ ቤት ሲሉ አቋም በያዙ ሁለት ምሁራን መካከል ክርክር ተካሄዷል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ ማርኮን አባተ ሕገ-መንግስቱ መተርጎም ያለበት በፌደሬሽን ምክር ቤት ነው ብለው የተከራከሩ ሲሆን የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ በፍቃዱ አባተ ደግሞ ሕገ-መንግስቱ መተርጎም ያለበት በፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን በፍርድ ቤት ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
“የሌሎች አገሮች ልምድ እና ተሞክሮን የተመለከትን እንደሆነ ሕግ-መንግስትን የመተርጎም ስልጣን በቀጥታ ለፍርድ ቤት ከመስጠት ይልቅ የተለየ መንገድ ሲከተሉ ይስተዋል” የሚሉት አቶ ማርኮን “የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስትም በዓለም ላይ ያልታየ አዲስ እና ፈጠራ በታከለበት መንገድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የትርጓሜውን ሥልጣን መስጠቱ ትክክል ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን አንፀባርቀዋል።
ለዚህ አባባላቸው እንደምክንያት ያነሱት የመጀመሪያው የመከራከሪያ ነጥባቸው “ሕገ-መንግስት በአብላጫዉ ከሕግነቱ ይልቅ የፖለቲካ ሰነድነቱ ያመዝናል፤ ይህ ሰነድ ሲወጣ በፖለቲካ ዉሳኔ እንጂ በሕግ ዉሳኔ አይደለም፤ ስለሆነም ሊተረጉመውም የሚገባው የፖለቲካ ተቋም ነው” የሚል ነው።
ሁለተኛው የአቶ ማርኮን የመከራከሪያ ነጥብ “ሌሎች ሕጎች የሚወጡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ በመሆኑ የሚወጣዉ ሕግ የተወሰኑ አካላትን እንዳይነካና ከሕገ-መንግስቱ ጋር የሚጣረስ ነገር እንዳይኖረው የሚቆጣጠር የተለየ አካል ያስፈልገዋል ለዚህ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወሳኝ ተቋም ነው” ብለው እንደሚያምኑ አስቀምጠዋል።
“ሕገ-መንግስቱ ሲረረቅ ጀምሮ በውክልና የተሳተፉበት ዜጎች ሳይሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች በመሆናቸው ምክንያት ሕገ-መንግስቱን ሊተረጉመዉ የሚገባውም ይኸው የብሔር ብሔረሰቦች ውክልና ባለው አካል ነው ሲሉ ሶስተኛውን የመከራከሪያ ነጥብ ያነሱት አቶ ማርኮን ፍርድ ቤት የሙያ ተቋም እንጂ ለዉክልና ቦታ የለዉም፤ ከዛም በላይ ፍርድ ቤት በእዉነተኛዉ ዓለም ላይ የታዩ የህግ ግድፈቶችን የሚዳኝ ተቋም እንጂ ቀድሞ መርምሮ ሕግ የማሻሻል ስራ የመስራት ስልጣን የለውም ይላሉ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ግን በሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ እየታገዘ ይህን ስራ መስራት ስለሚችል ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ስልጣኑን ሊነጠቅ እንደማይገባ አንስተዋል።
በሌላ በኩል ሕገ-መንግስቱን መተርጎም ያለበት የፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን ፍርድ ቤት ነው ብለው የተከራከሩት አቶ በፍቃዱ ለዚህ አባባላቸው እንደ ምክንያት ካቀረቡት ሃሳብ መካከል የመጀመሪያው “በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ ዘጠኝ ላይ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ መሆኑን እንጂ የፖለቲካ ሰነድ እንዳልሆነ ይደነግጋል፤ ሕግ መሆኑ ከታወቀ ደግሞ መተርጎም ያለበት ሕግን የመተርጎም ተፈጥሮአዊ መብት ባለው ፍርድ ቤት ነው” ብለዋል።
በአቶ በፍቃዱ በኩል ከተነሳው የክርክር ነጥብ መካከል ሁለተኛው “በማኅበረሰብ ውል ፅንሰ-ሃሳብ (Social Contract Theory) መሰረት ዜጎች በነፃነት ሃሳባቸዉን አንሸራሽራው የተወሰነ መብታቸዉን ለመንግስት ይሰጡና ነገር ግን ይህንን ስጦታ አላግባብ እንዳይጠቀምበት በሕገ-መንግስት መሰረት ቃል ኪዳን የሚገቡ ሲሆን ይህን መብታቸው ሲነካ የሚያስጠብቁት እና ፍትሕ የሚያገኙት በፍርድ ቤት ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ደረጃ በዓለም ላይ የሌለ ሕገ-መንግስትን የመተርጎም ሥልጣን ለፌዴሬሸን ምክር ቤት መሰጠቱ ተገቢ ባለመሆኑ ሊነጠቅ ይገባል” በማለት ተከራክረዋል።
ሌላኛው የአቶ በፍቃዱ የመከራከሪያ ነጥብ “የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተቋቋመበት ዓላማ የተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣቸዉ ሕጎች አነስ ያለ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚጎዳ እንዳይሆን የሚቆጣጠር ተቋም እንዲሆንና ፍትሃዊ ሕግ እንዲያወጣ ማድረግ እንጂ ሕግ እንዲተረጉም ሥልጣን መሰጠቱ ከመሰረታዊ የሕግ እና የሕገ-መንግስት እሳቤ የወጣ እና አግባብነት የሌለው ነው” ሲሉ ኮንነዋል።
እርስዎ ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን የማን መሆን አለበት ይላሉ? ተወያዩበት።