ቢሾፍቱ ከተማ በተቸራት ልዩ የተፈጥሮ ፀጋ፣ ባላት ምቹ የሆነ የአየር ፀባይ፣ እንዲሁም በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት መዳረሻነቷ ትታወቃለች። ከአዲስ አበባ በ47 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኘው ቢሾፍቱ በኦሮሚያ ክልል ስር ከሚገኙ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን፣ የቱሪዝም መዳረሻ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ቦታዎች መካከል ግንባር ቀደምት ናት።
የ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችን መተዋወቅ የጀመረችበት ወቅት መሆኑ ይታወቃል። በዘመኑ የባቡር መስመር ዝርጋታን ተከትለው ከተቆረቆሩ እና በሂደትም ካደጉ ከተሞች መካከል በ1917ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነገርላት የቢሾፍቱ ከተማ አንዷ ናት።
በቢሾፍቱ በርካታ ሀይቆች እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን የእነዚህ ሀይቆች መገኛም በተራራዎች መካከል ነው። በዚህም ምክንያት ቢሾፍቱ የሚለውን ስያሜ ለማግኘት እንደቻለች ነዋሪዎች ይናገራሉ። ቢሾፍቱ የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቋንቋ ቃል ሲሆን በአማርኛ “በውሃ የበለፀገች” የሚል ትርጓሜ አለው። ቢሾፍቱ ደብረዘይት በሚለው የቀድሞ ስሟም የምትታወቅ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ወ/ሮ ሰላምወርቅ ሸሪፍ የስም ለውጡን በተመለከተ “የከተማዋ ታሪካዊ ስያሜ ከብዙ ሀይቆች መገኛነቷ ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑ ታሪክ ይናገራል፣ ነገር ግን ከጣሊያን ወረራ በኋላ የአጼ ሀይለስላሴ ንጉሣዊ አስተዳደር ደብረዘይት የሚለውን ስም ለከተማው ሰጥተው ነበር” ሲሉ አስረድተዋል። እንደ ወ/ሮ የሰላምወርቅ ገለፃ የደርግ አገዛዝ ወድቆ የኢህአዴግ አገዛዝ መንበረ ስልጣኑን ሲቆጣጠር ከተማዋ ቢሾፍቱ የሚለውን ስም መልሳ ማግኘት ችላለች።
ቢሾፍቱ ነዋሪዎቿ በተለያየ ብሄር፣ ሀይማኖት እና ልዩ ልዩ መገለጫዎች ተሰባጥረው የሚገኙባት ስለመሆኗ ይነገርላታል። ወደ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ሳይቀር ለስራ የሚመላሱባት መሆኗ እና የህዝቡ የአኗኗር ዘይቤ ከአዲስ አበባ ብዙም ያልራቀ ነው።
ታዲያ በፍጥነት ሲገሰግስ ነበር የሚባልለት የዚህች ከተማ እድገት አሁን ላይ እያዘገመ ስለመሆኑ ነዋሪዎቿ ያነሳሉ። አዲስ ዘይቤም “በተፈጥሮዋ የታደለችው እና የቱሪስት መስህብ የሆነችው ከተማ እድገቷን የሚጎትት ምን ገጠማት?” ስትል ጥያቄ አነሳች።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ፣ አጠቃላይ ስፋቷ 20,774 ሄክታር እንደሚሸፍን ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በ14 ቀበሌዎችን የተደራጀችው ቢሾፍቱ ከተማ፣ 5 የገጠር ቀበሌዎችን እና 9 የቀበሌ ከተማዎችን ይዛ ትገኛለች። የከተማዋ ዙሪያ ለግብርና ስራ የተመቸ ስለመሆኑ ለማወቅ ጥቂት ዞር ዞር ማለት ይበቃል። በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች ከአመት አመት ልዩ ሰብሎችን በስፋት እንደሚያመርቱ ያነጋገርናቸው ገበሬዎች ይናገራሉ። በእሳተ ገሞራ አማካኝነት የተፈጠሩት ሰባት ሀይቆቿም ለከተማዋ የገቢ ምንጭነት ምን ያህል ጥቅም እንደሚሰጡ መገመት አያዳግትም። ነገር ግን ታገኛለች ተብሎ የሚገመተው ገቢ እና የከተማዋ እድገር ለየቅል ስለመሆኑ የከተማዋን ሁኔታ ተመልክቶ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
“ታዲያ ይህን ሁሉ የተፈጥሮ ሃብት፣ የከተማ አደረጃጀት፣ የቱሪስት መስህብነት ታድላ ሳለ ቢሾፍቱ የሚጠበቅባትን እድገት ማሳየት ለምን አዳገታት ብላችሁ ታስባላችሁ?” ስንል ለአንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ጥያቄ አነሳን።
ሮቤራ አያሌው የተባለ በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በአነስተኛ ንግድ የሚተዳደር ወጣት “ቢሾፍቱ ለሁሉም ነዋሪ ተስማሚ የሆነች ከተማ ናት፣ ማንም ሰው መጥቶ ተላምዶ ለመኖር ጊዜ አያወስበትም፣ ነገር ግን ከተማችን የሚያስፈልጋትን አይነት አስተዳደር ስለማግኘቷ እጠራጠራለሁ” ሲል አስተያየቱን ለአዲስ ዘይቤ አጋርቷል።
ሮቤራ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ትላልቅ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች በባለቤትነት የሚመሩ ግለሰቦችም ቢሆኑ፣ በያዙት ቦታ ላይ በሚሰሩት ስራ የሚያገኙትን ገቢ ከማሰብ በዘለለ ከተማዋ ለሰጠቻቸው የተፈጥሮ ስጦታ በምን መክፈል እንደሚችሉ የሚያስቡ እንደማይመስለው ይገልፃል። አክሎም “እነዚህ ሰዎች በመንግስት ዘንድ ከሌላው መደበኛ ነዋሪ ይልቅ ተሰሚነት አላቸው፣ የገቢ ምንጭ የሆነቻቸው ከተማ እድገቷ ሲጓተት ዝም ማለት የለባቸውም፤ ከተማዋ መሰረተ ልማቷ ቢሟላ እነሱም ከመደበኛው ነዋሪ እኩል ተጠቃሚ ይሆናሉ” በማለት ተናግሯል።
ሌላኛዋ ያነጋገርናት የከተማዋ ነዋሪ መርጊኔት ሮቤራ ትባላለች። በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ባለ አንድ መካከለኛ ሆቴል ውስጥ የመስተንግዶ ስራ ትሰራለች። መንግስት ቢሾፍቱን እየዘነጋት ነው የምትለው መርጊኔት “የአኗኗር ሁኔታችን እና ያለብን ወጪ የተመጣጠነ አይደለም” ስትልም ምሬቷን አካፍላናለች።
እንደ መርጊኔት አባባል፣ የቢሾፍቱ ከተማ የዋጋ ግሽበት ከመሃል አዲስ አበባ የተለየ አይደለም። ይሁን እንጂ ከመንግስት የሚያገኙት መሰረተ ልማት አገልግሎቶች በእጅጉ የተራራቀ መሆኑን ታብራራለች። “ቢሾፍቱ ማለት ሳሎኗ ውብ ሆኖ ጓዳዋ ያልተጸዳ መኖሪያ ቤት ማለት ናት” በማለት አብዛኛው የከተማ ነዋሪ በውሃ፣ በመብራት፣ በመንገድ ደህንነት እና በተለያዩ አስተዳደራዊ መፍትሄ በሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ ክፉኛ ተጎጂ መሆኑን ገልጻለች።
ይህንኑ የመርጊኔት ሃሳብ የሚያጠናክሩት ደግሞ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና በከተማዋ ውስጥ የሚገኝ ስመጥር ሆቴል እና ሪዞርት በባለቤትነት እና በስራ አስኪያጅነት የሚመሩ ግለሰብ “እርግጥ ነው የቢሾፍቱ ከተማ አብዛኛው ክፍል በመሰረተ ልማት በኩል የሚጠበቅበትን ያህል አልለማም፣ በዚህ ደግሞ ሁላችንም ተጎድተናል፣ ይህን ማስተካከል ያለበትም መንግስት ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አስተላልፈዋል።
“ትላልቅ ደረጃ ላይ ናቸው የሚባሉ የመዝናኛ ተቋማትን የምትመሩ አመራሮች ተሰሚነታችሁን ተጠቅማችሁ የከተማዋ እድገት ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ አልቻላችሁም፣ እገዛስ ለምን አላደረጋችሁም?” ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄም “መንግስትን በተለያየ መንገድ ከተማዋ ላይ የሚሰራው ስራ እንዲፋጠን ከመጠየቅ ቦዝነን አናውቅም” ሲሉ መልሰዋል።
በገንዘብና በልዩ ልዩ መንገዶች ለከተማዋ እገዛ ስላለማድረጋቸው የሚነሳ ቅሬታ ስለመኖሩ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲያብራሩ “ህዝቡ ያልተረዳው ነገር አሁን አሁን ሪዞርቶች ትልቅ መሬት ላይ ከመንጣለል ባለፈ የሚያገኙት ገቢ ሞልቶ የተረፈ የሚባል አለመሆኑን ነው” በማለት እንደኮቪድ ያሉ የተፈጥሮ ችግሮች እንዲሁም የፖለቲካ ጡዘት ያመጣቸው ሰው ሰራሽ ችግሮች በአንድም በሌላም መንገድ የሚያገኙት ገቢ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ የቀረቡትን ቅሬታዎች ይዘን ወደ ቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር በመሄድ፣ ከተማዋን በከንቲባነት መምራት ከጀመሩ ዘጠኝ ወራት ያስቆጠሩትን አቶ አለማየሁ አሰፋን አነጋግረናል። ከንቲባው “የቀረበው ቅሬታ መሰረተ ቢስ ነው ማለት ባይቻልም ነዋሪው ሊያገናዝበው የሚገባ ነገር አለ” በማለት የከተማዋ የእድገት ሁኔታ የተባለውን ያህል ወደ ኋላ እንዳልቀረ አስረድተዋል።
ከንቲባው ከተማዋ በዋነኛነት የገቢ ምንጯ የቱሪዝም መስህብነቷ መሆኑን በመጥቀስ ይህንንም በኮቪድ ሳቢያ የነበረው ገደብ በእጅጉ እንደጎዳት እና ከዚህም ለማገገም ጊዜ እንደሚያስፈልጋት አስረድተዋል። በሌላ በኩል እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ባለፉት 18 ወራት በሀገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ የመንግስት ዋነኛ የበጀት ድጋፍ ትኩረት ቅድሚያ ወደሚያስፈልጋቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ዞሮ ስለነበር ሌላ ተጽዕኖ እንደነበረው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
ከነዚህ ሁኔታዎች በተጨማሪም በ2009 በኢሬቻ በአል አከባበር ወቅት ተከስቶ የነበረው ግርግር ህዝቡን ለተዛባ መረጃ እና ፍራቻ ዳርጎት ስለነበር ላልተወሰነ ጊዜ ከተማዋ ከውዝግብ እስከምትጠራ ድረስ የእንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ነበር ብለዋል። በመሆኑም ቢሾፍቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥማትን ተግዳሮቶች እየተወጣች መንቀሳቀሷን አላቆመችም በማለት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ እና ምጣኔ ሀብት ኮሌጅ በህዝብ አስተዳደር እና በከተሞች እድገት አያያዝ ትምህርት ክፍል ውስጥ በከተሞች አመሰራረት እና እድገት ላይ ጥናት የሰሩት ወ/ሮ መስከረም ለገሰ “የከተማዋ የማስተር ፕላን አሰራር በጥናት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ በስሯ የሚገኙት ቤቶችና ህንፃዎች ትፍግፍግ ያሉ ናቸው። የከተማዋ ውበት በራሱ በእድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ሊታሰብበት ይገባል” በማለት ከፍ ያለ ኢንቨስትመንት እያደገ እንዲሄድ አሁንም ጥናት ሊደረግ ይገባል፤ አለበለዚያ እንደ አዲስ አበባ ተሰርተው የሚፈርሱ ብዙ ቤቶች እና ህንጻዎች እንደሚበዙ ያስረዳሉ። አክለውም “አሁንም የከተማዋን እድገት ወደ ኋላ የሚይዘው ምን እንዴት ይሰራ የሚለው ነገር ያልተጠና መሆኑ ይመስለኛል” ብለዋል።
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ አየር ሀይል፣ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ የጥበብ ማዕከላት እና መሰል ተቋማትን አቅፋ የያዘችው ቢሾፍቱ ከተማ በሕዝብ ብዛትም በኢኮኖሚውም በፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ ነች። የከተማዋን ተለዋዋጭነት በተለያዩ ገፅታዎቿ መመልከት ይቻላል። ከተማዋ ከሌሎች የክልሉ ከተሞች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ከተሞች አንዷ ናት። በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ከገጠር ወደከተማ እና ከከተማ ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት የከተማዋ የህዝብ ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። ታዲያ ነዋሪዎቿ እድገቷ ላይ ያላቸው ስጋት እየከፋ ሳይሄድ ይገታ ይሆን?