መጋቢት 22 ፣ 2013

“የመቀሌ ጊዜያዊ ከንቲባ ከስራቸው እንዲነሱ የተደረገው በስራ ግምገማ ነው” - ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)

ወቅታዊ ጉዳዮች

“የመቀሌ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታክልቲ ኃይለሥላሴ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በገዛ ፍቃዳቸው ሳይሆን በሥራ ግምገማ ነው።” - የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)

“የመቀሌ ጊዜያዊ ከንቲባ ከስራቸው እንዲነሱ የተደረገው በስራ ግምገማ ነው” - ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት ከሆነ “የመቀሌ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታክልቲ ኃይለሥላሴ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በገዛ ፍቃዳቸው ሳይሆን በሥራ ግምገማ ነው።” 

“የቀድሞው የመቀሌ ከንቲባ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው እርሳቸው እንደሚሉት በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን ለመልቀቅ ማመልከቻ አስገብተው ሳይሆን ግዜያዊ አስተዳደሩ ባካሄደው የ100 ቀናት የሥራ ግምገማ ውጤታማ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው” ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

“በመቀሌ ለሕዝቡ መድረስ የሚገባው ዕርዳታ እየተሰረቀ ነው፣ በትክክል እየተከፋፈለ አይደለም ከዚህ በተጨማሪ ትምህርት አልተጀመረም ይህ የአስተዳደሩ ክፈተት ስለሆነ ሥራን ማዕከል ያደረገ ግምገማ ተካሄዶ ገና እስከ ክፍለ ከተማ ባለው መዋቅር ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

“እርምጃው በአቶ አታክልቲ የተጀመረ አይደለም” ያሉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ “ከዚህ ቀደም የየክልሉን የግንባታ ቢሮ ኃላፊ ጨምሮ የሁለት ዞን አስተዳዳሪዎችንና የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ኃላፊ ከሥልጣናቸው እንደተነሱ” አስታውሰዋል።

“ለሕዝቡ ሲባል በትክክል መምራት የተሳነውንና ክፍተት ያለበትን አመራር እንዲስተካከል ማድረግ ተገቢ እንደሆነና የሥራ አፈፃፀም የሚለካው በምናደርገው ከፖለቲካ ነፃ በሆነ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ብቻ ነው” ሲሉ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ነግረውናል።

“ግምገማ እየተካሄደ ነው፤ ከሥልጣናቸው የሚነሱ ሰዎች ይኖራሉ” ያሉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ “አቶ አታክልቲ በገዛ ፈቃዴ ስልጣን ለቀኩኝ ያሉት ግን ሐሰት ነው ብለዋል።”

የቀድሞው የመቀሌ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ኃይለሥላሴ በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ምን እንደሆነ ለማወቅ ተደጋጋሚ ሙከራ እያደረግን ሲሆን እንዳገኘናቸው ምላሻቸውን ይዘን እንመለሳለን።

አስተያየት