መጋቢት 23 ፣ 2013

አዲስ አበባ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ላይ የዘረፋ ሙከራ ተደረገ

ፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ በሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጣቢያ ላይ የዘረፋ ወንጀል ሙከራ ተደረገ።

አዲስ አበባ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ላይ የዘረፋ ሙከራ ተደረገ

ለየካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም አጥቢያ ከሌሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ውስጥ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ ሰለፊያ መስኪድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጣቢያ ላይ የዘረፋ ወንጀል ሙከራ መደረጉን አዲስ ዘይቤ ከጣቢያው ሰራተኛ ከሆኑ ግለሰብ አረጋግጧል።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 3፣ ቀጠና 7፣ ምርጫ ጣቢያ 15 ላይ ከሌሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ ጣቢያውን ሰብረው ለመግባት የሞከሩ “ሌቦች” ነበሩ ሲሉ የነገሩን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የምርጫ ጣቢያው ሰራተኛ፤ በአካባቢው ነዋሪ ጥረት የዘራፊዎቹ ሃሳብ ከግብ ሳይደርስ ቀርቷል ብለዋል።

ምንጫችን እንደነገሩን ከሆነ አሁን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የገባበት ይህ ቤት ከዚህ ቀደም የስፖርት ማዕከል የነበረ ሲሆን ዘረፋ ተፈፅሞበት ያውቃል። የስፖርት ማዕከል እያለ በተቃጣበት ስርቆት የተለያዩ የስፖርት መስሪያ ቁሳቁሶች መዘረፋቸውን አዲስ ዘይቤ ሰምቷል።

የምርጫ ጣቢያው ላይ ጥበቃ እንዲመደብ ጥያቄ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም “ቦታው መንደር ውስጥ ስለሆነ አስጊ አይደለም የፖሊሶች ቅኝት (ፓትሮል) በቂ ነው” የሚል ምላሽ ማግኘታቸው ስማቸውን እንዳንጠቅስ የፈለጉት ምንጫችን ነግረውናል።

ሌሊት ላይ ተፈፅሞ በነዋሪዎች ርብርብ ከሽፏል የተባለውን ይህንን የዘረፋ ሙከራ ለአካባቢው ፖሊስ እንዳስታወቁና ፖሊሶች ጉዳዩን ለመመልከት ዛሬ ወደ ስፍራው እንደሚመጡ እንደነገሯቸው ምንጫችን ገልጸዋል። ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 3፣ ቀጠና 7፣ ምርጫ ጣቢያ 15 ላይ በአሁኑ ሰዓት የመራጮች ምዝገባ መካሄዱን እንደቀጠለ አዲስ ዘይቤ ከስፍራው አረጋግጧል።

አሁን ላይ የመራጮች ምዝገባ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ይህ የምርጫ ጣቢያ የፊታችን ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ለሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሁሉም የጣቢያው የተለያዩ መረጃዎች የተቀመጡበት ቦታ ነው።

“በቋሚነት በየቦታው ካሉ የምርጫ ጣቢያዎች ጋር በየዕለቱ የሚያጋጥማቸው ችግር ካለ የምንነጋገርበትን ስርዓት ዘርግተናል” ሲሉ የነገሩን የቀጠናው አስተባባሪ ዋና ሳጅን ግዛቸው አዱኛ “ሌሊት ላይ ሊፈፀም ነበር የተባለውን የዘረፋ ድርጊት በተመለከተ ግን ቦታው ላይ ሄደን ካጣራን በኋላ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን፤ የደረስንበትንም እናሳውቃችኋለን” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተያየት ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

አስተያየት