በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል ከተለያዩ አገራት በስጦታ የመጡትን ክትባቶች ዜጎች እንዲወስዱ እየተደረገ ነው። ይህንን ተከትሎ ክትባት የወሰዱ የጤና ባለሙያዎች ክትባቶቹን ከወሰዱ በኋላ በጤናቸው ላይ ምን አጋጠማቸው፤ የጤና ሚኒስቴርስ ምን ይላል ስንል የሚመለከታቸውን አነጋግረናል።
“የኮሮና ክትባት በፈቃደኝነት ወስጃለሁ” የሚሉት በጎተራ ማሳለጫ ጤና ጣቢያ የጤና መኮንን የሆኑት አቶ ቢኒያም ወልዴ “ክትባቱን ከወሰድኩ በኋላ የድካም ስሜት እና የመገጣጠሚያ ክፍል ህመም አጋጥሞኛል” ይላሉ። ከእርሳቸው ጋር ክትባቱን የወሰደ ሌላ የጤና ባለሙያ አሁን ላይ ከፍተኛ ህመም አጋጥሞት ሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገለት እንደሆነ የነገሩን አቶ ቢኒያም በዚህም ግራ እንደተጋቡ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አቶ ተክሌ ደነቀ በወይራ ቤተል ጤና ጣቢያ የፋርማሲ ባለሙያ ሲሆን የኮሮና ክትባት የወሰደ ቢሆንም ከመጠነኛ የድካም ስሜት የዘለለ ህመም እንዳልተሰማዉ ከነገረን በኋላ የትኛዉም መድኃኒት መጠኑ ይለያይ እንጂ የጎንዮሽ ጎዳት ይኖረዋል፤ ነገር ግን የጎንዮሽ ጉዳቱን ስለማናስተውለው ጉዳት ያለው አይመስለንም ሲል ነግሮናል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር የሆኑት መሰረት ዘላለም (ዶ/ር) ስለጉዳዩ ሲያብራሩ የኮሮና ክትባት በዓለም ጤና ድርጅት ዕውቅና የተሰጠው ቢሆንም የበሽታውን ጉዳት ለመቀነስ ሲባል የአስቸኳይ ክትባት ተብሎ በልዩ ሁኔታ እንደወጣ በዚህም ክትባቱ ያለቀለትና የመጫረሻው እንዳልሆነ ነገር ግን ለጊዜው ያለን አማራጭ ይህ በመሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገራት በተመሳሳይ እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል።
ክትባቱን የሚወስዱ ሰዎች ላይ እንደማንኛዉ አይነት ክትባት የተወሰኑ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደሚስተዋል፤ ከነዚህም ዉስጥ የክትባቱ መርፌ የተወጋበት ቦታ ላይ የህመም ስሜት፣ የራስ ምታት ስሜት፣ ትኩሳት፣ የሰውነት የመገጣጠሚያ ክፍል ላይ የህመም ስሜት፣ የድካም እንዲሁም የማቅለሽለሽ ስሜት እንደሚኖረው ነገር ግን ይህ ጊዜያዊ በመሆኑ የከፋ ጉዳት አያመጣም ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አብራርተዋል።
መረጃ ለመያዝና የተጠቀሱት ምልክቶች ከታዩ በኋላ ሌላ የከፋ ህመም ቢያጋጥም ህክምና ለማግኘት እንዲረዳ ክትባቱን ወስዶ እነዚህ ምልክቶች የታዩበት ሰው ክትባቱን ለወሰደበት ተቋም ሪፖርት ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይናገራሉ።
እየተሰጠ ያለው የአስትራዜኒካ ክትባት የኮሮና በሽታን ፊት ለፊት እየተጋፈጡ ላሉ በግል፣ በመንግስት እንዲሁም በአረጋዊያን መጦሪያ ዉስጥ ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ የአስተዳደር ባለሙያዎች እንዲሁም እድሜያቸው ለገፋና ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ሰዎች እንደሆነ ዳይሬክተሯ ነግረውናል።
ተጓዳኝ የጤና ችግር የሚያካትተው የትኞቹን የበሽታ አይነቶች ነው? ብርድ እና ጉንፋን የመሳሰሉትን ያካትታል ወይ ሲል አዲስ ዘይቤ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዳይሬክተሯ ጉንፋን እና ብርድ ተጓዳኝ የጤና ችግር ዉስጥ እንደማካተቱ በመግለፅ ተጓዳኝ የጤና ችግር የሚባለው ለምሳሌ የልብ ችግር፣ የደም ግፊት፣ የስኳር ህመም፣ ከሳንባ ጋር ተያይዞ የመተንፈሻ አካል እክል፣ የደም ዝውውር ችግር ያለባቸው፣ የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽተኞች እንዲሁም የኩላሊት፣ የጉበት እና የካንሰር ህመም ያለባቸው ሰዎች እንደሆኑ ተናግረዋል። ክትባቱን የሚወስዱ ሰዎች በቅድሚያ የሙቀት ልኬት እንደሚደረግላቸውና እና የኮሮና ምልክት ከታየ አልያም ኮሮና እንዳለበት በምርመራ የተረጋገጠበት ሰው ክትባት እንደማይሰጠው ዳይሬክተሯ ለአዲስ ዘይቤ አስታውቀዋል።
በጎተራ ማሳለጫ ጤና ጣቢያ ህክምና ፈላጊዎችን ስታስተናግድ ያገኘናት የጤና ባለሙያ ሲስተር ማህሌት ካሳሁን የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንዳልወሰደች ከነገረችን በኋላ ክትባቱ እየተሰጠ ያለው ቅድመ ምርመራ ሳይደረግ በመሆኑ ይህ ምን አልባት ኮሮና በውስጤ ካለ ክትባቱ ሲጨመርበት ለከፍተኛ ህመም ሊዳርገኝ ይችላል በሚል ፍራቻ ምክንያት እንዳልተከተበች ነግራናለች።
የአስትራዜኒካ የኮሮና ክትባት ከመጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ነበር ለበሽታው ቀጥተኛ ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያች መሰጠት የተጀመረው።