የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የመዲናይቱ ነዋሪዎች ሲናገሩ የተረጋጋ ህይወት ለመምራትና በሰላም ወጥተን በሰላም መግባት አጠራጣሪ እየሆነ ከመጣ ዋል አደር ብሏል ይላሉ።
ወጣት ተሾመ ፀጋዬ በአዲስ አበባ፤ ፒያሳ አካባቢ ነዋሪ ሲሆን ስለከተማዋ የፀጥታ ሁኔታ ሲናገር “እንደ አገር የገጠመን የደህንነት ስጋት እንዳለ ብናዉቅም ነገር ግን አሁን ላይ ከአቅም በላይ እየሆነ ነው” ይላል።
ለዚህ ማሳያ ይላል ተሾመ “የሰው ህይወት በወንጀል ምክንያት ይጠፋል፣ የአካል ጉዳት በግለሰብም ይሁን በቡድን ይፈፀማል እንዲሁም በየቀኑ በሚባል ደረጃ የተለያዩ የስርቆት ተግባራት በተለያዩ የትራንስፖርት መያዣ አካባቢዎች እና ሰዉ በተሰበሰበበት አካባቢ ተበራክቷል፤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ ከባድ ነው” ሲል ያነሳል።
“በዚህ ላይ የፀጥታ አካላት የሚያሳዩት ቸልተኝነት አለ” የሚለው ተሾመ “የፖሊስ ስራ በየቀኑ በተጠንቀቅ የሚኮንበት እንጂ በሳምንት ወይ በወር የሚደረግ ስራ ነው ብዬ አላምንም፤ እኔ ከተጎዳሁ በኋላ ሌላው ነገር ምን ፋይዳ አለዉ” ይላል።
በሜክሲኮ አካባቢ ያገኘነው ሌላኛው የመዲናይቱ ነዋሪ አወል አብዱራዛቅ ስለ አዲስ አበባ የፀጥታ እና የደህንነት ጉዳይ ሲያስረዳ “ችግሩ በከተማው ዉስጥ ያሉት የፖሊስ አባላት ስለ የአዲስ አበባ ማህበራዊ ዉስብስብነት እና የተደራጁ የወንጀለኛ ቡድኖች ባህሪ ያላቸው መረዳት ከፍ ያለ አለመሆን ነው” ብሎ እንደሚያምን ይናገራል። “ለዚህም ምክንያቱ አብዛኞቹ የፖሊስ አባላት ከተለያዩ የአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች መምጣታቸው” ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ያስቀምጣል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ግን በአወል አብዱራዛቅ ሃሳብ አይስማሙም። “የፖሊስነት ሙያ በፈቃደኝነት የሚገባበት እና በመስፈርትነት የተቀመጡትን የሚያሟላ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ መሳተፍ የሚችልበት ነው” የሚሉት ኮማንደር ፋሲካ “አሁን ያሉት የፖሊስ አባላት ለስራቸዉ ብቁ ናቸዉ” ሲሉ ይሞግታሉ።
በኅብረተሰቡ ዘንድ አመኔታ አለን ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ኮማንደር ፋሲካ ሲመልሱ “ኅብረተሰቡ በፖሊስ ላይ እምነት አለው” ካሉ በኋላ “ነገር ግን ወንጀል ፈፃሚዎች እና የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸዉ እንዲሁም መንግስትን የሚጠሉ አካላት ፖሊስን ሊጠሉና አናምነዉም ብለዉ ሊናገሩ ይችላሉ” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ለዚህ አባባላቸው እንደማያሳያ ያነሱት “ማኅበረሰቡ በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በሰላም ወጥቶ መግባቱን መናገሩንና በየጊዜዉ የተለያዩ ጥቆማዎችን እየሰጠ መሆኑን” ነው።
የልደታ አካባቢ ነዋሪዋና በቡና ንግድ ስራ ላይ የተሰማራችው ሰርካለም አበባዉ ግን በኮማንደሩ ሃሳብ አትስማማም። “በፖሊሶች ላይ ሙሉ እምነት እንዳይኖረኝ የሚደርግ ተግባር ከፖሊስ አባላት ተመልክቼ አውቃለሁ” የምትለው ሰርካለም “ለምሳሌ ሁሉም ባይሆኑ አንዳንድ የፖሊስ አባላት የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ከመሆናቸው ባሻገር የወንጀል ድርጊት ሲፈፀም አይተው እንዳላዩ የሚያልፉ ናቸው” ትላለች። “በከተማው በጊዜው የሚሰማው የወንጀል ዜና ራሱ እንዴት ሙሉ እምነት እንዲኖርህ ሊያደርግህ ይችላል?” ስትል ታክላለች።
በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፕረስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሲናገሩ “አሁን ከባድ ነው፤ ምንም የማይካደዉ ነገር በፌደራልም ሆነ በክልል ከተሞች በጣም አደገኛ፣ በጣም ውስብስብ እና ዘግናኝ የሆኑ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉና እየተባባሱ ናቸው” ይላሉ።
አቶ አወል “ወንጀል ፈፃሚዎቹ የመከላከያ ወታደራዊ ልብስ ሳይቀር እንደሚለብሱ፣ የፍትሕ ተቋማት እና የፀጥታ አካላትን መኪና እየተጠቀሙ ራሳቸዉን እንደ ሕጋዊ አካል አስመስለዉ የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ ወደ ሰዉ ቤት እንደሚገቡና ሰው ገድለው፣ ዕቃ ጭነው እንደሚሄዱ የታየበት ሁኔታ ብዙ ነው፤ ይህንን ሲደርጉ መጀመሪያ ወንጀል ስለሚፈጽሙበት አካል በቅርብ ሰዎች አማካኝነት ስለላ ያካሄዳሉ” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
የፀጥታ መዋቅሩ ወንጀልን መከላከል መሰረት ያደረገ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ አወል የወንጀል መከላከል ስራ ወቅቱን የጠበቀ እና ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባ፤ ከዚህም በላይ ከተቻለ የፀጥታ አካሉ ከወንጀል ፈፃሚዎች በላይ ሊፈራ እና ሊከበር እንደሚገባ አለበለዚያ ግን ቢያንስ ሊገዳደራቸዉ እንደሚገባ፤ አሁን ላይ ግን ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን እንደሚያምኑ ነግረውናል።
ላንቻ አካባቢ በስራ ላይ ያገኘነዉ በረዳት ሳጅን ማዕረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል ስሙን እንዳንጠቅስበት ከነገረን በኋላ “ሙያውን በ2005 ዓ.ም በጦላይ ለ7 ወራት በመሰልጠን እንደተቀላቀለ ነገር ግን ስገባ እንደነበረው አሁን ላይ ለስራው ምንም አይነት ፍቅርም ሆነ ደስተኛነት አይሰማኝም” ሲል ይገልፃል።
በመንግስትም ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ በቂ የሆነ ክብር እና ማበረታቻ የለንም የሚለው ረዳት ሳጅን በየግዜው ተለዋዋጭ ከሆነው የዓለም ብሎም የከተማዋ ሁኔታ አኳያ ተከታታይ ስልጠና እና ማበረታቻ ሊኖር እንደሚገባ ነገር ግን በ8 ዓመት የአገልግሎት ጊዜ ዉስጥ በ2009 ዓ.ም አንድ ግዜ ብቻ የአቅም ግንባታ እንደወሰደ ያስረዳል።
አዲስ ዘይቤ ካነጋገራቸው የፖሊስ አባላት መካከል ሌላኛዋ ሳጅን ብርቱካን ቢሰጥ በመኖሪያ አካባቢዋ ማንም ሰው ፖሊስ መሆኗን እንደማያውቅና የፖሊስ ደንብ ልብስ በመኖሪያ አካባቢዋ ለብሳ ታይታ እንደማታውቅ ትናገራለች። ይህ ለምን እንደሆነ የጠየቅናት ሳጅን ብርቱካን “በአንድ በኩል ጫና እንዳይደርስብኝ በሌላ በኩል ደግሞ በዕረፍት ቀኔ እንደማንኛው ሰው መሆን ስለምፈልግ ነው” ብላናለች። መታወቂያ እንዳልያዘች የነገረችን ሳጅን ብርቱካን መታወቂያ ማሳየት ሊያስፈልግሽ የሚችልበት የወንጀል ድርጊት ቢያጋጥምሽስ አልናት፤ “ያው ዩኒፎርሙ ስላለ ብዙም አያስፈልግም” ስትል መልሳልናለች።
ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ክፍተት እንዳለ አምነው ነገር ግን በቅርቡ መፍትሄ እንዲያገኝ በአጀንዳነት የተያዘ ጉዳይ ነው ብለውናል።
ስማቸዉን መናገር ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ ሕዝብ ጠዋት ለስራ ማታ ወደ ቤት ባዶ እጁን የሚንቀሳቀሰውና ግብር የሚከፍለው መንግስት ደህንነቴን ይጠብቅልኛል ብሎ ስለሚያስብ ነው ይላሉ። እንደ ሕግ ባለሙያው አስተያየት የወንጀል ድርጊት በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ኅብረተሰቡ ራሱን ወደ መጠበቅ ስለሚሸጋገር ሕግ እና ስርዓት መፍረሱ አይቀሬ ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን አካፍለውናል።
መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ በሰጠዉ መግለጫ በከተማዋ ዉስጥ በተደረገ የአንድ ሳምንት የተቀናጅ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽ በተደራጀ መንገድ አቅደው የዘረፋ እና የግድያ ወንጀሎችን የመሚፈፅሙ ተጠርጣሪዎችንና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ መያዙን ማስታወቁ አይዘነጋም። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የከባድ ወንጀል በ17 በመቶ ቀንሷል ብለውናል። ቃለ-መጠይቅ ላደረግንላቸው አዲስ አበቤዎች ግን የኮማንደሩ ሪፖርት አይዋጥላቸውም።