በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ 573 ዕጩዎችን ያቀረበው እናት ፓርቲ እና 282 ዕጩዎችን ያቀረበው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት ከሆነ ምርጫውን ካሸነፉ መገናኛ ብዙኃንን ከመንግስት ጣልቃገብነት ነፃ እናደርጋለን ብለዋል።
አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን "የተናገርነውን ሃሳብ አያስተላልፉልንም" የሚሉት የኢሶዴፓ ዋና ፀሃፊ ዓለሙ ኮይራ የእሳቸው ፓርቲ ስልጣን ቢይዝ የመገናኛ ብዙኃን ለሁሉም ፓርቲዎች በእኩልነት እና በሃቀኝነት እንዲያገለግሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዓለሙ ገለፃ ከሆነ በግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ የሚተዳደሩ የመገናኛ ብዙኃን በተለምዶ “የመንግስት” የሚባሉት አሰራራቸው እንዲስተካከል ይደረጋል። ለጋዜጠኞች ተገቢው ደሞዝ እንዲከፈላቸው እና ዋስትና (ኢንሹራንስ) እንዲያገኙ እናደርጋለን የሚሉት ዋና ፀሃፊው የጋዜጠኞች እስር እና እንግልትን ፓርቲያቸው እንደሚቃወም አክለዋል።
"ከአፄ ስርዓት ጀምሮ ያለውን አሰራር በመቀየር በታሪክ የመጀመርያ እንሆናለን" ያሉት የእናት ፓርቲ የውጭ አደረጃጀት እና የውስጥ አመራር ክፍል ኃላፊ አቶ ኪሮስ አድማሱ መገናኛ ብዙኃን ማለትም ጋዜጠኞች ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው የሚስሩበትን አሰራር እንፈጥራለን ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ይህንን ሃሳባችንን ከግብ ለማድረስ በባለሙያዎች ብቻ የሚሰራ፣ የሚመራ እና በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ የብሮድካስት ባለስልጣን እንዲኖር በማድረግ ለህዝቡ የሚሠራ የመገናኛ ብዙኃን በመፍጠር ይቻላል ባይ ናቸው።
ነፃ ሆነው በራሳቸው መቆም ካለባቸው ተቋማት መካከል ውስጥ አንዱ የመገናኛ ብዙኃን እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ኪሮስ ፓርቲያቸው የጋዜጠኛውን መብት መቶ በመቶ የሚያስጠብቅ ፓሊሲ እንዳለው ተናግረዋል።
እውነተኛ ዴሞክራሲ ባለበት አገር ሚዲያ ከመንግስትና ከማኅበረሰብ ገለልተኛ ታዛቢ ሆኖ እንደሚያገለግል የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ያነሳሉ። ሚዲያ ሁለት ሥራዎች አሉት የሚሉት ምሁራን አንደኛው ህዝቡን ማሳወቅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመንግስት ባህሪን መታዘብና መመርመር ነው።