ሰኔ 11 ፣ 2014

በዳውሮ ዞን የትምህርት መቋረጥ

City: Hawassaትምህርትወቅታዊ ጉዳዮች

የመምህራን ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ ትምህርታቸዉን መቋረጡን ተማሪዎች ገለጹ

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በዳውሮ ዞን የትምህርት መቋረጥ
Camera Icon

ፎቶ ቢኒያም ጳዉሎስ

በዳዉሮ ዞን በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ዉስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንዳልሆነ ተሰምቷል። የዳዉሮ ዞን በአስር ወረዳዎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር የተዋቀረ ሲሆን ከእነዚህ ዉስጥ የገሣ፣ የማረቃ ፣ ቶጫ፣ የከጪ፣ እና በዲሣ ወረዳዎች ይገኛሉ ። በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ የሚገኙ መምህራን ወርሃዊ ደሞዝ በሰዓቱ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ የመማር ማስተማር ስራው ተስተጓጉሏል። 

የገሣ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተመስገን ኡቴ እንደሚሉት በወቅቱ ለመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ያለመከፈሉ ምክንያት ዞኑ ያለበት “ዉዝፍ እዳ’’ ነው ። ይህ ዉዝፍ እዳ የመጣው የዳዉሮ ዞን ከዚህ ቀደም በደቡብ ክልል ስር በነበረበት ወቅት ለግብርና ስራዎች፣ ለሌሎች የተለያዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እና ጉዳዮች ወጪ እንዲሆን ተተምኖ ከተሰጠው ገንዘብ በተጨማሪ ለስራ ማስኬጃ ከክልሉ ከተበደረው ነው። ነገር ግን በአዲስ አደረጃጀት ከሌሎች ዞኖች ጋር አዲስ ክልል መሆን የቻለዉ የዳዉሮ ዞን ከዚህ ቀደም መከፈል የነበረበት "እዳ" ባለመከፈሉ አሁን ላይ ትልቅ ራስ ምታት እንደሆነበት ተነግሯል። 

ይህን በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ችግር እያመጣ እና በተለይ ደግሞ በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ የሚገኘውን ዉዝፍ እዳ ለመክፈል ከመንግሥት ሰራተኛ ወርሃዊ ደመወዝ ላይ ተቀናሽ ወይም ተቆራጭ በማድረግ ክፍያዉ እንዲፈፀም እየተደረገ ሲሆን ከዛ ከፍ ሲል ደግሞ ሌሎች እዳዉ የሚከፈልበት አማራጮች የማፈላለግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ከአቶ ተመስገን ሰምተናል። 

ስማቸዉ እንዲጠቀስ ፍቃደኛ ያልሆኑ የማረቃ ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆኑት መምህር፣ ከአስር ዓመት በላይ እንዳስተማሩ አንስተው “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በክፍያ ምክንያት ማስተማር እየቻልን እንዳናስተምር ሆነናል’’ በማለት ያስረዳሉ። መምህሩ ጨምረዉም “ወርሃዊ ደመወዛችን ወቅቱን ጠብቆ ያለመከፈሉ በስራችን ላይ ጫና እየፈጠረ ነው ፤ ጉዳዩን በተመለከተ ወደ ወረዳ እና ዞን ጥያቄ ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም’’ ሲሉ ነግረዉናል ።

የገሣ ዳልባ ወረዳ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪ የሆነዉ እና በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ሃገራዊ ፈተናውን ለመፈተን በዝግጅት ላይ የሚገኘዉ ቢኒያም ጳዉሎስ “በዚህ አንድ አመት ዉስጥ በትክክል ተማርን የምለዉ ሶስት እና አራት ወራት ብቻ ነዉ ፤ ምክንያቱም መምህራን ደመወዝ ካልተከፈለን አናስተምረም ስለሚሉ እኛም ቤታችን እንድንቀመጥ ተገደናል’’ በማለት ይናገራል ። 

“ዘንድሮ ተፈታኝ ሆነን ነገር ግን በቂ የትምህርት ጊዜ ባለማግኘታችን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እንዴት ተወዳዳሪ ሆነን ማለፍ እንችላለን የሚለዉ ሁሌም ያስጨንቀኛል’’ ያለው ተማሪ ቢኒያም ቤተሰቦቻቸውን በማስቸገር እና ከዩኒቨርስቲ ለመጡ ተማሪዎች ክፍያ በመፈፀም ማጠናከሪያ ትምህርት ለማግኘት እየሞከሩ እንደሚገኙ ገልጿል። 

ከዛሬ 3 እና 4 ዓመት ወዲህ በመንግሥት ሰራተኞች ላይ እየተስተዋለ የመጣዉ የደመወዝ እና የጥቅማጥቅም ክፍያ በወቅቱ አለመከፈል በአሁኑ ሰዓት በሰፊዉ ችግር እንደሆነ ለማወቅ ችለናል ። 

የገሣ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተመስገን ኡቴ ለአዲስ ዘይቤ እንዳስረዱት ለመምህራን ፣ ለፍርድ ቤት ሰራተኞች ፣ ለፖሊሶች ፣ ለጤና ተቋም ባለሞያዎች ከሌሎች የመንግስት ሰራተኞች በቅድሚያ ክፍያ እንዲፈፀም እየተደረገ መሆኑን ተናግረው “ነገር ግን አልፎ አልፎ በወቅቱ የደመወዝ ክፍያ ያለመከፈሉ በወረዳው ብቻ ሳይሆን በዞን ደረጃ አሁንም ድረስ ያለ ነዉ’’ ይላሉ። 

የማረቃ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ተኛ ክልፍ ተማሪ የሆነዉ ብሩክ በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ያለው ይህ የክፍያ ችግር እና ያስከተለው የትምህርት አሰጣጥ እክል “በስነ-ልቦናችን ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሯል’’ በማለት ያስረዳል ። 

መምህራን በስራ ገበታቸዉ ላይ ባለመገኘታቸዉ የተጎዳዉ ተማሪ ነዉ የሚለዉ ብሩክ እሱም እንደ ተማሪ ቢኒያም ከሚማሩባቸው ጊዜያት ይልቅ ቤታቸው ተቀምጠው የሚያሳልፏቸው ወራት እንደሚበልጡ ተናግሯል። በተጨማሪም ደመወዝ ሲከፈላቸዉ ብቻ ለማስተማር የሚመጡት መምህራን “ከሌሎች ትምህርት ቤቶች እኩል መሆን አለብን በማለት በአንድ ክፍለ ጊዜ ሶስት እና አራት ምዕራፎችን እንድንጨረስ ያደርጋሉ’’ ሲል ተናግሯል።

በዚሁ የማረቃ ከተማ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት እና ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ መምህር ለአዲስ ዘይቤ እንደሚሉት ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ዉጪ የግል የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎች እየተማሩ መሆናቸዉን አንስተዋል ። “እኛ ወቅቱን ጠብቆ ደመወዝ ስለማይከፈለን ችግር ላይ ወድቀናል ፤ ለምሳሌ እኔ አምስት ቤተሰብ አለኝ የማስተዳድራቸዉ ከማገኘዉ ደመወዝ ነዉ እሱ ደግሞ ካልተከፈለኝ ምን አበላቸዋለሁ?’’ ሲሉ የጠየቁት መምህር ችግሩ ተደጋጋሚ ሆኖ መፍትሔ የሚሰጣቸው አካል ግን ባለመኖሩ ተስፋ መቁረጣቸውን ጨምረው ገልጸዋል። 

ይህ ዉዝፍ እዳ በመሰረቱ በዳዉሮ ዞን ብቻ ሳይሆን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚል አዲስ ክልል የመሰረቱት የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር በነበሩበት ወቅት በተመሳሳይ የእዳዉ ተካፋይ መሆናቸዉ ተነግሯል ፤ ምንም እንኳን የብድር መጠንኑ የዳዉሮ ዞን ከፍተኛ ቢሆንም።

አቶ ተመስገን እንዳሉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ በመሆኑ የነበረበት እዳ ለቀድሞ ክልሉ እንዲከፈል የተለያዩ የገቢ ምንጮች እየተፈለጉ ሲሆን ነገር ግን አሁንም ችግሩ ባለመፈታቱ ጉዳዩ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ መሄዱን አስታዉሰዋል ። 

ለአቶ ተመስገን ከአዲስ ዘይቤ የዉዝፍ እዳዉ ምን ያህል እንደሆነ እና መቼ ተከፍሎ ሊያልቅ እንደሚችል ለተነሳላቸዉ ጥያቄ ሲመልሱ የብር መጠኑን በትክክል እንደማያዉቁ ጠቁመዉ መቼ ክፍያዉ ሊጠናቀቅ እንደሚችልም ለመመለስ ያዳግታል ብለዉናል።

ጉዳዩን በሚመለከት የዳዉሮን ዞን አስተዳዳሪ አዲስ ዘይቤ ለማናገር ያደረገችዉ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ።

አስተያየት