ሰኔ 11 ፣ 2014

ደሴ ከተማና ዙሪያውን አሽከርካሪዎችን ያማረረው ህገወጥ የኬላ ላይ ቀረጥ ክፍያ

City: Dessieወቅታዊ ጉዳዮችንግድ

አሽከርካሪዎች በህገወጥ ቀረጡ በመማረር ስራ እያቆሙ ይገኛሉ

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ደሴ ከተማና ዙሪያውን አሽከርካሪዎችን ያማረረው ህገወጥ የኬላ ላይ ቀረጥ ክፍያ
Camera Icon

ፎቶ: BBC

መንግስት የሚገባውን ገቢ ለማግኘት የተሻለ ነው የሚለውን የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ ወደ ስራ ቢገባም መሬት ላይ ያለው ተግባር ግን በዚያው ልክ እየተፈፀመ አይደለም ሲሉ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው አሸከርካሪዎች ቅሬታ ያቀርባሉ።

ዋናው የቅሬታቸው ምንጭ ደግሞ የፍተሻ ጣቢያ ላይ ያለው የቀረጥ አሰባሰብ ነው። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚናገሩት ከሆነ ህጋዊነቱ ጀምሮ በርካታ ችግሮች የሚታዩበት የቀረጥ ሂደት እጅግ አማራሪ ሆኗል ይላሉ። ለአብነት ያህል በአንድ ከተማ ላይ ሁለት ጊዜ ቀረጥ እንጠየቃለን ብለዋል።

አቶ ዳዊት ገብረሃና የጭነት መኪና አሽከርካሪ ሲሆኑ ከአርባምንጭ ሙዝ በመጫን ወደ ደሴ ከተማ በተደጋጋሚ ይመላለሳሉ። ደሴ ኬላ ላይ ስለሚያጋጥማቸው ችግር  ሲገልጹ፤

"የቀረጥ ሰብሳቢዎቹ ለከፈልክው ክፍያ ምንም አይነት የሚሰጡህ ማስረጃ /ደረሰኝ/ የለም። ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በምትገባበት ሰዓት ፍትሃዊ የሆነ ቀረጥ ከፍለህ ክልሉን እስክትወጣ ድረስ የትኛውም ከተማ ላይ ተጨማሪ ቀረጥ አትጠየቅም። ለከፈልክበትም ህጋዊ ደረሰኝ ስለሚሰጥህ ያንን እያሳየህ ወደሚቀጥለው መዳረሻህ ትሄዳለህ" በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።

ሌላው አስተያየት የሰጠን አሽከርካሪ ጀማል አሊ "ደሴ ከተማ መግቢያ ኬላ ላይ የተጋነነ ቀረጥ ከፍለን ደሴን አልፈን የምንሄድ ከሆነ ደግሞ መውጫ ላይ ሌላ ቀረጥ እንባላለን። በአንድ ከተማ ላይ ሁለት ጊዜ መውጫና መግቢያ ላይ ማለት ነው። ይህ ከዚህ በፊት ያልነበረና ህጋዊነት የሌለው አሰራር ነው" ብሏል።

አሽከርካሪዎቹ እንደሚሉት ቀረጥ መክፈል ካለባቸው በየከተማው ከሚቆሙ ገንዘብ ጨምረው አንድ ቦታ ላይ ቢከፍሉ እንደሚመርጡ ተናግረዋል። ዳዊት ገብረሃና እንደሚሉት “ምክንያቱም በተያያ ቦታ በምንቆም ጊዜ በፍጥነት ለገበያ መቅረብ የሚገባቸው እንደ አትክልትና ፍራፍሬ አይነት የሚበላሹ ምርቶች ለብክነት ይዳረጋሉ።"

ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸውን የገለጹት አሽከርካሪዎች እንደሚሉት የቅሬታችን መነሻ ደሴ ከተማ ይሁን እንጂ እንደ ክልል ለተግባሩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ይገባዋል ያሉ ሲሆን አሰራሩን በዘመናዊ መንገድ መምራትና ህግን መከተል ቅድሚያ የሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

"ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ስለህጋዊነታቸው ከጠየቅን የሚያደርሱብን ወከባ እና ማጉላላት ከባድ ስለሆነ ያሉንን ፈጽመን ከመሄድ ውጭ ሌላ አማራጭ ስለማይኖር ሁል ጊዜ እየተጎዳን እንገኛለን"  ብለዋል አሽከርካሪዎቹ።

መንግስት በተለይም የአካባቢው አስተዳደር የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሄ ማምጣት ይገባዋል ተብሏል። በተለይም አሽከርካሪዎች በጣም ከመማረራቸው የተነሳ ስራ እስከማቆም የደረሱ መኖራቸውን ለማወቅ ችለናል።

የቅሬታ አቅራቢዎችን ሃሳብ በመያዝ ለደሴ ከተማ ገቢዎች መምሪያ ላነሳነው ጥያቄ የመምሪያው ኃላፊ አቶ መላኩ ሚካኤል ችግሩ መኖሩን አምነው የቀረጥ አሰባሰብ ሁኔታ ከደሴ ከተማ አልፎ አጠቃላይ የአማራ ክልል ችግር በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግርም ፈጥሯል ይላሉ፤ "የጭነት አገልግሎት እየሰጡ ከአንድ ሃገር ወደ ሌላ የሚሄዱ መኪኖች በክልሉ ወስጥ አንድ ጊዜ ቀረጥ ከከፈሉ በኋላ በየደረሱበት የክልሉ ከተማ ተጨማሪ የቀረጥ ክፍያ መክፈል አይገባቸውም"  ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተከናወኑ ስላሉት ተግባራት አቶ መላኩ ሲገልጹ " የክልሉ መንግስት አሁን ላይ ቀረጥ በመሰብሰብ ላይ የሚገኙ አካላት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ለጸጥታ አካላት ትዕዛዝ አስተላልፏል። ከዚህ በኋላም ላለው አሰራር በጥናት ላይ ተመስርቶ ጨረታ በማውጣት መንግስት የሚያወጣውን ሕግ አክብረው ለሚሰሩ አካላት እንዲተላለፍ ተወስኗል” ብለዋል። ቀረጥና መሰብሰብ የመምሪያው ተግባር መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ የስራ እድል ለመፍጠር ሲባል ይህ ሃላፊነት ለወጣቶች የሚተላለፍ መሆኑን ተናግረዋል። ኃላፊው እንዳሉት ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት በተለይም በአሽከርካሪዎች የሚደርሰውን መንገላታትና ያልተገባ ወጪ እንደሚያስቀሩ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በዚህ ሳምንት ፓርላማ ቀርበው ከተወካዮች በተነሱላቸው ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሲሰጡ በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለውን ህገወጥ እንቅስቃሴ አንስተው ይህ ተግባር ቀጣይነት እንደማይኖረው መግለጻቸው ይታወሳል።

አስተያየት