መጋቢት 23 ፣ 2013

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድታሳድር ሱዳን ጠየቀች

ወቅታዊ ጉዳዮች

የሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሆነ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከመከናወኑ በፊት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ አንዳች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካ በጉዳዩ ጣልቃ እንድትገባ ጥያቄ ቀርቧል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድታሳድር ሱዳን ጠየቀች

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከመከናወኑን በፊት ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር አንዳች ስምምነት ላይ ሳትደርስ የውሃ ሙሌት ማከናወን ስለሌለባት በግድቡ ጉዳይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር አለባት ስትል ሱዳን ለአሜሪካ ጥያቄ ማቅረቧ ተሰምቷል።

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል-ማህዲ በዶናልድ ቡዝ ከተመራው የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጋር በሕዳሴ ግድብ እና በሁለቱ አገራት ግንኙነት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

የሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳስታወቀው ከሆነ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከመከናወኑ በፊት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ አንዳች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካ በጉዳዩ ጣልቃ እንድትገባ ጥያቄ ቀርቧል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት በራሷ ማከናወኗ በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ያሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ይህ የኢትዮጵያ አካሄድ ሱዳን ቀድሞ የነበራትን አቋም እንድትቀይር ሳያደርጋት እንዳልቀረ አመላክተዋል ተብሏል።

የግብጹ ፕሬዝደንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ የስዊዝ ቦይ መከፈትን በተመለከተ በስፍራው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ባሰሙት ንግግር አገራቸው በሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ሳቢያ ከናይል ወንዝ ማግኘት የሚገባትን የውሃ መብት ልታጣው አትፈቅድም ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው ማንም ከግብጽ አንድ ጠብታ ውሃ ሊወስድ አይችልም፤ ማንም ይህንን መሞከር ከፈለገ ያድርገው፤ ይህ ግን አካባቢውን ያናጋል ማለታቸው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዶናልድ ቡዝ ከተመራው የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጋር አድርገውት በነበረው ውይይት ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት እየተካሄደ የሚገኘውን የሶስትዮች ድርድር ዋጋ እንደምትሰጠው መናገራቸው ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ በሚቀጥለው የክረምት ወቅት 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መሙላቷን እንደማታቆም በተደጋጋሚ ተናግራለች። እንስካሁን ድረስም ከዚህ አቋሟ ሸብረክ አላላችም።

ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ ያደራድሩን ስትል ይፋዊ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው ሁሉ ጽፋ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ይህንን የሱዳንና ግብጽ ሃሳብ ሳትቀበለው ቀርታለች።   

አስተያየት