የቀድሞው የመቀሌ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታክልቲ ኃይለሥላሴ “ከኃላፊነቴ በገዛ ፈቃዴ እራሴን አነሳሁ እንጂ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ግምገማ ተደርጎ አይደለም የተነሳሁት” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
“የክልሉ አስተዳደር ለምን ከመቀሌ ወጥቶ ለሌላው የትግራይ ክልል ማኅበረሰብ አገልግሎት እና መሰረተ ልማት እንዲሟለለት እንደማያደርግ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር እሞግት” ነበር ሲሉ የነገሩን የቀድሞው የመቀሌ ከተማ ከንቲባ “የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) እንደነገሯችሁ በግምገማ ሳይሆን የተነሳሁት እየሆነ ያለው ነገር ስላልተስማማኝ በገዛ ፈቃዴ ነው ከኃላፊነቴ የለቀኩት” ሲሉ ነግረውናል።
“በተደጋጋሚ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) እና የክልሉ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ጀነራል ዮሐንስ ገብረመስቀል የሚሰሯቸውን ሕጋዊ ያልሆኑ ስራዎች እታገል ነበር” ሲሉ የነገሩን አቶ አታክልቲ “በተለይ ዋና ሥራ አስፈፃሚው በክልሉ በሚገኙ ኬላዎች ላይ ለስጋ ቤት ነጋዴዎች ኃላፊነት ሰጥቷቸው ኅብረተሰቡን እየበዘበዙ መሆኑን ተቃውሜያለሁ” ብለዋል።
“ለምሳሌ አቶ ፋሲል በርኽ የሚባል ሰው ሌቦች ከትግራይ የተለያዩ ማሽኖችን እንዲያወጡ ለማድረግ ከእያንዳንዱ ሰው 60 ሺህ ብር እየተቀበሉ እንደነበረና ግለሰቡ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሎ ሲጠየቅ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ነው የፈቀደልኝ፤ የሚሰበሰበውን ብር አብረን ነው የምንጠቀምበት” ብለው ስለመናገራቸው አቶ አታክልቲ ነግረውናል።
“የመሬት እና መዘጋጃ ቤት አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም ያሉት አቶ አታክልቲ ጀነራል ዮሐንስ ገብረመስቀል ያለሥልጣናቸው ለባለሃብቶች መሬት በመስጠት ግንባታ እንዲካሄድ እየፈቀዱ ነው፤ እርሳቸው የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊ እንጂ መሬት የመስጠት እና የመከልከል ሥልጣን የላቸውም” ብለን ታግለናል ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻ ስልጣን ለመልቀቅ ምክንያት የሆናቸውን ዋነኛ ጉዳይ የጠየቅናቸው አቶ አታክልቲ ሲመልሱ “የመቀሌ ከተማ የትራንስፖርትና ኮንስትራክሽን ኃላፊ አቶ ከበደ አሰፋ ጀነራል ዮሐንስ የሚያደርጉትን ትክክል ያልሆነ ስራ በመቃወማቸው ምክንያት ጀነራሉ ቂም ይዘው በኮማንድ ፖስቱ ስብሰባ ወቅት ከዚህ በኋላ አቶ ከበደ ተባረዋል ሲሉ ተናገሩ፤ እኔ ይህንን በመቃወው እርሳቸው የተሾሙ በእኔ ነው፤ የካቢኔ አባል ናቸው፤ መቀየር አልያም ባጠፉት ነገር መጠየቅ ካለባቸውም አብረን ገምግመን መሆን አለበት ማለቴን ተከትሎ ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፈላጭ ቆራጭ ምልክቶችን ስላሳዩኝና ስለዛቱብኝ በዚህ ሁኔታ ላለመቀጠል ከሥልጣኔ በገዛ ፈቃዴ ለቅቄያለሁኝ” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
“ስለሥራ አፈፃፀም የተደረገ ግምገማ የለም ያሉት የቀድሞው የመቀሌ ከተማ ከንቲባ፤ የካቢኔ አባላትን በሙሉ መጠየቅ ይቻላል” ብለዋል። “የስራ አፈፃፀሜ ቢገመገም እንኳን ከመቀሌ ውጪ የትም ስላልተሰራ፤ መሸለም እንጂ ሌላ ነገር የሚገባኝ ሰው አይደለሁም በማለት ገልፀዋል።
“ሃድነት በሚባል ክፍለ-ከተማ ባሳለፍነው እሁድ ጠዋት ሕዝብ አናግረን ከጨረስን በኋላ ቁርስ ለመመገብ ወደ አንድ ሬስቶራንት ውስጥ ገብቼ ስወጣ በነበርኩበት መኪና ላይ የቦንብ ፍንዳታ ተከስቶ ነበር” ሲሉ የነገሩን አቶ አታክልቲ “እኔ ላይ ጉዳት ባይደርስም በአካባቢው በነበረ የሆቴሉ የጥበቃ ሰራተኛ ላይ እና በመኪኖች ላይ ጉዳት አጋጥሟል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ትግራይ ውስጥ ያለው ለውጥ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው” ያሉት አቶ አታክልቲ “ይህ ለውጥ እንዲቀጥል ካስፈለገ በትክክል ለውጡን ማስቀጠል የሚችሉ ሰዎች መምራት አለባቸው እንጂ ትላንትና የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የነበሩ ሰዎች አሁን ላይ ኮፍያቸውን ቀይረው ሊመጡ አይገባም” ብለዋል።
“እኔ ወጣትና የተማርኩኝ ነኝ የትም ቦታ መስራት እችላለሁ፤ ለምን ለቀኩኝ የሚል ሃሳብ የለኝም” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት ከሆነ “የመቀሌ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታክልቲ ኃይለሥላሴ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በገዛ ፍቃዳቸው ሳይሆን በሥራ ግምገማ ነው።”