በአፋር ክልል ሀሩቃ በተባለ ቦታ ባለፈው ዓርብ በተሰነዘረ ጥቃት በትንሹ 30 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ50 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መቁሰላቸውን የአፋር ክልል የፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ጥቃቱን ፈጸሙ የተባሉት የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በዚያኑ ዕለት ምሽት ገዋኔ በተባለ ቦታ በከፈቱት ተኩስ ሁለት የክልሉ መንግስት ሰራተኞች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል። የሶማሌ ክልል ጥቃቱ የተፈጸመው “በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ነው” የሚለውን ውንጀላ አስተባብሏል።
የአፋር ክልል የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመድ ሁመድ ዛሬ እንደተናገሩት፤ ወደ ክልላቸው ዘልቆ የገባው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል፣ በሀሩቃ ቀበሌ ጥቃቱን የፈጸመው ከሁለት ቀን በፊት መጋቢት 25 ቀን ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ነው።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ወደ ቀበሌዋ ገብተው ተኩስ መክፈታቸውን የሚገልጹት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩ፥ በጥቃቱም “ከ30 በላይ ንጹሃን ዜጎች ተረሽነዋል” ብለዋል። በአርቡ ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ ከ50 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መቁሰላቸውንም አስረድተዋል።
በጥቃቱ የተጎዱት ሰዎች በሎጊያ እና ዱብቲ በሚገኙ ሆስፒታሎች በአሁኑ ወቅት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ጥቃት ሲፈጽም ነበር ያሉትን አንድ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባል እጅ-ከፍንጅ መያዛቸውን የሚናገሩት አቶ አህመድ፤ ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የአካባቢው ህብረተሰብ በወሰደው የመከላከል እርምጃ ሌሎች የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸውንም አክለዋል። መሰል ጥቃቶች ከዚህ ቀደምም በአካባቢው በተደጋጋሚ ይከሰቱ እንደነበር የሚናገሩት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩ፤ መንስኤውም “ከሶማሌ ክልል የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው” ይላሉ።
“በአፋር ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሦስት የኢሳ ቀበሌዎች አሉ። ‘የእኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስላሉ ቦታውን እንወስዳለን' የሚል የሶማሌ ክልል ግልፅ የሆነ አቋም አለ” ሲሉም ይወነጅላሉ።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት አርብ ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ገዋኔ በምትባለው ከተማ አካባቢ በከፈቱት ተኩስ ሁለት የአፋር ክልል የመንገድ ልማት እና ትራንስፖርት ቢሮ ሠራተኞች መገደላቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ በተጨማሪነት ገልጸዋል።
አብዱልቃድር ሁመር እና መሀመድ ሰይድ የተባሉት ሁለቱ ሰራተኞች የተገደሉት ለስራ ከአዋሽ ወደ ሰመራ በመኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር ተብሏል። በሀሩቃ እና በገዋኔ ተፈጸሙ ስለ ተባሉ ጥቃቶች የተጠየቁ አንድ የሶማሌ ክልል የመንግስት ሰራተኛ የአፋር ክልል ላደረሰው ጥቃት ምላሽ ከመስጠት በዘለለ “የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በነዋሪዎች ላይ ጥቃት አልፈጸመም” ሲሉ አስተባብለዋል።
በሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በቡድን አስተባባሪነት የሚሰሩት አቶ አብዲ መሀመድ እንዳሉት በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ላይ ጥቃት የተፈጸመው አርብ ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ነው። ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ በአፋር ክልል ባለሥልጣናት “ሀሩቃ” ተብሎ ቢጠራም ትክክለኛ ስያሜው ግን “ገረብኢሴ” የሚባል እንደሆነና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ስር ይተዳደር እንደነበር ያስረዳሉ። የሶማሌ ክልል በ“ሀሩቃ” ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ሰዓት በአፋር ክልል ስር የተጠቃለሉ ሌሎች ሁለት ቀበሌዎች ላይም “የይገባኛል ጥያቄ” እንዳለውም ያብራራሉ።
በገረብኢሴ አካባቢ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ካምፕ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ አብዶ፤ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል አባላት ጥቃቱን የሰነዘሩት በዚሁ ካምፕ ላይ ነው ባይ ናቸው። ጥቃቱ የተሰነዘረባቸው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ለጥቃቱ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ያጠፉት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል።
የሶማሊ ክልል ጸጥታ ቢሮ፤ በጥቃቱ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ የሚያጣሩ ሰዎች ወደ ቦታው መላኩን እና መረጃው ተጠናቅሮ እንዳለቀ ለብዙኃን መገናኛዎች እንደሚገለጽ ጠቁመዋል። በገዋኔ አካባቢ በጥይት ተመትተው ስለሞቱት የአፋር ክልል የመንግሥት ሠራተኞች የተጠየቁት አቶ አብዲ በአካባቢው በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ የሁለቱም ክልል ኃይሎች የተኩስ ልውውጥ ያደርጉ ስለነበር፤ ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው ለመግለጽ ያስቸግራል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “በራሪው ጥይት ከየትኛው አካል እንደመታቸው አይታወቅም” ሲሉም አክለዋል።