መጋቢት 29 ፣ 2013

በመደበኛ ስያሜዎቿ የማትጠቀም ከተማ

City: Adamaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

አዳማ ከተማ ክፍለ ከተማዎች እና ቀበሌዎች የስያሜ ለውጥ የተደረገ ቢሆንም በነዋሪው ዘንድ ጥቅም ላይ አልዋለም።

በመደበኛ ስያሜዎቿ የማትጠቀም ከተማ

በአዳማ ከተማ ጉዳይ ገጥሞዎት “ቢቃ ቀበሌ በየት ነው?” ብለው ቢጠይቁ “አላውቀውም” የሚል ምላሽ የማግኘት ዕድልዎ የሰፋ ነው፡፡ በቀን ወደ 60 ሺሕ የሚገመቱ ሰዎች ገብተው የሚወጡባት ከተማ በመሆኗ ምናልባት እንግዳ ስለሚበዛ ምላሹ ላያስገርም ይችላል፡፡ 20 ሺህ ያህሉ ለመዝናናት 40 ሺህ ያህሉ ስብሰባን ጨምሮ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ጧት ገብተው ማታ ይመለሳሉ፡፡ 

ከመንገደኛ ይልቅ አገልግሎት ሰጪዎች ቦታዎችን የማወቅ እድል እንዳላቸው በመገመት ወደ ሚኒባስ ታክሲዎችንም ሊያማክሩ ይችላሉ፡፡ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ)፣ በፈረስ የሚጎተቱ ጋሪዎችን ጨምሮ ሚኒባስ ታክሲዎች የአዳማ ከተማ የትራንስፖርት አማራጮች ናቸው፡፡

ብዙዎቹ የታክሲ እና ባጃጅ ሹፌሮች “የድሮ ስሙ ምንድነው? ቀበሌ ስንት ነው?” ብለው አቅጣጫ ለመጠቆም ይሞክራሉ፡፡ ይህ የቀድሞ ስሙን ለማያውቅ እንግዳ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ የአዳማ ከተማ መደበኛ ስያሜዎች የተለያዩ ቀበሌዎች እና ስፍራዎች መጠሪያዎች ነዋሪው በተለምዶ ከሚሰጣቸው ስያሜዎች ጋር ለየቅል ናቸው፡፡ 

ናዝሬት - አዳማ  

ከ105 ዓመታት በፊት የተቆረቆረችው፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምስራቅ ሸዋ ዞን ሥር የምትገኘው፣ ከሐገሪቱ መዲና በአንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለችው በቀድሞ ስሟ ናዝሬት አሁን አዳማ ከሰሜን ምስራቅ ወደ ደቡብ ምዕራብ የሚነፍስ ሞቃታማ አየር አላት፡፡ አዳማ ማዘጋጃ ቤት እና የከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የገጠር ቀበሌዎችም አሏት፡፡ የምዕራብ፣ የሰሜን ምዕራብ፣ የሰሜን እና ደቡብ ዳርቻዎቿ ተዳፋትነት ያላቸው ናቸው፡፡ ለእድገቷ ማነቆ ሆነዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይህ ተዳፋታማ ተፈጥሮዋ ነው፡፡ ከተማዋ በአካባቢዋ ካሉ ከተሞች ጋር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ትስስር አላት፡፡ ኢንዱስትሪ ፖርኮችን ጨምሮ ሌሎችም ፋብሪካዎች በአዳማ ይገኛሉ፡፡

ከቀበሌ ወደ ባህላዊ ስያሜ 

ከተማዋ ከተቆረቆረችበት ጊዜ አንስቶ ቀበሌ 01፣ ቀበሌ 02 የሚባሉ 14 ቀበሌዎች ነበሯት፡፡ በ2008 ዓ.ም. 100ኛ ዓመቷን ካከበረች በኋላ ግን ይህ የቁጥር መጠሪያ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ኩነቶችን በሚያስታውሱ ስያሜዎች ተለወጠ፡፡ የስያሜ ለውጡ የኦሮሞ ቋንቋ፣ ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ እንዳለው፣ ከቅድመ ምስረታዋ ጀምሮ ያሉ የአካባቢ መጠሪያዎች በመካተታቸው ስያሜዎቹ ማኅበረሰቡን እንዲወክሉ እንደሚያደርግ የአዳማ ከተማ ባህል እና ቱሪዘም ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

የከተማዋ መስተዳድር እና የአዳማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የታሪክ ጥናት ባለሙያ ጋብዞ፤ ለረዥም ዓመታት በአካባቢው የኖሩ የሐገር ሽማግሌዎችን፣ ባለድርሻ አካላትን ያካተተው ጥናት 2010 ዓ.ም. ላይ ተግባራዊ ተደረገ፡፡ በወቅቱ በአዳማ ምክርቤት ጸድቀው ሥራ ላይ የዋሉት ስድስት ክፍለ ከተሞች እና 14 ቀበሌዎች ናቸው፡፡ ክፍለ ከተሞቹ አባ ገዳ፣ ቦኩ፣ ዳቤ፣ ቦሌ፣ ሉጎ፣ ደንበላ ይባላሉ፡፡ እያንዳንዳቸው ክፍለ ከተሞች በውስጣቸው ከሁለት እስከ አራት ቀበሌዎችን ይይዛሉ፡፡ የአስራ አራቱ ቀበሌዎች የቁጥር መጠሪያ ታሪካዊ እና ባህላዊ ሁነቶችን ወደሚያስታውስ ስያሜ ተለውጧል፡፡ በስድስቱ ክፍለ ከተሞች ስር የሚገኙት 14 ቀበሌዎች ጎሮ፣ ሚገራ፣ ጋራ ሉጎ፣ ደደቻ አራራ፣ ደጋጋ፣ ጉርሙ፣ በዳቱ፣ ኦዳ፣ ኢሬቻ፣ ቢቃ፣ በሬቻ፣ ገዳ፣ ጨፌ፣ ሃንጋቱ ቀበሌ ይባላሉ፡፡

ለምን ጥቅም ላይ አልዋሉም? 

ስሙን መግለፅ ያልፈለገ በከተማዋ አንድ ቀበሌ የሚያገለግል ወጣት በ“ሰፊ ጥናት” ወጡ የተባሉት ስሞች ቀበሌዎቹን ፈልጎ ማግኘትን  አስቸጋሪ ያደረጉት የህዝብ ተሳትፎ ባለመኖሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “እኔ የሚመስለኝ ሕዝቡ አለመወያየቱ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ጥናት ተደርጓል ቢባልም በፖለቲካ ኃይሎች አስተባባሪነት፣ በጥቂት የከተማዋ ሰዎች ተሳትፎ የተደረገ ነው” 

ፈተናው ለነዋሪው ብቻ ሳይሆን በአስተዳደሩ ውስጥ ለሚያገለግሉ ኃላፊዎችም አልቀረም፡፡ “እንኳን ተራው ነዋሪ እኛም ቀበሌና ክፍለ ከተማ እየሰራን መልመድ ከብዶናል” ሲል ወጣቱ ሀሳቡን ያጠናክራል፡፡

አንዳንድ የሰፈሩ ነዋሪዎች ሳይቀሩ በአካባቢያቸው የሚገኘውን ቀበሌ በቀድሞ ስሙ ማለትም በቁጥር ካልሆነ በአዲሱ ስያሜው አያውቁትም፡፡ የዚህም ምክንያት የምታብራራው ሌላዋ ወጣት ደግሞ እንዲህ ትላለች፡፡  

“የሆነ ቀን ተቀይሯል አሉን እንጂ ብዙም አላስተዋወቁትም፡፡ ብዙ የሚያውቀው ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ የመንግሥት ቢሮዎች ላይ፣ መታወቂያ ላይ፣.. ካልሆነ እየተጠቀምንበት አይደለም”

የመንግሥት ተቋማት እና የአካባቢው ነዋሪ በተመሳሳይ ስያሜ ያለመጠቀሙ ሰበብ ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ሁለት ምላሾች ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው ስያሜው ሲለወጥ በበቂ መጠን ውይይት አለመደረጉ ነው፡፡ ቅየራው ላይ ጥያቄ ያላቸው፣ መለወጡን የሚደግፉ፣ የነበረው እንዲቀጥል የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ይህንን የሚያስታርቅና ወደ አንድ ሐሳብ የሚያመጣ ሥራ ቀድሞ አልተሰራም፡፡ 

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በበቂ መጠን እንዲተዋወቅ አለመደረጉ ነው፡፡ ነዋሪው የእኔ ብሎ ሊገለገልበት እንዲችል በሚያደርግ መልክ አላወቀውም፡፡ እዚህ ላይ የተሰራው ሥራ ዝቅተኛ ነው፡፡ የእነዚህ ሰበቦች ድምር ደግሞ ለአካባቢው አዲስ የሆነን ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ነዋሪውንም የሚያደናግር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ 

 

አስተያየት